ፊታውራሪ ገበየሁ (በፈረስ ስማቸው አባ ጎራው) በኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ውስጥ በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በተቀጣጠለው የፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ውስጥ ስማቸው በወርቅ ቀለም የተጻፈ እጅግ ታዋቂ የጦር አበጋዝ ነበሩ። ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ በተጉለት እና ቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ አስታ በምትባል ታሪካዊ ስፍራ ተወለዱ። ገና በልጅነታቸው ከዐፄ ምኒልክ ጋር አብረው ያደጉ እና የቅርብ ጓደኛ የነበሩ በመሆናቸው በሁለቱ መሪዎች መካከል የነበረው ትስስር ከንጉሥ እና ከሎሌነት የዘለለ፣ ፍጹም መተማመን እና ታማኝነት የሰፈነበት ጥልቅ የወንድማማችነት ትስስር ነበር። ይህም በመሆኑ ዐፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን አንድነት ለመመለስ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በጀመሩት ታላቅ ጉዞ ውስጥ ፊታውራሪ ገበየሁን ቀኝ እጃቸው እና ዋነኛ የጦር መከታቸው አድርገው መርጠዋቸዋል።
ፊታውራሪ ገበየሁ በታሪክ መዛግብት ውስጥ በዋናነት በጦር ሜዳ ጀግንነታቸው እና በአድዋ ጦርነት በከፈሉት መስዋዕትነት ቢታወቁም በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የነበራቸው የአስተዳደር ሚና እና የፖለቲካ ተጽዕኖም እጅግ የጎላ ነበር። እርሳቸው የጦር መሪ ብቻ ሳይሆኑ የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ አካባቢዎች በብቃት ያስተዳደሩ እና በንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ትልቅ አመኔታ የነበራቸው ታማኝ የመንግሥት ምሰሶ ነበሩ።
በአስተዳደር ዘመናቸው ካከናወኗቸው ዋና ዋና ኃላፊነቶች መካከል የታሪካዊቷ የወረኢሉ (ደቡብ ወሎ) ገዥነታቸው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። በወቅቱ ወረኢሉ ለዐፄ ምኒልክ መንግሥት እጅግ ወሳኝ የነበረች፣ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት እና ወታደራዊ ዝግጅቶች የሚከናወኑባት ስትራቴጂካዊ ማእከል ነበረች። ይህንን የሀገሪቱን የጀርባ አጥንት የሆነ አካባቢ በበላይነት እንዲመሩ መመረጣቸው ፊታውራሪ ገበየሁ በአስተዳደር ስልታቸው፣ በታማኝነታቸው እና በሕግ አስከባሪነታቸው የነበራቸውን የላቀ ብቃት በግልጽ ያሳያል። በግዛታቸውም ውስጥ ሰላም እና መረጋጋትን በማስፈን፣ የፍትሕ ሥርዓትን በመዘርጋት እና ሕዝባዊ አቤቱታዎችን በመፍታት ረገድ የተከበሩ መሪ ነበሩ።
ከዚህም በተጨማሪ ፊታውራሪ ገበየሁ በዋናው መንግሥት መናገሻ ውስጥ ከዐፄ ምኒልክ የቅርብ አማካሪዎች አንዱ ነበሩ። በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ውሳኔዎች፣ በድንበር መከለል እና በውጭ ጉዳይ ግንኙነቶች ላይ በቀጥታ በመሳተፍ የመንግሥትን አቅጣጫ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። “ፊታውራሪ” የሚለው ማዕረግ በወቅቱ ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላ ጦር ኃይሉን ስምሪት፣ ስንቅ፣ ትጥቅ እና ዝግጅት የመምራት ሰፊ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊነት የነበረው በመሆኑ እርሳቸው በአሁኑ ዘመን ከመከላከያ ሚኒስትር ጋር የሚመጣጠን ሰፊ የሚኒስትርነት ሥልጣንን ደርበው የያዙ ታላቅ የሀገር መሪ ነበሩ።
ፊታውራሪ ገበየሁ በጦር ስልት ቀማሪነታቸው፣ በወታደራዊ መሪነታቸው እና ፍርሃት አልባ በሆነው ጀግንነታቸው በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት ዘንድ እጅግ የተከበሩ እና የሚፈሩ መሪ ለመሆን በቅተዋል።
የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመደፈር ወደ መሐል ሀገር ለመግባት በጀመረበት ወቅት ፊታውራሪ ገበየሁ ጠላትን ቀድሞ ለመመከት በተደረጉት ዋና ዋና ውጊያዎች ላይ ሁሉ የግንባር ቀደምነቱን ሚና ተጫውተዋል። የታላቁ የአድዋ ጦርነት ዋዜማ በነበረው እና በታሪክ የአምባላጌ ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ውጊያ ላይ ፊታውራሪ ገበየሁ ያሳዩት ወታደራዊ እርምጃ በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ በስፋት ይወሳል። እሳቸው የሚመሩት ጦር የጠላትን እንቅስቃሴ በቅርብ ይከታተል በነበረበት ወቅት ንጉሡ ሳይፈቅዱ ወይም ይፋዊ የጦር ትዕዛዝ ሳይሰጥ በጠዋት በመነሳት የጠላትን ጠንካራ ምሽግ ሰብረው በመግባት ውጊያውን ከፈቱ። ይህ ድንገተኛ እና ፈጣን እርምጃ የጣሊያንን ጦር መከላከያ ያሳጣ እና ያደናገጠ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰራዊትም በታላቅ የሞራል መነቃቃት ጠላትን ድባቅ እንዲመታ መንገድ ከፍቷል። ይህንን አስደናቂ ወታደራዊ ድል አስመልክቶም በወቅቱ የነበሩ ሰዎች
“ያ ጎራው ገበየሁ አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፣ ለምሳም ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው፡፡”
የሚል ታዋቂ የጀግንነት ግጥም በማውጣት ጀግንነታቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር አድርገዋል።
ከአምባላጌ ድል በመቀጠል የተደረገው የመቀሌው ውጊያ ሌላው የፊታውራሪ ገበየሁ ስልታዊ የጦር መሪነት የተመሰከረበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነበር። በወቅቱ የጣሊያን ጦር በመቀሌ እንዳየሱስ ላይ በተጠናከረ ምሽግ ተደራጅቶ ነበረ፤ ምሽጉን በቀጥታ ፊት ለፊት መግጠም ከፍተኛ የሰው ህይወት ሊያስቀጥፍ እንደሚችል ፊታውራሪ ገበየሁ ተረድተው ነበር። በዚህም ምክንያት ጠላትን በሀይል ከመግጠም ይልቅ የጣሊያንን ምሽግ በመክበብ ወደ ምሽጉ የሚገባውን ዋነኛ የውኃ ምንጭ የመቁረጥን ስልታዊ እቅድ በእቴጌ ጠሐይቱ ሀሳብ አመንጪነት አወጡ። ይህ የውኃ ምንጭ የመቁረጥ ወታደራዊ ስልት እጅግ ስኬታማ ነበረ፤ የጣሊያን ጦር በውኃ ጥም ምክንያት ክፉኛ እንዲዳከም እና በመጨረሻም እጁን እንዲሰጥ ለማድረግ አስገዳጅ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህ እርምጃ የኢትዮጵያን ሰራዊት ህይወት ሳይቀጥፍ ትልቅ ድል ያስገኘ በመሆኑ የእሳቸውን የላቀ የጦር መሪነት ጥበብ በግልጽ ያሳየ ነበር።
የካቲት 23 ቀን 1896 ዓ.ም በተደረገው የታላቁ እና ታሪካዊው የአድዋ ጦርነት ላይ ፊታውራሪ ገበየሁ የመሐል ጦሩን በበላይነት እየመሩ ወደ ጦር ሜዳ ዘመቱ። ውጊያው እጅግ በበረታበትና በሁለቱም በኩል ከፍተኛ ፍልሚያ በሚደረግበት ወቅት እሳቸው ከፊት በመሆን ሰራዊታቸውን እያበረታቱ እና እየመሩ በጀግንነት ሲዋጉ በጦር ሜዳ ላይ በክብር ተሰውተዋል። ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ ጦርነቱ ሳይገቡ በፊት “ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፤ ከፊት ለፊቴ ስፋለም ከወደቅሁ ግን አስክሬኔን ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ” የሚል ጽኑ ቃል ኪዳን ነበራቸው።
በዚያ ታሪካዊ ዕለት የጄነራል አልቤርቶኒ የሚመራው የጣሊያን ጦር ብርጌድ ይዞት የነበረውን ስትራቴጂካዊ ምሽግ ለመስበር የፊታውራሪ ገበየሁ ጦር የመጀመሪያውን እና እጅግ አስቸጋሪውን ጥቃት ሰንዝሯል። የጠላት ጦር በዘመናዊ መሣሪያዎች፣ በመድፍ እና በአውቶማቲክ መትረየስ ጥይቶች የታገዘ ኃይለኛ እሳት ቢያዘንብም አባ ጎራው ግን ቅንጣት ታህል ፍርሃት ሳይበግራቸው ሰይፋቸውን መዝዘው እና ፈረሳቸውን እየጋለቡ ጦራቸውን ወደፊት መሩት።
የጦርነቱ ፍልሚያ እጅግ በጠነከረበት እና የሞት ጥላ ባጠላበት በዚያ የመጨረሻ ሰዓት ፊታውራሪ ገበየሁ ወደ ጠላት ምሽግ በቆራጥነት በመግባት የጣሊያንን የመከላከል መስመር ሙሉ በሙሉ አበራዩት። ነገር ግን፣ ይህንን ታላቅ የጀግንነት ተጋድሎ በሚያደርጉበት እና ጠላትን እያባረሩ በደመሰሱበት በዚያው የመጀመሪያው የጦርነት ምዕራፍ ላይ በጠላት ጥይት ተመትተው በክብር ወደቁ።
የፊታውራሪ ገበየሁ ሰማዕትነት በኢትዮጵያ ጦር ዘንድ ፍርሃትን ሳይሆን የፈጠረው ከፍተኛ ቁጭትን እና የበቀል እሳትን ነበር። የእርሳቸውን መውደቅ ያዩት የጦሩ አባላት በወንድማቸው እና በመሪያቸው ሞት ተቆጭተው የጣሊያንን ምሽግ በበለጠ ኃይል እና ወታደራዊ ስልት ጥሰው በመግባት የጠላትን ጦር ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ በቁ። የአባ ጎራው መስዋዕትነት ለአድዋ ድል መገኘት ትልቁን መሠረት ጥሏል።
