ሕይወት የምትሰጥ ለምን ሕይወቷን ትጣ?

0
148

ልጅን ወደ ዓለም የማምጣት ደስታ በአፍታ ወደ አደጋ ሊለወጥ ይችላል። ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ ደም መፍሰስ ደግሞ የዚህ ክፉ አጋጣሚ ዋነኛ መንስኤ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው በየዓመቱ ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች በቅድመ፣ በወሊድ ወይም በድሕረ ወሊድ ወቅት ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ወደ 70 ሺህ የሚጠጉ እናቶች ደግሞ በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው መዳን ጠቅላላ ሆስፒታል የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶ/ር በሙሉ ፋሲካ እንደሚያስረዱት ደም መፍሰስ ከወሊድ በፊት፣ በወሊድ ጊዜ ወይም ከወሊድ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። በወሊድ ወቅት የሚከሰት ደም መፍሰስ ደግሞ በዓለም ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ለእናቶች ሞት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው።

ዶ/ር በሙሉ እንደገለጹት ከወሊድ በፊት የሚከሰት ደም መፍሰስ ከእንግዴ ልጅ ጋር (የእንግዴ ልጅ ከማህፀን ግድግዳ መላቀቅ ወይም የእንግዴ ልጅ ወደ ማህፀን በር ቀድሞ መጠጋት) በተያያዙ ችግሮች ሊመጣ ይችላል።  ከወሊድ በኋላ ግን የደም መፍሰስ ዋነኛ መንስኤ የማህፀን ድካም  ነው።

በመደበኛ ሁኔታ ልጅ ከተወለደ በኋላ ማህፀን በመኮማተር የእንግዴ ልጅ ከነበረበት ቦታ የሚመጣውን ደም መፍሰስ ይቆጣጠራል። ማህፀኑ በበቂ ሁኔታ ካልተጨነቀ ግን የደም ሥሮች በትክክል ስለማይዘጉ ከፍተኛ ደም ሊፈስ ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ የእንግዴ ልጅ ክፍል በማህፀን ውስጥ መቅረት፣ በማህፀን አንገትና በሴት ብልት ላይ በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ቁስል፣ የማህፀን መቀደድና የደም መርጋት ችግሮች ደም መፍሰስን ሊያስከትሉ ይችላሉ። አስፈላጊው ጉዳይ ግን የተለየ የአደጋ ምልክት የሌላት እናትም ድንገት ከወሊድ በኋላ የደም መፍሰስ ችግር ሊያጋጥማት ስለሚችል ሁሉም እናቶች በቅርብ ሙያዊ የህክምና ክትትል ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው ዶ/ር በሙሉ ያስገነዘቡት።

ማተርናል ኤንድ ቻይልድ ሄልዝ የተባለ ድርጅት  በምሥራቅ ኢትዮጵያ 13 የመንግሥት ሆስፒታሎችን ያካተተ አ.አ.አ በ2024 ጥናት አካሂዶ ነበር፤ ጥናቱ እንደሚያመላክተው 38 ሺህ 782 ወሊዶችን ተከትሎ 306 ሴቶች ከወሊድ በኋላ ደም መፍሰስ አጋጥሟቸዋል። በጥናቱ መሠረት የማህፀን በተለያዩ ምክንያች ሥራውን በአግባቡ አለማከናወን ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የደም መፍሰስ 77 በመቶ  ምክንያት መሆኑን ያመላክታል፡፡ ከተመዘገቡት 70 ሆስፒታሎች ውስጥ የእናቶች ሞት ደግሞ 19ኙ ከወሊድ በኋላ ከሚከሰት የደም መፍሰስ ጋር የተያያዙ እንደነበሩ አስነብቧል።

ከፍተኛ ደም መፍሰስ በአስቸኳይ ተገቢውን ሕክምና አግኝቶ ካልቆመ እናት በአጭር ጊዜ ብዙ ደም ልታጣ ትችላለች። ይህም የደም ግፊት መውረድ፣ የሰውነት አካላት በቂ ኦክስጅን አለማግኘት፣ ከባድ የደም እጥረት እና የኩላሊት፣ የልብ ወይም የአዕምሮ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።ችግሩ ከፍ ካለም  ለሞት ሊዳርጋትም ይችላል።

