የዘንድሮዉ ክረምት ምን ይዞ መጣ?

0
136

በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወቅት በበርካታ አካባቢዎች አርሶ አደሮች  ከጥዋት እስከ ማታ  በማሳቸው ላይ ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላሉ። ከእነዚህ ጠንካራ የልማት አርበኞች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦከምከም ወረዳ ጣራ ገዳም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጌጡ ደሴ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ፈጠነች ጌጡ ይጠቀሳሉ። የጋዜጣችን ዝግጅት ክፍል በአካባቢው ያለውን የሰብል ልማት እንቅስቃሴ እና የዘንድሮውን የክረምት እርሻ ገጽታ ለመቃኘት ከአርሶ አደሩ ጋር በስልክ አጭር ቆይታ አድርጓል።

አርሶ አደር ጌጡ ደሴ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ፈጠነች በአካባቢያቸው በግንባር ቀደም (በሞዴል) አርሶ አደርነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ዘንድሮም ቀድመው ማሳቸውን አርሰው በልዩ ልዩ ሰብሎች ሸፍነዋል። አርሶ አደሩ እንደሚሉት  አራት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማረስ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ሸፍነዋል። በማሳቸው ላይ ከዘሯቸው ሰብሎች መካከል ጤፍ፣ በቆሎ፣ ዘንጋዳ፣ ስንዴ፣ ገብስ እና ባቄላ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የሰብሎቹ የአሁን ላይ ቁመና እጅግ ተስፋ ሰጪ እና የሚያስደስት መሆኑን አርሶ አደሩ ሲናገሩ መደስታቸውን ድምጻቸው ያሳብቃል። በተለይም የማሽላው (ዘንጋዳው)፣ የጤፉ እና የስንዴው ቁመና በሚፈለገው መጠን እየዘነበ ባለው ዝናብ ታግዞ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ነው ያሉን።

የአቶ ጌጡ ማሳ ጥሩ  የሰብል ቁመና ሊያሳይ የቻለበት ሌላው ምክንያት በዘፈቀደ በሚደረግ እርሻ ሥራ ሳይሆን ዘመናዊ የግብርና ግብዓትን በአግባቡ በመጠቀም ጭምር ነው። አርሶ አደሩ በተለይም የጤፍ እና የበቆሎ  ማሳቸውን በምርጥ ዘር  ሸፍነዋል።

ከዚህም ባሻገር እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ ከመንግሥት ከቀረበላቸው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) አዘጋጅተው ተጠቅመዋል። በአሁኑ ወቅት በማሳቸው ላይ የስንዴ፣ የበቆሎ እና የባቄላ አረም የማረም ሥራ በስፋት እየሠሩ ይገኛሉ። ሰብላቸውን ከአረም ለመከላከልም የጉልበት ሥራን ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የፀረ-አረም ኬሚካል  ጭምር እየተጠቀሙ ነው። የዘንድሮውን ክረምት የአየር ንብረት በተመለከተ አቶ ጌጡ በዘንድሮው የምርት ዘመን መግቢያ ላይ የዝናቡ ሁኔታ ስጋት ፈጥሮባቸው እንደነበር ሲናገሩ፤ “ዝናቡ የክረምቱ መጀመሪያ ላይ በትንሹ ዘግየት ብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በየቀኑ በበቂ ሁኔታ እየዘነበ ነው። ዝናብ እና ፀሐይ እየተፈራረቀ ስለሆነ ሰብሉ በቂ ሙቀት አግኝቶ በፍጥነት እያደገ ይገኛል፤ ምንም አይነት የዝናብ እጥረትም ሆነ ስጋት የለም” ብለዋል። የሊቦከምከም ወረዳ አርሶ አደር የግብዓት አቅርቦቱ ጥሩ እንደነበር ቢነግሩንም በአንዳንድ ወረዳዎች ግብዓት በወቅቱ አለመድረስ እንቅፋት ነበር።

የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ በሪሁን እውነቱ ለበኵር በስልክ እንደገለጹት ወረዳው በዘንድሮው የመኸር እርሻ ያቀደውን ማሳ በዘር ሸፍኗል። በምርት ዘመኑ ከ36 ሺህ 527 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ነው ያስታወቁት። ከዚህ ውስጥ 21 ሺህ 355 ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም የለማ ሲሆን በዚህም ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ እና ገብስ በስፋት ተዘርተውበታል። ከእዚህም በተጨማሪ ባቄላ እና የቢራ ገብስ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎች አሁን ላይ ማሳውን አረንጓዴ ሸማ አስመስለውታል፡፡ አካባቢው ለዳግም ልማት ምቹ በመሆኑ በተለይም የቢራ ገብስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

በወረዳው ለምርት ዘመኑ 58 ሺህ 434 ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ  ታቅዶ እስካሁን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ የተቻለው 43 ሺህ 577 ኩንታል ነው፡፡ እንዲሁም 553 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል።

አቶ በሪሁን እንደሚያስረዱት የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ፣ በሚፈለገው መጠን እና በሚፈለገው ቦታ አለመቅረብ አርሶ አደሩን የፈተኑ ተግዳሮቶች ነበሩ። ይሁን እንጂ የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደሮች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። የአፈር ማዳበሪያ ቢዘገይም ቀድመው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት፣ ባዮ-ስላሪ እና አረንጓዴ ማዳበሪያ) በስፋት አዘጋጅተው ማሳቸውን በዘር መሸፈን ችለዋል፡፡ ሌላው አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ አቅራቢያው   ድረስ ባይቀርብለትም ተደራጅቶ ወረታ ድረስ በመሄድ ችግሩን ማቃለል ችሏል።

በዘንድሮው ክረምት ዝናብ  መዝነብ የጀመረው ዘግይቶ ሰኔ መጨረሻ  ነው። ይህ ቢሆንም አሁን ላይ እየጣለ ያለው ዝናብ የተስተካከለ በመሆኑ የሰብሉ ቁመና እጅግ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ይገኛል። የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደሮች ትጋት በመኸር እርሻ ብቻ የተገታ አይደለም። አቶ በሪሁን እንዳስታወቁት ከዋናው ሰብል በተጨማሪ በዳግም ልማት (በተለይም በመስኖ) ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው።

በአጠቃላይ የፋርጣ ወረዳ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከዳግም ልማቱ ጋር ተዳምሮ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ነው፡፡ አሁን ላይም ያለው የሰብል ቁመና፣ በ36 ሺህ 120 ሄክታር ላይ የተደረገው የአረም ቁጥጥር እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጠንካራ የሥራ ፍቅር የታቀደው ምርት እውን እንደሚሆን ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወቅት ያጋጠመው የዝናብ እጥረት በታቀደው የሰብል ምርት መጠን ላይ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን  ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን የሰብል ልማት ቡድን መሪ አስታውቋል። አካባቢው የበልግ አብቃይ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ቡድን መሪው አቶ  ደጀኔ ከበደ ከበኵር ጋዜጣ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በመኸር እርሻው ከ58 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ባለው 58 ሺህ 132 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል። ይሁን እንጂ የዝናቡ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ሰብሉ ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። በተለይም በባቲ ዙሪያ፣ ባቲ ከተማ፣ ደዋጨፋ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የዝናብ እጥረቱ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዝናብ እጥረቱ አሁን ባለበት ከቀጠለ በምርት መጠኑ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ሊያመጣ እንደሚችል ተገልጿል። ቡድን መሪው አክለውም “በምርት ዘመኑ  ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ቢታቀድም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህንን ማሳካት አዳጋች ነው፤ ግማሹ ማሳ ላይ ነው፣ ግማሹ አልበቀለም” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።

