የነሐሴ ድምቀቶች

0
254

ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዋግኽምራ፣ በላስታ እና በራያ አካባቢ በስፋት የሚከበሩ ባሕላዊ ጨዋታዎች ናቸው፤ በሌሎች አካባቢዎችም  የሚታወቁ  እና የሚከበሩ ናቸው፡፡ በዓሉ ከተፈጥሯዊ፣ ከታሪካዊ እና ከባሕላዊ መስህቦች ውስጥ አንዱ እና የፆመ ፍልሰታ መጨረሻ በሆነዉ ነሃሴ 16 ቀን በድምቀት ተጀምሮ ነሐሴ 21 ይጠናቀቃል፡፡

ነሐሴ ወር በገባ በ15ኛው ቀን ልጃገረዶች ወደ ጫካ ወርደው በወገባቸው የሚታጠቁትን በአካባቢው አጠራር የሻደይ ቅጠል የሚሰበስቡበት ነው፡፡ ቅጠሉ የሚሰበሰበውም ገደላማ ከሆነ ስፍራ ላይ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ ልጃገረዶቹን አውሬ እንዳይተናኮላቸው ወይንም ሌሎች ጉዳቶች እንዳይድርሱባቸው በሚል የአካባቢው ጎረምሳዎች ከአቅራቢያቸዉ በመሆን ይጠብቋቸዋል፡፡

በነሐሴ 15 ምሽት ልጃገረዶች የሰበሰቡትን የሻደይ ቅጠል ሲጎነጉኑ ያመሻሉ፤ ምናልባት እንኳን እንዴት እንደሚጎነጎን ካልቻሉ እናቶቻቸው ወይንም ታላላቅ እህቶቻቸው እንዲሠሩ ላቸው  ያደርጋሉ፡፡

ነሐሴ 16 የበዓሉ አከባበር በይፋ የሚጀምርበት ዕለት ነው፡፡ ልጃገረዶች እርስ በእርስ ተጠራርተው ይሰባሰባሉ፡፡ በበዓሉ ሰሞን ሥራ የምትታዘዝ ልጅ የለችም። ምክንያቱም እነዚህ ቀናት ሴቷ በይፋ ነጻነቷን የምታውጅበት ነው፡፡ እነዚህ በዓላት በተለይ ልጃገረዶች አደባባይ በመውጣት በድምቀት የሚያከብሯቸው በመሆናቸው የልጃገረዶች የነፃነት በዓላት በመባል ይታወቃል፡፡

የዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳር  የሰቆጣ ከተማ ተወላጅ እና የባህል አምባሳደር ወ/ሮ ቤዛዊት ወዳይ ለበኵር ጋዜጣ   እንደገለፁት ሻደይ  ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊት ያለው ባህል ነው፤ በተለይ ለልጃገረዶች የተለየ ድባብ እና ስሜት አለው፡፡

ሻደይ ሴቶቹ በወገባቸው የሚያስሩት ቅጠል ስያሜ ሲሆን ወርሃ ነሐሴን በየዓመቱ በናፍቆት የሚጠብቅ፣ እንደየ ዕድሜ ክልላቸው የተለየ አለባበስ የሚጠይቅ(ያገባ ፣ያላገባ፣ የታጨ፣ያልታጨ) የፀጉር አሠራር እንዲሁም አጊያጊያጥ ያለው ባህላው እሴት እንደሆነ ነው ወ/ሮ ቤዛዊት የገለጹት፡፡

የሻደይ ዝግጅት የሚጀምረው ከሳምንት በፊት ሲሆን የአንድ ሰፈር ሰዎች በመሰባሰብ የሚለብሷቸውን አልባሳት በመምረጥ፣ ጌጣጌጦችን በመግዛትና በመጨረሻም ቡድኑን የሚያስተባብር አንድ ሰብሳቢም በመምረጥ ይጀመራል።

አከባበሩ በሦስት የእድሜ እርከን እስከ 10 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት፤ ከ10 እስከ 15 ዓመት እና ከ15 ዓመት በላይ በሚል ይከፈላል፡፡