ይህንን አደጋ ለመቀነስ የቅድመ ወሊድ ክትትል ከእርግዝናው መጀመሪያ ጀምሮ ማድረግ፣ የደም እጥረትንና ሌሎች የአደጋ ሁኔታዎችን ቀድሞ ማወቅ፣ በሰለጠነ የጤና ባለሙያ መውለድና ከወሊድ በኋላ ወላዷን  በቅርብ መከታተል ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ዶ/ር በሙሉ አስገንዝበዋል።

ከልጁ መወለድ በኋላ የማህፀንን መኮማተር የሚያግዙ መድኃኒቶችን መስጠት  በተለይም ኦክሲቶሲን ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ አደጋን ለመቀነስ እንደሚረዱ ነው ያብራሩ፡፡ ይህንን በማድረግ እናትን ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ የሚከሰት ሞትን በእጅጉ ይቀንሳል።

የደም መፍሰስ ከተከሰተ ግን ጊዜ ሳይባክን ሕክምና መጀመር ወሳኝ ነው ያሉት ዶ/ር በሙሉ፤  ሕክምናው  የደም መጠንን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ የወላዷን የጤና ሁኔታ ከደም መፍሰሱ ጋር በማጣመር ቀድሞ እርምጃ መወሰድን ያበረታታሉ።

የደም መፍሰስን ለመቀነስ የሚረዳ መድኃኒት እና  የደም ሥር ፈሳሽ መስጠት፣ አስፈላጊ ከሆነ ደም መተካት እና ፈጣን እርምጃዎችን/ቀዶ ጥገና/ መውሰድ የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ወሳኝ  ድርጊቶች  መሆናቸውን ነው ያብራሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዘርፉ ባለሙያዎች በእርግዝና ክትትል ወቅት   ከወሊድ በኋላ ከባድ ደም መፍሰስን እናቶች “የወሊድ መደበኛ ነገር ነው” ብለው ማለፍ እንደሌለባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት አለባቸው ሲሉም መክረዋል።

ይህ ግንዛቤ የተፈጠረላት  እናትም ያልተለመደ ወይም በፍጥነት የሚጨምር ደም መፍሰስ፣ መፍዘዝ፣ ከፍተኛ ድካም፣ የልብ ምት መፍጠን ወይም ራስን የመሳት ስሜት ከተፈጠረባት ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም በማምራት እርዳታ በመፈለግ እራሷን ከከፋ አደጋ ለመጠበቅ በቂ እውቀት ይኖራታል ነው ያሉ።

በአጠቃላይ ከወሊድ በኋላ ደም መፍሰስ ሁልጊዜ ሊከላከል ባይቻልም ቀድሞ ምልክት በመለየትና ፈጣን ሕክምና በመስጠት ሞትንና ከባድ የጤና ጉዳትን በእጅጉ መቀነስ ይቻላል። የጥራት ያለው የቅድመ ወሊድ ክትትል፣ በሰለጠነ ባለሙያ መውለድ፣ ከወሊድ በኋላ በቅርብ መከታተልና ችግሩ ሲከሰት ያለመዘግየት ሕክምና መስጠት የእናቶችን ሕይወት ለማዳን ቁልፍ መፍትሔዎች መሆናቸውንም ነው ዶ/ር በሙሉ ያብራሩት።

 

መረጃ

የድህረ ወሊድ ጥንቃቄ እና ማገገሚያ ጊዜ በተለምዶ ከወሊድ በኋላ እስከ ስድስት  ሳምንታት (42 ቀናት) ድረስ ይቆያል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የእናት አካል ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመለሳል፤ ልዩ እንክብካቤና ክትትልም ይደረጋል።

ዋና ዋና የጥንቃቄ ጊዜያት

  • የመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት እስከ 48 ሰዓታት፦ ከፍተኛ የደም መፍሰስ እና የደም ግፊት አደጋ ሊኖር ስለሚችል ጥብቅ የህክምና ክትትል ይደረጋል።
  • የመጀመሪያዎቹ 2 ሳምንታት፦ አካላዊ ድካም ከፍተኛ የሚሆንበት፣ ማህፀን ወደ ቦታው የሚመለስበት እና የደም መፍሰስ (ሎቺያ) የሚቀንስበት ጊዜ ነው።
  • እስከ 6 ሳምንታት (አጠቃላይ ማገገም)፦ የድህረ ወሊድ ምርመራ የሚደረግበት፣ ስሜታዊ ሁኔታዎች የሚረጋጉበት እና አካል ሙሉ በሙሉ እረፍት የሚያስፈልገው ወሳኝ ወሰን ነው።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የነሐሴ  18  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here