የባሕር በር አልባ ሀገር ማለት ከውቅያኖስ ወይም ከባሕር ጋር የተገናኘ ግዛት የሌላት ሀገር እንደሆነ ብሪታኒካ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ አፍሪካን ጨምሮ በእስያ፣ በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ 44 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለም ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 32ቱ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት የባሕር በር አልባ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ ተመድበዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት በአፍሪካ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ ዝቅተኛው የሰው ልጅ ልማት ደረጃ (ኢንዴክስ) ውስጥ ከሚመደቡ ዐሥራ ሁለቱ ሀገራት ዘጠኙ የባሕር በር አልባ መሆናቸውን መረጃው ያክላል። እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከዓለም አጠቃላይ ስፋት ከ11 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ሲወስዱ የዓለምን አጠቃላይ ሕዝብ ወደ ሰባት በመቶ የሚጠጋውን ይይዛሉ።
የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው የተነሳ ልዩ የልማት ፍላጎቶችና ከባድ ተግዳሮቶች አሉባቸው፡፡ ለአብነትም ወደ ባሕር ለመድረስ የጎረቤት ሀገራትን መሠረተ ልማት ለመጠቀም ስለሚገደዱ የትራንስፖርት ወጫቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የወጪና ገቢ ንግዳቸው ስኬት በጎረቤት ሀገራት የፖለቲካ መረጋጋት፣ የየብስ መሠረተ ልማት ጥራትና የጉምሩክ ቀልጣፋነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
በከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ ምክንያት ምርቶቻቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸው የዋጋ ተወዳዳሪነት ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ የባቡር እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት የንግድ ትስስሩን ያዘገይባቸዋል፡፡
ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር ንግድ አለመኖር ብቻ ሳይሆን እንደ ዓሳ ልማት ያሉ ጠቃሚ ሀብቶችንም ያጣሉ፤ ይህ ዘርፍ የባሕር በር ላላቸው በርካታ ሀገራት የኢኮኖሚያቸው የጀርባ አጥንት ነው፡፡
እነዚህ ሀገራት ልዩ የልማት ፍላጎቶች ያሏቸው ሲሆን ከባሕር ዳርቻ ካላቸው ሀገራት ጋር ቀልጣፋ፣ ሕጋዊ እና የረጅም ጊዜ መሸጋገሪይ(የትራንዚት) እና የጉምሩክ ስምምነቶች ያስፈልጓቸዋል፡፡ የወደብ አገልግሎትን ፈጣን ለማድረግ የሚያስችሉ የተቀናጁ የትራንስፖርት ኮሪደሮች፣ የባቡር እና የጭነት መኪና መንገዶች መገንባትም ይኖርባቸዋል፡፡
የሚያጋጥማቸውን የጂኦግራፊ እክልን ለመቀነስም በይነመረብን ያማከሉ የዲጂታል አገልግሎቶችን እና የኢ-ኮሜርስ ንግድን ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ የማይጠይቁ ክብደታቸው ቀላል ነገር ግን ዕሴታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምርቶችን ማምረት ላይም ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከአጎራባች ሀገራት ጋር የንግድ ቀጣናዎችና በነፃ የንግድ ስምምነቶች (ለምሳሌ እንደ አፍሪካ የንግድ ቀጣና) በጠንካራ ሁኔታ መሳተፍ ግድ ይላቸዋል፡፡
የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመራ የቆየው የቪዬና የድርጊት መርሃግብር ዋነኛው የአጋርነት ማዕቀፍ ነበር፡፡ መርሃ ግብሩ በባሕር በር አልባ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቀነስ የተዘጋጀ እ.አ.አ ከ2014 እስከ 2024 የቆየ የዐሥር ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀፍ ነው፡፡ ይህ መርሃ ግብር የመሠረተ ልማት ዝርጋታን፣ የንግድ ማሳደግን እና የትራንስፖርት ትስስር ማሻሻልን ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
የቪዬና መርሃ ግብር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) ያስቀመጣቸውን መብቶች በተግባር ለመተርጎም ሲያግዝ ቆይቷል፡፡ ኮንቬንሽኑ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በጎረቤት ሀገራት መሬት ላይ በነፃነት የመንቀሳቀስ እና ንግዳቸውን የማከናወን መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡
በትራንዚት ወቅት የሚጓጓዙ ዕቃዎች በአጎራባች ሀገራት ልዩ የጉምሩክ ቀረጥ እንዳይጣልባቸው የሚከለክሉ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ይደግፋል፡፡ የባሕር በር አልባ ሀገራት የባሕር በር ካላቸው ሀገራት ጋር በሚያደርጓቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት የወደብ አገልግሎቶችን በእኩልነት እንዲያገኙ ያበረታታም ነበር፡፡
የቪዬና የድርጊት መርሃ ግብር እ.አ.አ ከ2014 እስከ 2024 መጠናቀቁን ተከትሎም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚቆይ አዲስ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ ጸድቋል፡፡ ይህም የአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብር (Awaza Programme of Action 2024 –2034) በመባል ይታወቃል፡፡
ይህ ዕቅድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ የሚገኙ 32 የባሕር በር አልባ ታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ ለማድረግና ከተፈጥሮ አቀማመጣቸው የተነሳ ከባሕር በሩ ባለመድረሳቸው የሚነሱ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያለመ ነው፡፡
አዲሱ ዕቅድ ለምን አስፈለገ?
