በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነዎት እንበል። አወያዩ አንድ ውስብስብ እና አዲስ ርዕሰ ጉዳይ አንስቶ አስተያየት እንዲሰጡ ጠየቀዎት።
በዙሪያዎ ያሉ ሰዎች ሁሉ አፍጥጠው ይመለከቱዎታል። ልብዎ ይመታል፤ ውስጣዊ ጭንቀት ይወርዎታል። በዚህ ቅጽበት በውስጥዎ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚጮኸው የማን ድምፅ ነው? የኢጎ (እኔ የሚል) ድምፅ!
ኢጎ በጆሮዎ ሹክ ይላል። “አላውቅም ካልህ እንደ ደካማ እና ሞኝ ትቆጠራለህ፤ ፈጥነህ አሳማኝ የሚመስሉ ቃላትን ደርድረህ ሁሉን አዋቂ መስለህ ታይ!” ይላል።
ኢጎ ማለት እኔ ከሁሉ እበልጣለሁ ወይም ሁልጊዜ እኔ ብቻ ነኝ ትክክል የሚል የተጋነነ የራስ ወዳድነትና የኩራት ስሜት ነው። ለምሳሌ በክርክር ወቅት ስህተታችን በግልጽ እየታየ “እንዴት በእኔ ላይ ይፈረዳል? እንዴት እኔ እሸነፋለሁ?” በሚል እልህ ይቅርታ አለመጠየቅ የኢጎ ውጤት ነው። ባጭሩ ኢጎ ማለት ራሳችንን ከሌሎች አስበልጠን እንድናይና እውነታን እንዳንቀበል የሚጋርደን የውስጥ መጋረጃ ነው።
ይህ በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ በየዕለቱ የሚካሄድ ፍልሚያ ነው። ኢጓችን ሁልጊዜ ትክክለኛ፣ ሁሉን አዋቂ እና እንከን-አልባ መስሎ ለመታየት ይተጋል። ነገር ግን እውነታው ፍጹም ተቃራኒ ነው። “አላውቅም” ማለት የድንቁርና መገለጫ ሳይሆን ኢጎን ሰብሮ ወደ እውነተኛ ጥበብ፣ እውቀት እና ነጻነት የመሸጋገሪያ ብቸኛው ድልድይ ነው።
ራያን ሆሊደይ “ኢጎ ኢዝ ዘ ኢነሚ’ (ኢጎ ጠላትህ ነው) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል “ኢጎ የመማር ትልቁ ጠላት ነው፤ ምክንያቱም ገና ሳያውቅ እንደሚያውቅ፣ ገና ሳይደርስ እንደደረሰ አድርጎ ራሱን ያታልላል” ብሏል።
ኢጎ ሁልጊዜ የሚያስበው ስለ ክብር እና ስም ነው። “አላውቅም” የሚለውን ቃል ሲሰማ እንደ ትልቅ ውርደት እና ስጋት ይቆጥረዋል። ምክንያቱም ኢጎ ዋጋውን የሚያገኘው ከእውነተኛው ውስጣዊ ማንነቱ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች ከንቱ አድናቆት ነው።
በተቃራኒው አዳም ግራንት “ቲንክ ኤጌን” በተሰኘው መጽሐፉ እንደሚያስረዳው የእውቀት አድማሳቸውን የሚያሰፉ ሰዎች እንደ ሳይንቲስት የሚያስቡ ናቸው። ሳይንቲስቶች የራሳቸውን ድንቁርና ለመቀበል አይፈሩም፤ እንዲያውም የማያውቁትን ነገር ሲያገኙ እንደ አዲስ የመመርመሪያ እድል ይቆጥሩታል። ኢጎ ግን ራሱን እንደ “ሰባኪ” ወይም “ጠበቃ” አድርጎ በመቁጠር ምንም ያልተረዳውን ሃሳብ እንኳን ትክክል እንደሆነ ለማስረዳት በከንቱ ይሟገታል።
ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስ “እኔ ከሌሎች የተሻልኩ አዋቂ የምሆነው በአንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም ምንም እንደማላውቅ በማወቄ ነው” ሲል የገለጸው ይኸው ከኢጎ የጸዳውን አእምሯዊ ትህትና ነው።
በ1999 እ.አ.አ በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች የሆኑት ዴቪድ ዳኒንግ እና ጀስቲን ክሩገር “የዳኒንግ-ክሩገር ተፅዕኖ” የተባለውን ጥናት ይፋ አደረጉ። ጥናቱ የሚያስደንቅ እውነታ አሳይቷል፡
በየትኛውም መስክ ዝቅተኛ እውቀት ያላቸው ሰዎች በከፍተኛ የኢጎ እብጠት ተውጠው ራሳቸውን እንደ “ሁሉን አዋቂ” ይገምታሉ። በተቃራኒው ደግሞ ጥልቅ እውቀት ያላቸው እውነተኛ ምሁራን፣ የነገሮችን ውስብስብነት እና የራሳቸውን እውቀት ውስንነት ስለሚረዱ ኢጓቸውን ዝቅ አድርገው “ብዙ የማላውቀው ነገር አለ” ብለው ያምናሉ።
ማለትም “ሁሉንም አውቃለሁ” ባይነት ያልበሰለ ኢጎ የሚያደርገው መከላከያ ሲሆን፤ “አላውቅም” ብሎ በድፍረት መናገር ግን ኢጎውን የተቆጣጠረ የበሰለ አእምሮ መገለጫ ነው።