ይህንን የጀግና መውደቅ የሰሙት ዐፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከፍተኛ ሐዘን እንደገጠማቸው እና ንጉሠ ነገሥቱ “ክንፌ ተሰበረ” በማለት የላቀ ጀግንነታቸውን እና ታማኝነታቸውን እንደመሰከሩላቸው በታሪክ መዛግብት ሰፍሮ ይገኛል።
ለሀገራቸው እና ለክብራቸው ሲሉ የከፈሉት ይህ ታላቅ መስዋዕትነትም የታሪካቸው ማሳረጊያ ሆነ። ጦርነቱ በኢትዮጵያ ታላቅ ድል ከተጠናቀቀ በኋላ በጃንሜዳ በተደረገው የሰራዊት ትዕይንት ላይ የእሳቸው ፈረስ ያለ ሰው በባዶው ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት ዐፄ ምኒልክ የቅርብ ጓደኛቸውን እና ታማኝ የጦር መሪያቸውን በማጣት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን መግታት አቅቷቸው በሰራዊቱ ፊት በታላቅ ድምፅ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱ በታሪክ ይነገራል። የጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ አፅምም በገቡት ቃል ኪዳን መሰረት በትውልድ ቦታቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በክብር ሊያርፍ ችሏል።
ምንጭ፡- ‘‘ዳግማዊ አፄ ምኒልክ’’-አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ ‘‘ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ’’ -ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ (ጸሐፌ ትእዛዝ) እና ‘‘የአድዋ ጦርነት’’ – ጳውሎስ ኞኞ
ሳምንቱ በታሪክ
የአንድነት ዘመቻው
ዐፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ (ካሳ ኃይሉ) በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተበታተነችውን ኢትዮጵያን በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር ለመሰብሰብ የተነሱ ታላቅ መሪ ነበሩ። እቅዳቸውን ከግብ ለማድረስ ደግሞ የክረምቱን ወራት ወታደራዊ ዝግጅት በማድረግ እና ስትራቴጂ በመንደፍ ካሳልፉ በኋላ የክረምቱ ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ጋብ ሲል ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ዘመቻቸውን የጀመሩት ነሐሴ 20 ቀን 1845 ዓ.ም ነበር። የዘመነ መሳፍንትን ሥርዓት ለማክተም በጎንደር እና በወሎ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩትን ያፈነገጡ መሳፍንት ለመግታት ንጉሡ ጦራቸውን በስፋት ያደራጁበት እና አዳዲስ ወታደራዊ አዋጆችን ለሠራዊታቸው ያወጁበት ይህ ታሪካዊ ክስተት ዐፄ ቴዎድሮስ በጥር 11 ቀን 1847 ዓ.ም በደረስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን ዘውድ እንዲደፉ እና ሀገሪቱን የማዋሃድ ራዕያቸውን እንዲጀምሩ ትልቅ መሠረት ጥሏል።
ንጉሡ ሀገርን በአንድነት ለመምራት የነበራቸውን ራዕይ በጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የራሷን የጦር መሣሪያ እንድታመርት በማድረግ ጭምር ለማረጋገጥ በመጣራቸው ጋፋት በተባለ ስፍራ ላይ ከአውሮፓውያን የእጅ ጥበበኞች ጋር በመሆን ‘‘ሴባስቶፖል’’ የተባለውን ታሪካዊ እና ታላቅ መድፍ ማሠራታቸው የዚሁ የጽናት ጉዞ አካል ነበር። ነገር ግን ይህ የአንድነት እና የዘመናዊነት ጉዞ በመጨረሻ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተገባው የዲፕሎማሲ መሻከር ምክንያት መቅደላ ምሽግ ላይ ፈታኝ መስቀለኛ መንገድ ገጥሞታል፡፡ በታሪካዊው የመቅደላ ጦርነት ወቅት የእንግሊዝ ጦር ምሽጉን በሰበረበት በመጨረሻው ሰዓት ዐፄ ቴዎድሮስ ‘‘ለነጭ አልማረክም’’ በማለት በገዛ ሽጉጣቸው ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ክብር አሳልፈው ሰጥተዋል። በመሆኑም በቆራጥነት የተጀመረውና የተጠናከረው ያ የቆራጥነት ወታደራዊ ስምሪት በመቅደላ ምሽግ ላይ በታላቅ የሀገር ፍቅር ሰማዕትነት ተደምድሟል ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‘‘የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ (1847-1983)’’ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


