በአማራ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰተው የሰላም እጦት ክፉኛ ከጎዳቸው መካከል ትምህርት ቀዳሚው ነው። ግጭቱ ትምህርት ቤቶችን ከመዝጋትና መሠረተ ልማቶችን ከማውደም ባለፈ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ከትምህርት ገበታቸው አርቋል። ይህም የአንድ የትምህርት ዘመን መቋረጥ ብቻ ሳይሆን በልጆች የወደፊት ሕይወትና በክልሉ የሰው ኃይል ልማት ላይ የሚያስከትለው ዘላቂ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው።
ይህንን አስመልክቶ በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሥተባባሪነት 23ኛው የአማራ ትምህርት ክልላዊ ልማት ትብብር ፎረም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ አጋር አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊዎች፣ ረጅ ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
እኛም በውይይቱ ከተገኙት ውስጥ ለአብነት የደቡብ ጎንደር እና የምሥራቅ ጎጃም ትምህርት መምሪያዎችን አነጋግረናል፡፡
በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት ከባድ ጉዳት ካስተናገዱ አካባቢዎች መካከል ደቡብ ጎንደር እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ይጠቀሳሉ። የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ አሥራቴ በግጭቱ ምክንያት የደረሰው የትምህርት ስብራት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከባለፈው 2016 /2017 በጀት ዓመት ጋር የትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ሁኔታ በአንጻራዊነት ሲታይ መሻሻል እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህ ደግሞ በተገባደደው የትምህርት ዘመን (2018 ዓ.ም) በዞኑ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዳናወኑ አብነት አንስተዋል፡፡
ሆኖም በትምህርት ገበታ መገኘት ያለባቸው ሁሉም ተማሪዎች መምጣት አልቻሉም፤ የተወሰኑት ደግሞ ትምህርት ከጀመሩ በኋላ አቋርጠዋል፡፡
አኳያ ሲታይ 59 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ብቻ ነው ወደ ትምህርት ቤት ወደ ትምህርት ቤት ከመጡት ተማሪዎች ውስጥ ደግሞ 20 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች አቋርጠዋል፡፡
በዚህም በትምህርት ዘመኑ ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ ነው አቶ ደስታ የተናገሩት፡፡
“ይህም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ብክነት ነው” ያሉት አቶ ደስታ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማደስ፣ የተማሪዎችን ትምህርት ለማስቀጠልና ከትምህርት ውጭ የሆኑትን ለመመለስ የሁሉም የቤት ሥራ ሆኖ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መምሪያ ኃላፊው እንደተናገሩት የቤት ሥራውን ለማሳካት በመንግሥት ብቻ የሚስተካል ባለመሆኑ የረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እና እገዛ ሊኖር ይገባል፡፡ ድርጅቶቹ ሲያደርጉት የነበረው ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል ይባዋል፡፡
መምሪያ ኃላፊው አክለውም “ለ2019 የትምህርት ዘመን 835 ሺህ 454 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ በመያዝ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ይህም የትምህርት መልሶ የማስጀመር ጥረቱን የሚያሳይ ጅማሮ መሆኑን ያሳያል” ነው ያሉት፡፡ ለስኬቱ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻዎች እንዲረባቡ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የትምህርት ስብራቱ በምሥራቅ ጎጃም ዞንም ከባድ ነው። “በ2018 የትምህርት ዘመን ከዘጠኝ መቶ 96 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባት መቶ 45 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው እና ከ627 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸው የችግሩን ስፋት ያሳያል” ያሉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ ናቸው።
ኃላፊው እንዳሉት ከትምህርት መራቅ በራሱ ከባድ ጉዳት ሲሆን፣ ሕፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለስደትና ለሌሎች ማሕበራዊ ችግሮች ተጋላጭ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ትምህርትን ማስቀጠል ማለት ትምህርት ቤትን ብቻ መክፈት ሳይሆን የሕፃናትን ደኅንነትና የወደፊት ዕድልን መጠበቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ትምህርትን በአደጋ ጊዜ ለማስቀጠል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶ ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች የሚበረታታ ነው” ብለዋል፡፡