ከ15 ዓመት በላይ የሆኑት ድኮት (የእጅ አምባር)፣ በአንገታቸው ሁለት አይነት መስቀል እና  ድሪ፣ ለእግራቸው የብር አልቦ አድርገው እና  በጥልፍ ቀሚስ ተሽቆጥቁጠው ይሄዳሉ። ከ15 ዓመት በታች የሆኑት ደግሞ ከብር የተሠራ ድሪ፤ ትልልቅ ክብ ቀለበት ቅርጽ ያለው የጆሮ ጌጥ ያደርጋሉ፡፡  ከ10 ዓመት በታች የሆኑት ፀጉራቸው ቁንጮና ጋሜ (መሀል ፀገራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩ ያደገ) ይሆናል። ጉዟቸውንም የሚጀምሩት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ነበር፡፡   በቀድሞው ጊዜ  ከቤተክርስቲያን መልስ ወደ አካባቢው አስተዳደር ወይም ሀገረ ገዥው  ቤት እንዲሁም በአካባቢው ወዳሉ ታላላቅ ሰዎች ይሄዱ እንደነበር ወ/ሮ ቤዛዊት አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከቤተክርስቲን መልስ  በአካባቢያቸው ያሉ ትልልቅ ሰዎች ቤት በመሄድ ዘፈናቸውን ይጀምራሉ።

በዓሉ ለልጃገረዶች እና ሴቶች የተለየ ስሜት አለው የሚባለው  በገጠሩም ሆነ በከተማው ሴት ልጅ በየቀኑ ካለባት የሥራ ጫና ትላቀቃለች፡፡  ከነሐሴ 16 እስከ 21 ባሉት ቀናትም ልጃገረዶች በዓሉን ለማክበር ቤተሰብ እምነት ጥሎ ከቤታቸው  በጠዋት ወጥተው ከሌሎች ጓደኞቻቸው  ጋር ተሰባስበው ጎረቤት የሚያድሩበት እና  የሚጨፍሩበት የነጻነት ወቅት ስለሆነ ነው፡፡

ወ/ሮ ቤዛዊት እንደሚሉት የበዓሉ ቀን ሲጀምር ጨዋታው ራስን አስጊጦ በአቅራቢያው ባለው ቤተክርስቲያን በመሄድ ፤

ተስቤ ተስቤ ተስቤ እንደእባቡ

አወይ ብላ ደጃፍ ገባሁ ከክበቡ፡፡

በማለት ለማመስገን መምጣታቸውን በዘፈን ግጥም በመደርደር  በማመስገን ይጀመራል፡፡ ቤተክርስቲያን ባለው ቆይታ ሴቶቹ ወገባቸው ላይ ካለው  ሻደይ ቅጠል  ጫፍ ላይ ያለውን ነጩን  ቆርጠው ለቤተክርስያን በመጎዝጎዝ ይወጣሉ፡፡

