ነፃነት፣ ደስታ እና ውበት

0
143

በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር የነሐሴ ወር ማጠናቀቂያን ተከትሎ የሚመጣው ወቅት በበርካታ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ሁነቶች የተሞላ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች በሴቶች እና በልጃገረዶች ዘንድ በልዩ ድምቀት የሚከበረው የአሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በዓል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡

በዓሉ የጾመ ፍልሰታን ማጠናቀቅ ተከትሎ ከነሐሴ 16 እስከ 21 ባሉት ቀናት ውስጥ የሚከበር ሲሆን የሴቶች ነፃነት፣ የባህል እድገት እና የማህበረሰብ አንድነት መግለጫ በመሆን ያገለግላል፡፡

በዓሉ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መጠሪያ ቢኖረውም ይዘቱ እና መንፈሱ ግን ተመሳሳይ ነው። አሸንድዬ  በላስታ (ላሊበላ)፣ በሰሜን ወሎ፣ በጎንደር እና አካባቢው የሚጠራበት ስም ነው። ሻደይ በዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን በተለይም በሰቆጣ እና አካባቢዋ የሚታወቅበት መጠሪያ ነው። እንዲሁም ሶለል  በራያ ቆቦ እና አካባቢው የሚሰጠው ባህላዊ ስም ነው።

በዓሉ ሲደርስ ልጃገረዶች ወራት አቅደው ያዘጋጁትን ህብረ-ቀለም ያለው የሀበሻ ቀሚስ ይለብሳሉ፤ የቁንጮ፣ ጥልፍ እና ባህላዊ ሹሩባዎችን ይሰተካከላሉ፤ ጌጣጌጦቻቸውንም ያዘጋጃሉ።

የበዓሉ ዋነኛ ምሳሌያዊ ምልክት ደግሞ በወገባቸው ላይ የሚያስሩት ለምለም “የአሸንድዬ/የሻደይ ሳር” ነው። ይህ ሳር የለምለምነት፣ የአዲስ ተስፋ እና የህይወት መታደስ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ልጃገረዶቹ በቡድን ሆነው ከበሮ እየመቱ፣ እያጨበጨቡ እና በዜማ እየተጫወቱ ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር ቤተሰብን እና ማህበረሰቡን ያመሰግናሉ፣ ይመረቃሉ፤ ከቤተሰቦቹም ሽልማት እና ገጸ-በረከት ይቀበላሉ።

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶችማ/መምሪያ – ማኅበረ ቅዱሳን – የሰቆጣ ማእከል “በዓለ ፍልሰታና ሻደይ” በሚል ታሪካዊ እና ትውፊታዊ ትስስሩን አስቀምጦታል። “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የሻደይ በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና እንደሚናገሩት የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ የዘመን መለወጫ፣ የመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቈረጥ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልሰታ) እና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ከሻደይ በዓል ተያያዥነት ያላቸው ሲኾን በተለይ የእመቤታችን ትንሣኤ (በዓለ ፍልሰታ) ከሻደይ በዓል ጋር የጎላ ግንኙት እንዳለው የቤተ ክርስቲያን መምህራንና የሃገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡” ሲል አስፍሯል።

ይህ ሐታታ “እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኀጢአት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ ወደ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የኾነችው፣ የሰው ልጆች መመኪያ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ድካም ካረፈች በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡” ሲል አስፍሯል።

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጫዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርአያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ እንደዚሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ ነው ይላል።

ቅድስት ድንግል ማርያም በነሐሴ 16 ቀን በቅዱሳን መላእክት ሽብሸባ፣ ዕልልታና ዝማሬ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ ሐዋርያት በታላቅ ደስታ ይመለከቱ፤ ይደነቁም ነበር ይላል የሀይማኖቱ አስተምህሮ።

“ልጃገረዶችም ከቅዱሳን መላእክት ከተመለከቱት ሥርዓት በመነሣት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ ረጃጅምና ለምለም ቅጠል በወገባቸው አሥረው  እንደ መላእክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ፣ እያዘዋወሩና እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባስበው በፍቅርና በሐሴት የወቅቱ መታሰቢያ የኾነውን የሻደይን በዓል ያከብራሉ” ሲል ሐታታው አስነብቧል።

በበዓሉ ሴቶች የድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቍጠር ከበሮ አዘጋጅተው አሸንድዬ የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ  ይዘክራሉ፡፡

የልጃገረዶቹ በዓል እንዲሁ መዝፈን እና መጫዎት ብቻ አይደለም። ይልቁንም  ዐበይት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ያሉት ነው።

የሴቶች ነፃነት እና ስነ-ፆታ እኩልነት

አሸንድዬ/ሻደይ የሴቶች ነፃነት በግልጽ የሚንፀባረቅበት ሁነት ነው። በበዓሉ ቀናት ልጃገረዶች ያለምንም ማህበራዊ ጫና እና ገደብ ሀሳባቸውን፣ ፍላጎታቸውን፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ወቀሳዎቻቸውን በዜማ እና በግጥም ያቀርባሉ። በተጨማሪም በቡድን ደረጃ መሪዎቻቸውን በመምረጥ፣ ስራዎችን በመከፋፈል እና በዓሉን በመምራት የአመራርነት ክህሎታቸውን ያዳብራሉ።