በሞባይል ኢንደስትሪው ዓለምን በበላይነት ይመራ የነበረው ኖኪያ ለውድቀት የተዳረገው በቴክኖሎጂ እጥረት ብቻ አልነበረም፤ በዋነኝነት በከፍተኛ አመራሮቹ የኢጎ አባዜ ነበር።
በስማርት ስልክ ዓለም ውስጥ የ”ተች ስክሪን” እና የ”አንድሮይድ” አብዮት ሲመጣ የኖኪያ አመራሮች አዲሱን የገበያ ሁኔታ “አልተረዳነውም/አናውቀውም” ብለው አምነው ከመቀበል ይልቅ “እኛ የምንሰራው ብቻ ነው ትክክል” በሚል ትምክህት በመጓዛቸው ግዙፉ ኩባንያ ከገበያ ውጪ ለመሆን ተገደደ። “አላውቅም” ብሎ ኢጎን ማሸነፍ የሚያስገኛቸው አራት ታላላቅ ጥቅሞች አሉ።
ከይስሙላ ማንነት እና ከጭንቀት ነፃ ያወጣል፦
ሁሉን አዋቂ መስሎ ለመታየት መሞከር ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጫና ይፈጥራል። “ውሸቴ እንዳይጋለጥ”፣ “አላዋቂነቴ እንዳይታወቅ” በሚል ስጋት ውስጥ መኖር ለአእምሮ ድካም እና ለጭንቀት ይዳርጋል። ይህን አላውቀውም ብሎ በድፍረት መናገር ኢጎ የተሸከመውን ከባድ የይስሙላ ጭንብል በአንዴ አውልቆ ጥሎ እውነተኛ የአእምሮ ሰላም ይሰጣል።
የማያወላውል ተአማኒነትን ይገነባል ፦
ሰዎች ሁሉን አዋቂ ነኝ የሚልን በኢጎ የተወጠረ ሰው በጥርጣሬ ይመለከታሉ። በተቃራኒው የማያውቀውን ነገር በቅንነት “ይህ ጉዳይ አይገባኝም፣ ግን አጣርቼ እነግርሃለሁ” የሚልን ግለሰብ ከልባቸው ያምኑታል። አላውቅም ማለት ከኢጎ የጸዳ ታማኝ ሰው መሆንዎን ያስመሰክራል፤ ይህም በንግግርዎ ላይ እውነተኛ ክብደት እና ተቀባይነት ይጨምራል።
የመማር እና የማደግ በር ይከፍታል፦
ታዋቂዋ የስነ-ልቦና ተመራማሪ ካሮል ድዌክ “ማይንድሴት” በተሰኘው መጽሐፏ እንደምትገልጸው ኢጎ ሁልጊዜ ከ”የተገደበ አስተሳሰብ” (ፊክስድ ማይንድሴት) ጋር የተቆራኘ ነው። አውቃለሁ ብለው ኢጎዎን ያረኩበት ቅጽበት የመማር ሂደቱ ያከትማል። ኢጎን አሸንፈው አላውቅም ሲሉ ግን ለአእምሮዎ አዲስ መረጃ የመቀበያ በር ይከፍታሉ፤ ለመመርመር እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማደግ እድል ያገኛሉ።
ጥራት ያለው ውሳኔ እንዲወሰን ያደርጋል ፦
በህይወትም ሆነ በስራ ቦታ ትልልቅ ውድቀቶች የሚመጡት ባለማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅ ላይ በቆመ የኢጎ ድፍረት ነው። የማናውቀውን ነገር አምነን መቀበላችን ሌሎች የተሻለ ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች እንድንጠይቅ፣ ጥናት እንድናደርግ እና ከአውዳሚ ስህተቶች እንድንጠበቅ ያደርገናል።
ኢጎን አሸንፎ “አላውቅም”ን በብልሃት እንዴት መጠቀም ይቻላል?
“አላውቅም” ማለት ራስን ዝቅ አድርጎ የመተው ሳይሆን አለማወቅን ወደ ጥበብ የመቀየር ጥበብ ነው። ይህንን ቃል በሙያዊ እና በግል ህይወታችን ውስጥ እንዲህ ልንገልጸው እንችላለን፡
“ይህ በጣም ድንቅ ጥያቄ ነው፤ አሁን በእጄ ላይ በቂ መረጃ ስለሌለ አላውቀውም፤ ነገር ግን ጉዳዩን በጥልቀት አጣርቼ ምላሹን አካፍልሃለሁ” ማለት እንችላለን። ወይም “በዚህ ዘርፍ ላይ ያለኝ ግንዛቤ ውሱን ነው፤ የኢጎዬ ምርኮኛ ሆኜ ከመገመት ይልቅ አንተ የተሻለ ልምድ ስላለህ ብታስረዳኝ ደስ ይለኛል” የሚሉ አነጋገሮችን መጠቀም እንችላልን።
እውነተኛ ብልህነት ሁሉንም ነገር ማወቅ ሳይሆን የማያውቁትን ነገር በግልጽ አምኖ ለመቀበል የሚያስችል የኢጎ ነፃነት ማግኘት ነው። በሚቀጥለው ጊዜ የማያውቁት ነገር ሲያጋጥምዎት ኢጎዎ እንዲሸፍነው አይፍቀዱለት።
ፈገግ ይበሉ፤ ኢጎዎን ይግደሉ፤ በሙሉ በራስ መተማመን “አላውቅም!” ይበሉ። ያኔ ወደ እውነተኛው ጥበብ እና ተአማኒነት የመጀመሪያውን ታላቅ እርምጃ ይጓዛሉ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


