የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት”አፈሩን የሚያጠፋ ሀገር ራሱን ያጠፋል፤ ደኖች የፕላኔታችን ሳንባዎች ናቸው” ሲሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ወሳኝነት ገልጸው ነበር። የደኖች መመንጠር እና የአፈር መሸርሸር ለሀገር ህልውና ቀጥተኛ ስጋት መሆናቸውን ያሳስባል።
በተመሳሳይ ታዋቂው የሕንድ መሪ ማህትማ ጋንዲ”ምድር የሁሉንም ሰው ፍላጎት ለማሟላት በቂ ሀብት አላት፤ የሁሉንም ሰው ስግብግብነት ግን ማሟላት አትችልም” በማለት የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ የመጠቀምን አስፈላጊነት ማስገንዘባቸውን ታሪክ ይዘክረዋል።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት እንዳስታወቀው ሰብዓዊ ፍላጎት ተፈጥሮ ከምትችለው በላይ እየጨመረ ይገኛል፤ የአየር ንብረት መዛባት ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። አረንጓዴ ልማት ደግሞ ዋነኛው አማራጭ ሆኗል።
በተመሳሳይ በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የአረንጓዴ ልማት እሳቤ ተፈጥሮን ከመታደግ የተሻገረ፣ የሕይወታዊ ፍጡራን ሁሉ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ነው የሚያስገነዝበው።
ድርጅቱ ይህንን መነሻ በማድረግ የዓለም ሀገራትን ተሞክሮ በማጋራት እንዲተገብሩት ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል። በአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ ከሚወሰድባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ደቡብ ኮሪያ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። ለዚህ አብነት የሚነሳው ደግሞ እ.አ.አ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የነበረውን አጠቃላይ የደን መጨፍጨፍ ለመግታት ባካሄደችው ብሔራዊ ንቅናቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ በደን መሸፈን መቻሏ ነው። የሀገሪቱ አሁናዊ የደን ሽፋንም 64 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል፡፡
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በተጠቀሱት ዓመታት የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ35 በመቶ በታች ነበር፤ ዜጎች ሐሳቡን በሙሉ ፍላጎት በመቀበል በአንድነት መተግበራቸው ደግሞ በአጭር ጊዜ ስኬታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ባለው ብዝኃ ሕይወት ብዛት እና የዓለምን የአየር ንብረት በመጠበቅ ባለው አስተዋጽኦ የዓለም ሳንባ እየተባለ ይጠራል – አማዞን። በአማዞን ደን ጥበቃ እና በዘላቂ የእርሻ-ደን (Agroforestry) ሥርዓት የካርቦን ልቀትን በመቀነስ እና ብዝኃ – ሕይወትን በመጠበቅ ባለውለታዋ እና የቀደምት ተሞክሮ ባለቤት ደግሞ ብራዚል ናት። የአካባቢ ጥበቃ ተቋሙ እንዳመላከተው ብራዚል በጠንካራ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ በአማዞን ደን እና በዙሪያው የምታደርገው ጥበቃ ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል።
የበረሃማነት መስፋፋትን ለመግታት “ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ” (Great Green Wall) የሚባለውን ፕሮጀክት በማቋቋም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን በመትከል የአፈር መሸርሸርን በመታደግ በአረንጓዴ ልማት አሻራዋ አብነት የምትጠቀሰው ደግሞ ቻይና ናት።
ሀገራችንም ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል፤ የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፉት ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ መጥቷል። የሀገራችን የደን ሽፋንም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል (የዘንድሮውን መርሃ ግብር የጽድቀት ምጣኔ ሳይጨምር ከ23 በመቶ በላይ መድረሱን ልብ ይሏል)።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ጉዞ
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እና የአፈር መሸርሸር ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ስጋት በሆኑበት በዚህ ዘመን፣ አረንጓዴ ልማት የህልውና እና የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሣርያ ሆኗል። ሀገራችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ተሞክሮዎችን ከመተግበር ባለፈ የራሷን ነባር ዕውቀቶች እና ሀገራዊ ፖሊሲዎች በማቀናጀት ቀደምት የአረንጓዴ ልማት ባለቤት ለመሆን ችላለች።
ታሪካዊ አመጣጥ እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ክስተት አይደለም። የተፈጥሮ ሀብትን የመንከባከብ ባሕላችን ለዘመናት የቆዬ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በቀዳሚነት የምትጠቀስ አብነት ናት። ለአሁኑ የአረንጓዴ ልማት መሠረት የጣለች ስለመሆኗም ነው የሚነገረው።
በአጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ተግባራዊ የተደረገው የደን ጥበቃ እንዲሁም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን የነበሩ የደን ልማት ድንጋጌዎች ደግሞ የዘመናዊ ጥበቃ ጅምር ማሳያዎች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ ደርግ በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎችን ለማገገም የጀመራቸው የምግብ ዋስትና እና የታፋሰስ ልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ደን ልማት ፈር ቀዳጅ ናቸው። ይሁን እንጂ ሥራዎቹ ተቋማዊ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ መመራት የጀመሩት ከቅርብ ዓመታት በኋላ ነው። ኢትዮጵያ ይፋ ያደረገችው የካርበን ልቀትን በመቀነስ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት መተግበር የጀመረችው የማይበገር የአረንጓዴ ልማት (ኢኮኖሚ) ስትራቴጂ አንዱ ማሳያ ሀገራዊ ዕቅድ ነው።
በተመሳሳይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል፣ ደኖችን በመልካም ሁኔታ በመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅምን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል።
የአማራ ክልል ተሞክሮ
የአማራ ክልል ከፍተኛ የመሬት መሸርሸር፣ የደን መጨፍጨፍ እና ከፍተኛ የአፈር ለምነት መቀነስ የገጠመው ክልል እንደነበር የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል። በመሆኑም የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለክልሉ ግብርና የህልውና ያህል ወሳኝ ናቸው። በተከናወኑት ተግባራትም እጅግ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ገቢ ተኮር ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉን ያስታወቀው ቢሮው ይህም የአየር ንብረት መዛባትን ለመጠበቅ ከማስቻሉ በተጨማሪ የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መሠረት መሆኑን ጠቁሟል።
እንደ ቢሮው መረጃ በተለይ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተከናወኑ የእርከን ሥራዎች እና የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች የተጎዱ በርካታ መሬቶችን እንዲያገግሙ አስችለዋል።
በአጠቃላይ አረንጓዴ ልማት የምድር እስትንፋስ፣ የመኖርም ዋስትና መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ተቋም አስገንዝቧል፡፡ ከዓለም ሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር ጋር ተያይዞም የታዳሽ ኃይል ዕድገት በዚያው ልክ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ደግሞ የዚህ ዋስትና መሆኑን ተቋሙ ጠቅሷል።
እንደ ተቋሙ መረጃ በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውስጥ ከሠላሳ በመቶ በላይ የሚሆነው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች (ከፀሐይ፣ ከነፋስ እና ከውኃ) የሚመነጭ ነው።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


