የጋላፓጐስ ደሴቶች ብሔራዊ ፓርክ ከመሆናቸው በፊት በ1 ሺህ 832 “አርቺፓላጐ ደ ኢኳዶር” ወይም የኢኳዶር የደሴቶች ስብስብ ተብለው ይታወቁ ነበር፡፡ በ1959 ግን ስብስቡ የኢኳዶር የመጀመሪያው ብሔራዊ ፓርክ ሆኖ ተመስርቷል፡፡
ፓርኩ ከኢኳዶር 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በዓለም አቀፉ የአካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት በ1979 ነው የተመዘገበው፡፡
ፓርኩ 19 ደሴቶችን አቅፏል፤ ቀጣናው አምስት የተለያዩ የዓየር ሞገዶች የሚገናኙበት በመሆኑ ለተለያዩ እንስሳት እና እፅዋት መገኛነት የተመቸ ሆኗል፡፡ ደሴቶቹ ጠቅላላ ስፋታቸው 7 ሺህ 995 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የተለካ ሲሆን 45 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዌር በተንጣለለው ውቅያኖስ ላይ ተሰራጭተው ነው የሚገኙት፡፡
ከደሴቶቹ መልካምድራዊ አቀማመጥ በከፍታው ቀዳሚው 1 ሺህ 707 ሜትር የተለካው በኢዛቤላ ደሴት የሚገኘው ቮልካን ዎልፍ ተራራ ነው፡፡ ከ19ኙ ደሴቶች ኗሪዎች የሚበዙባቸው ኢዛቤላ፣ ባልትራ፣ ሳንክሪስቶቦል እና ሳንታክሩዝ ሦስት በመቶ የቆዳ ሽፋን ይዘዋል፡፡
በፓርኩ ከእንስሳት ግዙፍ ኤሊዎች፣ ኢጉዋና ከዓእዋፍ አልባትሮስ ጭልፊት፣ ፒንጉዊን፣ ዓሳ ነባሪ እና የባህር አንበሳ መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ከእፅዋት 600 ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን አብዛኛዎቹ ብርቅዬ ናቸው፡፡ ካሥራ ሁለት ብርቅዬ አጥቢዎችም 10ሩ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡
በጋላፓጐስ ደሴቶች 42 በመቶ እፅዋት ፣79 በመቶ አጥቢ እንስሳት፣ 80 በመቶ ዓእዋፍ፣ 91 በመቶ ተሳቢ እንስሳት እና 56 በመቶ ነፍሳት ብርቅዬዎች መሆናቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
ፓርኩን በየዓመቱ 150 ሺህ ሰዎች ይጐበኙታል፡፡ ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ ከ60 እስከ 100 ሚሊ ሜትር ወይም ከሁለት እስከ አራት ኢንች ተለክቷል፡፡ፓርኩ ለቻርለስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብ ማስረጃ እና መነሻ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ለፓርኩ ሕልውና ወራሪ ዝርያዎች፣ የህዝብ ብዛት፣ ህገ ወጥ አስጋሪነት እና የአስተዳደር አካላት ቸልተኝነት በስጋትነት ተቀምጠዋል፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ ዶት ኦርግ፣ ጋላፓጐስ ዶት ኦርግ እና ቁዋሳር ኤክስ ድረ ገጽን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