ከዛ በኋላ ደግሞ በሰፈሩ ካሉ ትልልቅ አባቶች ቤት በመሄድ ፦

አስገባኝ በረኛ – የጌታዬ ዳኛ፤

አስገባኝ – ከልካይ እመቤቴን ላይ…

በማለት መጨፈር ሲጀምሩ በሩ  ይከፈትላቸዋል፡፡

ይሄ የማን ነው አዳራሽ፣

የጌታየ የድርብ ለባሽ፤

ይሄ የማን ነው ደጅ፣

የእመቤቴ የቀጭን ለባሽ፡፡

በማለት ዘፈናቸውን ይቀጥላሉ።

ሻደይ በተለይ በሰቆጣ ልጃገረዶች፤

አሽከር አበባየ አሽከር ይሙት፣

ይሙት ይላሉ የኔታ፣

አሽከር አይደለም ወይ የሚሆነው ጌታ፡፡

በማለት በር ተከፍቶላቸው እስኪገቡ እንደሚጨፍሩ ወ/ሮ ቤዛዊት አብራርተዋል፡፡ ወደ ቤት ከገቡ በኋላ ደግሞ የቤቱን ባለቤቶች፤

ከፈረስ አፍንጫ ይወጣል ትንኝ፣

እሰይ የኔ ጌታ ጤና ይስጥልኝ፡፡

ምድር ጭሬ፣ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ፣

እሰይ የኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ፡፡

በማለት ያወድሳሉ፡፡

ስለለየ፣ ስለለየ ….እሰይ፣

የኔ እመቤት የፈተለችው፣

ሸማኔ ታጥቶ ማርያም ሠራችው፤ በማለት  ሙገሳው ይቀጥላል።

ዘፍነው ሽልማት ካልተሰጣቸው ወይ ከዘገየ ደግሞ፤

አንቱን አይደለም የማወሳሳው

ቀና ብለው እዩኝ የሰው ጡር አለው፡፡ ብለው በነገር ሸንቆጥ ያደርጓቸዋል።

ታዲያ ይላሉ ወ/ሮ ቤዛዊት ከቤቱ ያለው ዝናርም ሆነ የግብርና እቃ እየታየ ነው ግጥም የሚገጠመው፤ ለምሳሌ

እዩት እዛ ማዶ ተሰቅሏል ዝናሩ፣

እዩት የኔ ጌታ ሲታጠቅ ማማሩ፡፡

 

ትልልቅ ሴቶችን ደግሞ፡-

ምድር  ጭሬ ጭሬ  አወጣሁ መግላሊት፣

እሰይ የኔ እመቤት የልቤ መድኋኒት፡፡ በማለት ያሞግሳሉ

በዚያን ቀን ያው ሽልማት መስጠት ግድ ነው፤ እሱን ተቀብለው፤

አበባየ ነሽ አበባየ ጉዳይ፣

ሰመረች በአንች ላይ፡፡ እያሉ ወደ ሌላ መንደር ይሄዳሉ።

ወ/ሮ ቤዛ እንደሚሉት ዘፈኑ በየቤቱ ብቻ ሳይሆን በመንገድ ላይ የተገኘውን ግለሰብ ሁሉ እያቆሙ መዝፈን እና ማሞገስ ይኖራል፡፡

ሰው ሁሉ ሲሠጠኝ አንድ አንድ ብር ነው፣

የኔማ ጌታዬ እጁ እንደሞላ ነው፡፡ በማለት ይሞገሳል፡፡

ታዲያ ህብረተሰቡም አያሳፍራቸውም፤ማር እና ቂቤው ይዛቃል፤ ወተትም ይቀዳል፣ በጥሬ ገንዘብም የሚያበረክት አለ። የሚበላው ለፍቅር እና ለአብሮነት ማዕድ ይዘጋጃል፤ ጥሬ ገንዘቡ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ጧፍ ተገዝቶ እና ጥሬ ብሩ ገቢ ይደረጋል።

የዋግ ልጃገረዶችን በነሐሴ ወር ሻደይ ሲጨፍሩ   ማየት ደግሞ እንግዳ ትዕይንት አይደለም። ሕብረ ዝማሬው፣ የሴቶቹ ውበት፣ አጊያጊያጥ እና አለባበሳቸው ዐይን፣ ጆሮ እና ቀልብን ይይዛሉ።

በዚህ ወቅት ደግሞ ያላገባች ሴት የምትታጭበት ማህበራዊ ክዋኔም አለው፤ ልቡ ልጅቱን ለቁምነገር የከጀለ ወጣት ወገቧ ላይ ካለው ሻደይ በጥሶ በመውሰድ ፍላጎቱን ያሳያል፤ እሷም ፍላጎት ካላት የወንዱ ቤተሰብ ለሴቷ ቤተሰብ ማርዳ የሚባል ጌጥ በመግዛት ልጅቱን ለልጃቸዉ መፈለጋቸዉን ያስታውቃሉ፡፡

ባህሉ ዛሬ ላይ ከሰቆጣ ከተማ አልፎ አጎራባች አካባቢዎች ድረስ በመድረስ በጋራ የሚያከብሩት፣ ከእነርሱ ባለፈ የሌላውን አካባቢ ባህል የሚያዩበት ፣ እንደ ሀገር ደግሞ ጠቅለል ብሎ የሚከበር እየሆነ መምጣቱን  ያነሱት ወ/ሮ ቤዛ፤ ወደ ፊት ደግሞ እንደ ሀገር የቱሪስት መሥህብ በመሆን ተጠናክሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚተላለፍ አስገንዝበዋል፡፡

መረጃ

 

ሻደይ፣ አሸንድዬ  እና  አሸንዳ  በክልሎች እና በየአካባቢዎች የሚታወቁባቸው ስያሜዎች

  • ሻደይ፦ በዋግ ኽምራ (ሰቆጣ እና አካባቢው)
  • አሸንድዬ፦ በላስታ (ላልይበላ እና አካባቢው)
  • ሶለል፦ በራያ እና ቆቦ አካባቢ

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ  18  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here