ማህበራዊ ትስስር እና እርቅ

በዓሉ በህብረተሰቡ መካከል ያለውን የጋራ ትስስር፣ ወንድማማችነት እና ፍቅር ያጠናክራል። በበዓሉ ወቅት ቂም እና ጠብ ይወገዳል፤ ይቅርታ እና እርቅ ሰፊ ቦታ ይሰጠዋል። ከዚህ በፊት የተቀያየሙ ቢኖሩ ለበዓሉ አብሮነት ሲሉ ሰላም ያወርዳሉ።

 

የባህል እና ሀገር በቀል እውቀት ጥበቃ

የባህላዊ አልባሳት አሰራር፣ የሹሩባ ስታይሎች፣ የከበሮ አመታት ጥበብ እና የቃል ግጥሞች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይበላሹ እንዲሸጋገሩ ትልቅ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። አሁን በፍጥነት በዓለማቀፋዊነት ወጀብ ለሚከንፈው የባህል ለውጥ እንዲህ ዓይነት በዓላት አዲሱ ትውልድ ወደ ኋላ ሄዶ እንዲያስብ እና መነሻውን እንዲመረምር ያግዛሉ።

የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ እድገት

በዓሉ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ወደ ላሊበላ፣ ሰቆጣ እና ቆቦ በመሳብ ለአካባቢው ኢኮኖሚ ከፍተኛ መነቃቃትን ይፈጥራል። ለአነስተኛ ነጋዴዎች፣ ለሆቴል ባለቤቶች፣ ለትራንስፖርት ሰጪዎች እና ለባህል አልባሳት ሰሪዎች የገቢ ምንጭ ይሆናል።

የአሸንድዬ/ሻደይ/ሶለል በዓል ማህበራዊ፣ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን አስመልክቶ በሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል።

በአፀደ ተፈራ፣ ተስፋዬ ፈንታው እና ካሳ ንጉስ  በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሰራው ጥናት በዓሉ በሰሜን ወሎ እና በዋግኸምራ ማህበረሰቦች ዘንድ ያለውን ታሪካዊ መሠረት፣ የማህበራዊ ትስስር እሴት እና በባህል ጥበቃ ላይ ያለውን ሚና በጥበብ ገልጿል። ጥናቱ እንደሚያመላክተው በዓሉ የሴቶችን ማህበራዊ ድምፅ ከፍ ለማድረግ ካላቸው አቅሞች ሁሉ ትልቁ ተፈጥሯዊ መድረክ ነው።

በደብረ ብርሀን ዩንቨርሲቲ በዶክተር ዘመኑ ቢረስ የተሰራው  ጥናት የአሸንድዬ በዓል በላሊበላ ከተማ የቱሪዝም እድገት ላይ ያለውን አዎንታዊ ተፅዕኖ በዝርዝር አሳይቷል። በጥናቱ መሠረት በዓሉ የቱሪዝም ፍሰትን በመጨመር፣ ለአካባቢው ህብረተሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የክልሉን በጎ ገፅታ በመገንባት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።

የኢትዮጵያ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የቅርስነት ጥናት እና መዝገብ ሰነድ  አዘጋጅቷል። በዚያ ሰነድ የልጃገረዶች ጨዋታ የማይጨበጥ የዓለም የባህል ቅርስ  ሆኖ እንዲመዘገብ ለዩኔስኮ የቀረበው ሰነድ የበዓሉን ዓለም አቀፋዊ የባህል እሴት በሚገባ ያሳያል።

የአሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በዓል ተራ የደስታ ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆን የሴቶች ነፃነት መግለጫ፣ የባህል እድገት መስተዋት እና የኢኮኖሚ እድገት ሞተር ነው። ይህንን ድንቅ ሀገር በቀል ቅርስ ዘመኑ ከሚያመጣቸው አሉታዊ የባህል ብክለቶች ጠብቆ ማቆየት፣ በዩኔስኮ የማስመዝገብ ሂደቱን ማፋጠን እና የቱሪዝም አቅሙን በስፋት መጠቀም የመንግሥት፣ የጥናት ተቋማት እና የመላው ህብረተሰብ የጋራ ኃላፊነት ሆኖ ይታያል።ማረፊያ

የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በዓል መቼ እና እንዴት መከበር እንደጀመረ በጥናት የታወቀ ባይሆንም አፈ-ታሪኮች እና አንዳንድ ሊቃውንት ክብረ በዓሉ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሙሴ ዘመን መከበር እንደጀመረ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ልጃገረዶች ለዘመናት ለበዓሉ የሚያሰሙትን ግጥም ነው፡፡

“አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ

ፍስስ በይ በቀሚሴ፡፡

አበሙሴ፣ ወርቅ አበሙሴ

ፍስስ በይ በቀሚሴ፡፡”

በዓሉ ከኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ መጎደል እና ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋርም በቀጥታ እንደሚገናኝ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡

ምንጭ፡-Visit Amhara

(አቢብ በዓለሜ)

በኲር የነሐሴ  18  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here