የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥትንና ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የወጡ ሕጎችን፣ ሀገሪቱ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የእስረኛ አያያዝ ደረጃዎችን ባከበረ ሁኔታ በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎችን ማስፈፀም በሚያስችል ሁኔታ ማደራጀት በማስፈለጉ እንደተቋቋመ አዋጁ ያስቀምጣል፡፡
ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ሰብአዊ ክብርና መብት በማክበር እንዲሁም ግላዊ ሁኔታ በሚጠይቀው የፍርድ አፈፃፀምና እርማት ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግና ከሕብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ሥርዓት መደንገግ በማስፈለጉ፣ ታራሚዎች ባላቸው (በፈፀሙት) አደገኛ ወንጀል፣ ያላቸው የአደገኛነት ባህሪ ወይም ባላቸው የጉዳት ተጋላጭነት ወይም በፆታቸው እንዲሁም ከፍርድ በፊት በማረፊያ ቤቶች የሚቆዩ እስረኞች ሊደረግላቸው የሚገባውን አያያዝ መደንገግ በማስፈለጉ፤ ማረሚያ ቤቶች ለእስረኞች እንዲሁም ለመላው ሕብረተሰብ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የተቀላጠፈ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበትን ሕጋዊ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 ንኡስ አንቀፅ አንድ መሠረት ተደንግጎ ተቋቁሟል፡፡
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሐኑ ጎሽም የክልሉን ማረሚያ ቤቶች የ2018 ዓ.ም አፈፃፀም እና የ2019 እቅድ ከባለድርሻ አካላት እና ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ጋር ከሰሞኑ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱም ኃላፊው እንደገለፁት ወንጀል ክስተት ስለሆነ በማንኛውም ሁኔታ ድርጊት ፈፃሚውን አግልሎ አንፆ እና አምራች ዜጋ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ማረሚያ ቤቶች የመቅጫ ሳይሆኑ የእርምት እና ፀባይን የማነፃ ማዕከላት ናቸው የሚባሉት። ማነጽ እና ማረም በአንድ ጊዜ የሚሠራ ባለመሆኑ ጊዜ ይወስዳል፤ ይህንን ለማሳካት ደግሞ በዋናነት ለታራሚዎች የሥነ ምግባር፣ የሥነ ዜጋ እና የሥነ ልቦና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህ የማረም እና የማነፅ ተግባር ወንጀልን ቀንሶ ማህበራዊ ሰላም ማስፈን ያስችላል፡፡
የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 295/2017 መሠረት ተጠሪነቱ ለፍትሕ ቢሮ ከሆነ ወዲህ ማረሚያ ቤቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ታራሚዎችን እንዲቀበሉ በማድረግ እና የታራሚዎችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በማስከበር ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡንም አቶ ብርሐኑ ጠቅሰዋል። በማረሚያ ቤት የገቡ ታራሚዎች የሙያ፣ የቀለም እና የሥነ ልቦና ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ፊት ለሚመሩት ሕይወት አምራች ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ ይሠራል።
በተያዘው በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራበታል ተብለው ከተቀመጡ አቅጣጫዎች አንዱ የወቅቱን የኑሮ ውድነት ያገናዘበ የታራሚዎች የምግብ ዋጋ ማሻሻያ ማድረግ ነው። ሌላው ቀጣይ በትኩረት የሚሠራው ሥራ ደግሞ የፖሊስ ኀይሉን በቁጥር፣ በጥራት እና በሥነ ምግባር ማጠናከር፤ አገልግሎት አሰጣጡን ከሰው ንክኪ ነጻ ማድረግ እና ታራሚዎች ባሉበት አካባቢ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉበትን አሠራር ማስፋፋት ላይም እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል። የማረሚያ ቤቶችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ እና ከፍትሕ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከርም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የሰሜን ሸዋ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር የቻለሰው አሰፋ በበኩላቸው ታራሚዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ፣ የሥነ ምግባር እና የአዕምሮ ለውጥ አግኝተው እንዲወጡ እንደ ዞን እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ታራሚዎች በልስብ ስፌት፣ በብረታ ብረት፣ በእንጨት ሥራ…. ስልጠና ወስደው እዛው እያሉ አምርተው በመሸጥ ውጭ ያለውን ቤተሰብ በገቢ እንዲደግፉ አስችሏቸዋል፡፡ ዘንድሮ በዞን ደረጃ በቅርጻ ቅርጽ ሥራ የላቀ አፈጻጸም ያሳየ ታራሚ ሽልማት አግኝቷል፡፡