ይህንን የተፈጥሮ ፈተና ለመቋቋም ከቀበሌ እስከ ዞን  ድረስ ግብረ-ኀይል ተቋቁሞ የዕለት ተዕለት ክትትል እየተደረገ ይገኛል። በመፍትሔነትም አርሶ አደሮች ፈጥነው የሚደርሱ እና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን እንዲዘሩ፣ በአካባቢው ያሉ የውኃ አማራጮችን በማፈላለግ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም ሰብሉን እንዲያጠጡ የምክር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የዝናብ እጥረቱ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እና የከተማ አሥተዳደሮች የሚታይ ቢሆንም የግብርና ባለሙያዎች፣ የየደረጃው አመራሮችና አርሶ አደሩ በመቀናጀት ፈጥኖ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ እያደረጉ መሆኑ ገልጸዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የ2018/19 የምርት ዘመን እንዴት ነው? ስንልም ለዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ለአቶ ሰውመሆን ተገኘ በስልክ  ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ ዞኑ ባሕላዊውን አሠራር በመቀየር ወደ ዘመናዊ ሜካናይዜሽን እና የኩታ ገጠም እርሻ በስፋት በመሸጋገር ላይ ይገኛል። የዘንድሮው የክረምት እርሻ እንቅስቃሴ ከምንጊዜውም በተለየ መነቃቃት እና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ም/ኃላፊው ማብራሪያ በዞኑ በ2018/19 የምርት ዘመን ከ266 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ አርሶ አደሩ ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከ271 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማረስ ተችሏል። መረጃው እስከተጠናቀረበት ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከ262 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች  ተሸፍኗል። ምርታማነትን ለማሳደግም 39 ሺህ 550 ኩንታል  ከፍተኛ ምርት ሰጭ የሆኑ የምርጥ ዘር ዝርያዎች (በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና አኩሪ አተር) መጠቀም ተችሏል። በተጓዳኝም ከ458 ሺህ ኩንታል በላይ የዳፕ እና ዩሪያ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ማሳ ጥቅም ላይ ውሏል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ድካምን በሚቀንሰው እና ጊዜን በሚቆጥበው የትራክተር እርሻ 69 ሺህ 490 ሄክታር በ108 ትራክተሮች አርሶ ለዘር አብቅቷል።

የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ይበልጥ ለማፋጠን ደግሞ የዞኑ አሥተዳደር ከባንኮች ጋር በፈጠረው የብድር ትስስር አርሶ አደሮች፣ ዩኒየኖች እና ግለሰቦች በዘንድሮው ዓመት ብቻ 87 አዳዲስ ትራክተሮችን ገዝተው ወደ ሥራ አስገብተዋል።

በዞኑ በተለይም እንደ ደንበጫ፣ ጃቢ ጠህናን እና በመሳሰሉት ወረዳዎች በክረምቱ መግቢያ ላይ የነበረው የዝናብ መቆራረጥ ስጋት ፈጥሮ ነበር። በአራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው የበቆሎ ዘር  በነበረዉ የዝናብ እጥረት ተገልብጦ ድጋሜ ተዘርቷል፡፡ አሁን ላይ በዞኑ የዝናብ ስርጭቱ እጅግ አጥጋቢ በመሆኑ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አቶ ሰውመሆን ተገኘ  አረጋግጠዋል።

የግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊው ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ አሁን ያለው ምቹ የአየር ጸባይ እና የዝናብ ስርጭት ሳይቋረጥ በዚሁ ከቀጠለ በዞኑ ከሚለማው ከ266 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 14 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።

መረጃ

ሰብልን መንከባከብ የተትረፈረፈ እና ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት እጅግ ወሳኝ ተግባር ነው። ስለሆነም የተሻለ ምርት ለማግኘት መከናወን የሚገባቸው ዋና ዋና ተግባራት።

መሬቱን በድግግሞሽ ማረስ

ሰብልን በማፈራረቅ መዝራት

የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን መጠቀም እና በአግባቡ መዝራት

አረምን በወቅቱ ማረም

ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በአግባቡ መጠቀም

የተባይ እና የበሽታ መከላከል ሥራን ማጠናከር

ምርቱን በወቅቱ መሰብሰብ እና መሰል ተግባራት ናቸዉ፡፡

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የነሐሴ 18  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here