የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዘመን በይፋ ተጀምሯል። ዘንድሮ የሚታየው ፉክክር በሜዳ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ ቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ ሕጎች፣ የአሰልጣኞች ለውጥ እና የተጫዋቾች ጥራት የውድድሩን አቅጣጫ የሚወስኑ ዋና ነገሮች ሆነው ቀርበዋል። እንደ ቢቢሲ ስፖርት ትንታኔ የሊጉ የዳኝነት ስርዓት ማሻሻያዎች እና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም የጨዋታውን ፍጥነት እና ድባብ ከፍ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።
በዚህ ዓመት ከታዩት ትልልቅ ለውጦች አንዱ በዳኝነት ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተደረገው እድገት ነው። ከፊል አውቶማቲክ የኦፍሳይድ ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚደገፉ የውሳኔ ሂደቶች እና የቫር ውሳኔዎችን ፈጣን ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። ይህም ለተመልካቾች የተሻለ ልምድ እና ለዳኞች የበለጠ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጡ እንደሚያግዝ ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል።
ከሜዳ ውጪ ደግሞ የገንዘብ ቁጥጥር ሕጎች በክለቦች የዝውውር ፖሊሲ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው። ብዙ ክለቦች የገንዘብ ደንቦቹን ለማክበር የተጫዋቾች ግዢና ሽያጭ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ጀምረዋል። ይህም የሊጉን የኃይል ሚዛን ሊቀይር ይችላል።
ብዙ የስፖርት መገናኛ አውታሮች የዘንድሮው የዋንጫ ፉክክር ሲነሳ ቀዳሚ እጩ አድርገው የሚያስቀምጡት አርሴናልን ነው። የኦፕታ ትንበያ አርሴናል በሊጉ ውስጥ በጣም የተረጋጋ ስብስብ ካላቸው ክለቦች አንዱ መሆኑን ያመለክታል። ሚኬል አርቴታ በተከታታይ ዓመታት ቡድኑን በማሳደግ የሊጉን ምርጥ የኋላ ክፍል መገንባት ችሏል። ይሁን እንጂ በወሳኝ ጨዋታዎች የግብ እድሎችን በብቃት መጠቀም አሁንም ያልተፈታ ጥያቄ ሆኖ እስካሁን መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ማንቸስተር ሲቲ በሊጉ ውስጥ ካሉ በጣም አደገኛ ቡድኖች አንዱ ነው። የኤርሊንግ ሃላንድ የግብ ማግባት ብቃት እና የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ደረጃ አሁንም ትልቅ ኃይል ናቸው። ይሁን እንጂ በዘ አትሌቲክ ትንታኔ መሠረት የአሰልጣኝ ለውጥ እና አዲስ የጨዋታ ስርዓት በመጀመሪያዎቹ ወራት በቡድኑ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ።
ቼልሲ እና ሊቨርፑልም ከዋንጫ ፉክክሩ ውጪ ሊሆኑ እንደማይችሉ የዘ አትሌቲክ መረጃ አመልክቷል። ቼልሲ በወጣት እና ባለተሰጥኦዎች የተሞላ ስብስብ ቢኖረውም የቡድን ውህደት መፍጠር ላይ ግን ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል። የአንፊልዱ ክለብ በበኩሉ ፈጣን የማጥቃት ኃይሉን በመጠቀም በማንኛውም ጊዜ ለዋንጫ ፉክክር መመለስ ይችላል ተብሎ ይገመታል።
ከዋንጫ ፉክክሩ ባሻገር ለሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ የሚደረገው ፍልሚያም ከፍተኛ ትኩረት ይስባል። ኦፕታ እና ስካይ ስፖርትስ በሚያቀርቧቸው ግምቶች መሰረት አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲ ለአራቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታዎች ዋና ተፎካካሪዎች ናቸው። ኒውካስል ዩናይትድ፣ ቶተንሃም ሆትስፐር እና አስቶን ቪላ ደግሞ ለኢሮፓ ሊግ እና ለኮንፈረንስ ሊግ ቦታዎች ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ የሚል ግምት ከወዲሁ አግኝተዋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ የህልውና ፍልሚያ ሆኖ ይቀጥላል። የኦፕታ መረጃ እንደሚያሳየው አዲስ አዳጊዎቹ ኮንቨንትሪ ሲቲ፣ኢፕሲዊች ሲቲ እና ሀል ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ፍጥነት እና ጥራት ጋር ለመላመድ ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል። በተለይ የስብስብ ጥራት እና የልምድ እጥረት አዲስ አዳጊዎቹን ወደ ሻምፒዮንሺፕ ሊመልስ ይችላል።
ኢኤስፒኤን እንዳስነበበው የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ጫና፣ በፍጥነት እና በአካል ብቃት ላይ የተመሰረተ ይሆናል። አሰልጣኞች ተከላካዮችን ወደ አማካይ ክፍል በማስገባት እና የኳስ ቁጥጥርን በማሳደግ የጨዋታ ስርዓታቸውን እያዘመኑ ነው። ይህም ለተመልካቾች አስደሳች እና ያልተገመተ የውድድር ዘመን እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
የአሰልጣኞች ለውጥ፣ የፋይናንስ ሕጎች፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና የቡድኖች የተጫዋች ጥራት የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመንን ገጽታ ከወዲሁ ቀይረውታል። እስከ አሁን ባለው ግምት አርሴናል ለዋንጫው ቀዳሚ እጩ ቢሆንም ፕሪሚየር ሊጉ ሁልጊዜ የሚታወቀው ባልተጠበቁ ውጤቶች ነው። እናም የዋንጫው ባለቤት፣ የአውሮፓ ተሳታፊዎች እና የሚወርዱት ክለቦች ማንነት እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ አጓጊ ሆኖ ይቀጥላል። የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል? የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የኢሮፓ ሊግ እና የኮንፍረንስ ሊግ ተሳትፎንስ የትኞቹ ክለቦች ያረጋግጣሉ? የትኞቹ ክለቦችስ ይወርዳሉ? የእርስዎን ግምት ያጋሩን!፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