ይሄም ማረሚያ ቤቶች ፀባያቸውን ከማረም ባሻገር በሥራ እርስ በርሳቸው የተወዳዳሪነት ማዕከል እየሆኑ መምጣቱን ማሳያ እንደሆነም ነው የገለፁት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አበበ አዳነ በ2017 ዓ.ም ጉዳት ደርሶበት የነበረው የዳባት ማረሚያ ቤት ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ማረሚያ ቤት ወንጀለኛን በእስራት ቀጥቶ ማውጫ ሳይሆን በዕውቀት አንጾ ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቅል ተቋም ለማድረግ በትጋት እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ፍርደኞች እና በፍርድ ቤት ቀጠሮ የሚጠብቁትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ የሚወጡበት እና ልዩ ልዩ ሙያ ይዘው ራሳቸውን እና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ አስፈላጊውን መሠረታዊ እውቀት የሚገበዩበት ተቋም መሆኑንም ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ የ2018 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸም እና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ግምገማ ላይ እንደገለፁት በክልሉ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ዳግም ተጠግነው ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው ታራሚዎችን ተቀብለው በማነጽ እና በማረም ሥራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በቆይታቸው አርሞ ከማውጣት ባለፈ አምራች ዜጋ የሚያደርጉ የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኙም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
ታራሚው በማረሚያ ቤት ሲቆይ የሚፈጠረውን የሕይወት ክፍተት ለመሙላት እንዲሁም ተመልሶ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀል ወደ ኋላ እንዳይቀር አስፈላጊው የትምህርት መሰረተ ልማት እስከ 10ኛ ክፍል የሚያስቀጥል መደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይሰጣል፡፡
ታራሚዎችም በተማሩት መሰረት አስፈላጊውን የሙያ ብቃት ምዘና (ሲኦሲ) አልፈው በብቃት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ነው ኮሚሽነር ሀብታሙ የገለፁት።
እንጨትሥራ፣ ግብርና፣ ፀጉርሥራ፣ ብረታብረት፣ ሽመና…በመሥራት የሙያ ባለቤት በመሆን ገቢ እየፈጠሩ መሆኑን ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በፀጉር ሙያ የሠለጠኑ ሲወጡ እቃ በመግዛት የሚሠሩበትን መንገድ የማመቻቸት ተግባር እንደሚሠራ ነው የገለፁት፡፡
ልጆቻቸውን ይዘው ለሚገቡ ታራሚዎች ለልጆቻቸው መማሪያ በባሕር ዳር ማረሚያ ቤት ቅድመ መደበኛ መጀመሩን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡ ይሄ ልምድ ወደ ሌሎቹም እንደሚሠፋ አስገንዝበዋል፡፡
ሰዎች ውጭ ላይ በጥርጣሬ የሚመለከቱት ዋናው ጉዳይ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያለውን የሠብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ አስተያየት የሠጡን ኮሚሽነሩ፤ ምንም ዓይነት ኢ ሰብዓዊ አያያዝ እንደሌለ በየጊዜው የሚመለከተው የሰብዓዊ መብት አካላት መጎብኘቱን አንስተው አሠራሩ ሙሉ በሙሉ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ሲመጣ ብቻ የሚከናወን እና ከሕግ ውጭ በግለሰቦች ፈቃድ የሚታሰር ታራሚ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡
በ2019 በጀት ዓመት በዋናነት የሚሠራው ተቋሙን ማዘመን፣ የታራሚዎችን መረጃ አያያዝ እና ጥበቃን በሲሲቲቪ ካሜራዎች ዲጂታላይዝ ማድረግ እና ታራሚዎች ሲወጡ የሥራ ዕድል እና የሥራ መሣሪያ ድጋፍ አግኝተው ከማኅበረሰቡ ጋር በዘላቂነት የሚቀላቀሉበትን አሠራር መዘርጋት ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።
የሕግ አንቀጽ
ሰብዓዊ መብቶች በርካታ መለያ ባህሪያት ያሏቸው ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
- ተፈጥሮአዊነት፡- ሰብዓዊ መብቶች በማንኛውም የመንግሥት አካል ወይም በማንኛውም ሰው የሚሰጡ ሳይሆን የሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚያገኛቸው በመሆኑ ተፈጠሮአዊ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች የሚገኙት በስጦታ፣ በግዢ ወይም በውርስ ሳይሆን የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ካለው ክብር እና ዋጋ የተነሳ ነው፡፡
- ሁሉን አቀፋዊነት፡- ሰብዓዊ መብቶች በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰብዓዊ ፍጡራን ተመሳሳይ ክብርና እውቅና የሚሰጡ መብቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ሰብዓዊ መብቶች በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በልደት፣ በሀብት ደረጃ ወይም በሌላ ልዩነት ሳይደረግ መከበር አለባቸው፡፡
- የማይገፈፉ ወይም የማይገረሰሱ ናቸው፡- ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ከማንም ሰው ላይ ሊገፈፉ ወይም ሊገረሰሱ አይችሉም፡፡ ማንም ሰው የማንንም ሰው ሰብዓዊ መብት ሊነጥቅ ካለመቻሉም በላይ ሰዎች እነዚህን መብቶችን አሳልፈው ሊሰጡም አይችሉም፡፡
- የማይነጣጠሉና ተደጋጋፊ ናቸው፡- ሰብዓዊ መብቶች እርስ በርስ የተደጋገፉ እና የተያያዙ በመሆናቸው በሰብዓዊ መብቶች ውስጥ ተዘርዝረው የሚገኙ ሁሉም መብቶች በአንድነት መከበር እና እውቅና ማግኘት አለባቸው፡፡
ምክንያቱም ለአንዱ መብት መሟላት የሌላኛው መብት መከበር ወይም መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
መሠረታዊነት የሰብዓዊ መብቶች መሠረታዊ በመሆናቸው የእነዚህ መብቶች አለመከበር የሰው ልጆች ክብርና ሕይዎት ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ተራ ፍላጎቶችና ምኞቶች ሳይሆኑ የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በክብር ይኖር ዘንድ ወሳኝ ናቸው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