አቶ ጌታሁን እንደተናገሩት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የትምህርት ቤት ግብዓት እንዲሟላ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማሕረሰቡን በማንቃት፣ መምህንን ከስነ ልቦና ጠባሳ እንዲላቀቁ የስነ ልቦና ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት እና የተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር ረጂ ድርጅቶች መልካም ተግባራትን እያከናወኑ ነው፡፡ በቀጣይም ችግሩን ሊመጥን የሚችል ሥራ አጠናክረው እንዲሠሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መኳንንት አደመ ባለፉት ዓመታት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ስኬቶችን እና ጉድለቶችን አንስተዋል። አቶ መኳንንት እንዳሉት በ2018 የትምህርት ዘመን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ሳይመዘገቡ ቀርተዋል፤ ከአንድ ሺህ 400 በላይ ትምህርት ቤቶችም በጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባ ማካሄድ አልቻሉም። ሦስት ሺህ 449 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከችግሩ ግዝፈት አኳያም የመልሶ ግንባታው፣ ፋይናንስ እና የሰው ኃይል ፍላጎት ከመንግሥት አቅም በላይ ነው፤
በሆኑም “የአጋር ድርጅቶች ሚና ከድንገተኛ ድጋፍ ባለፈ ሊታይ ይገባል” ነው ያሉ።
ትምህርት ቤት መገንባት፣ የትምህርት ግብዓት ማቅረብና የተማሪዎችን የስነ ልቦና ድጋፍ ማጠናከር አስፈላጊ ናቸው፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ደግሞ በሦስት ቁልፍ አቅጣጫዎች መሥራት እንደሚገባ ነው ያነሱት። የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን በፍጥነት መልሶ ማቋቋም፣ ከትምህርት ውጭ የሆኑ ሕፃናትን ለመመለስ የተለየ የመመለሻና የመያዣ ሥርዓት መፍጠር እና መምህራንና ተማሪዎች ግጭቱ ያስከተለባቸውን የስነ ልቦና ጫና እንዲያልፉ የስነ ልቦና እና የማሕበራዊ ድጋፍ ማድረግ ናቸው።
በሂደቱም የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ የአካባቢ አስተዳደሮችና የማሕበረሰብ መሪዎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ በትምህርት ዘርፉ የሚቴየው ችግር ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ ብቻ የሚፈታ አይደለም፤ በትምህርት ቤት ቆይቶ እንዲማር፣ እንዲያድግና እንዲጠበቅ ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው በ2019 የትምህርት ዘመን ከሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለማደስም በትኩረት ይሠራል።
ይሁንና ቁጥሩ ትልቅ ስለሆነ ብቻ ስኬት አለመሆኑን በመገንዘብ በጀቱ፣ መሠረተ ልማቱ፣ መምህሩ፣ የተማሪው ደኅንነትና የመማር ጥራት በአንድነት መታሰብ እንዳለባቸው አቶ መኳንንት ተናግረዋል።
“የትምህርት ቀውሱ የትውልድ ጉዳይ ነው” ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው አጋር ድርጅቶች ድጋፋቸውን በተቀናጀ ዕቅድ ማጠናከር፣ ማሕበረሰቡ ትምህርት ቤቶችን በባለቤትነት መንከባከብ እና መንግሥት ደግሞ የሚያስፈልገውን መሪነትና ቅንጅት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
“ከሁሉም በላይ ግን ትምህርት ቤቶች ከግጭት ነፃ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፤ ትምህርት ቤቶች የግጭት መዳረሻ እንዳይሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል”ም ብለዋል፡፡
አቶ መኳንንት እንዳሉት ያለፉት ሦስት ዓመታት ያስከተሉትን የትምህርት ኪሳራ በአንድ ዓመት ሙሉ በሙሉ ማካካስ አይቻል ይሆናል። ነገር ግን የተማሪዎችን መመለስ፣ ትምህርት ቤቶችን መክፈትና መልሶ መገንባት፣ መምህራንን ማበረታታት እና የመማር ጥራትን ማሻሻል በጋራ ከተሠራ የጠፋውን ተስፋ መመለስ ያስችላል።
ረጂ ድርጅቶች በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን በማንሳት በክልሉ ትምህርት ቢሮ ስም ምስጋና አቅርበዋል፤ በቀጣይ በማንኛውም ለመማር ማስተማሩ ሂደት አስፈላጊ በሆኑ ድጋፎች የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የበኩላቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፋዋል።
ግእዝ በአማርኛ
ምን ፈለግህ – ምንት ተኀሥሥ
መቸ አወራኸኝ – ማእዜ ዜነውከኒ
ዋጋው ስንት ነው – ስፍን ውእቱ ሤጡ
ነገ ከመምህሬ ጋር እንገናኛለን – ጌሰም ንትራከብ ምስለ መምህርየ
(ሰናይት በየነ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