የቀደመው የቪዬና ዕቅድ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቀውሶች ማለትም እንደ ኮቪድ-19 እና በጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህም የባሕር በር አልባ ሀገራትን የወጪ ንግድ ዋጋ በማናር የኢኮኖሚ ተጋላጭነታቸውን አሳድጎታል፡፡
አዲሱ የ10 ዓመት ዕቅድ እነዚህን ክፍተቶች በዘመናዊ መንገድ ለመሙላት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ የአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብር በአምስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኩራል፡፡
የመጀመሪያው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ሲሆን ሀገራቱ ጥሬ ዕቃ ብቻ ከመላክ ወጥተው ምርቶቻቸውን እንዲያቀነባብሩ እና የንግድ ዘርፎቻቸውን እንዲያበዙ ያግዛል፡፡
ሁለተኛው በዲጂታል ንግድ እና በኢንተርኔት ትስስር አማካኝነት የተቀላጠፈ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ሦስተኛው የትራንስፖርትና የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን ፈጣንና ቀልጣፋ የሆኑ የድንበር ተሻጋሪ የባቡር፣ የመኪና መንገድ እና የኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን ማሳደግ ላይ ያተኩራል፡፡
አራተኛው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ነው፡፡ ይህም የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ለአየር ንብረት መዛባት ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው አረንጓዴ ኢኮኖሚንና የፋይናንስ ድጋፎችን ያመቻቻል፡፡ አምስተኛው የትኩረት አቅጣጫው ደግሞ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሲሆን ከጎረቤትና የባሕር በር ካላቸው ሀገራት ጋር የጉምሩክ አሠራርን ማቅለልና የጋራ የንግድ ኮሪደሮችን መፍጠር መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል፡፡
ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ
ኢትዮጵያ ይህንን ዕቅድ ከራሷ የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እና ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ጋር በማጣጣም እየተገበረችው ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለም አቀፍ የባሕር ኢኮኖሚ ዕድሎች ላይ እኩል የመሳተፍ መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ በጽኑ ታምናለች፡፡
ኢትዮጵያ ለምን የባሕር በር አስፈለጋት?
ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የባሕር በር ከሌላቸው ከፍተኛ ሕዝብ ካሏቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን ነው፡፡ የነዳጅና የሌሎች አስፈላጊ ምርቶች አቅርቦትን ለማረጋጋት፣ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ፣ ከዓለም ገበያ ጋር የተሻለ ቀጥተኛ ግንኙነት ለመፍጠር እና በአንድ የውጭ ወደብ ላይ ብቻ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የባሕር በር ግዴታ ያስፈልጋታል፡፡
ለምን ቀይ ባሕር? የሚለው ሲነሳ ደግሞ ቀይ ባሕር በአፍሪካና በእስያ መካከል የሚገኝ ሲሆን ወደ ስዊዝ ካናል የሚያስገባ ዋና የዓለም የባሕር ንግድ መስመር ነው፡፡ በተለይ ባብ አል-መንደብ የሚባለው የባሕር መግቢያ ከቀይ ባሕር ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤና ወደ ሕንድ ውቅያኖስ የሚወስድ ስትራቴጂካዊ መግቢያ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አካባቢ የሚገኝ ወደብ ለኢትዮጵያ በንግድ ብቻ ሳይሆን በቀጣናዊ ስትራቴጂም እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
አንዲት ሀገር የባሕር በር ስትፈልግ የሌላ ሀገርን ሉዓላዊ ግዛት መውሰድ ወይም ባሕሩን መቆጣጠር አይጠይቅም፡፡ ለምሳሌ በሁለት ሀገራት መካከል በሚደረግ ስምምነት አንዲት ሀገር የወደብ አጠቃቀም፣ የንግድ መብት ወይም ረጅም ጊዜ የሊዝ መብት ልታገኝ ትችላለች፡፡
ኢትዮጵያ በወደብ ላይ ሙሉ በሙሉ ቀጥተኛ መዳረሻ ስለሌላት የውጭ ንግዷ በሌሎች ሀገራት ወደቦችና የመጓጓዣ መስመሮች ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሲከሰት ወደብ፣ የትራንስፖርት ወጪ፣ የምርት ዋጋ እና የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ስለዚህ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገራዊ ስትራቴጂ ጉዳይም ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት የባሕር በር ጉዳይ ለምን አከራካሪ ሆነ? የሚለውን ስናይ እንደሚታወቀው ኤርትራ ነፃነቷን ከማግኘቷ ከ1983 ዓ.ም በፊት የኢትዮጵያ ክፍል ነበረች፡፡
በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ምፅዋና አሰብ የባሕር ወደቦች ቀጥተኛ መዳረሻ ነበራት፡፡ በ1983ዓ.ም ኤርትራ ነፃ ሀገር ከሆነች በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር ዳርቻ የሌላት ሀገር ሆናለች፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነታቸው ጥሩ ስለነበር ኢትዮጵያም የኤርትራን ወደቦች ለንግድ ትጠቀም ነበር፡፡
ከኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት በኋላ ግን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሻክሯል፡፡ ኢትዮጵያም የኤርትራን ወደቦች መጠቀሟን በማቆም የጅቡቲን ወደብ በስፋት መጠቀም ጀመረች። ይህ ለኢትዮጵያ ንግድ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም በአንድ ዋና የወደብ መስመር ላይ ብቻ መጠቀሟ ከፍተኛ ጥገኝነትን ፈጥሯል። የምታወጣው ወጪም በጣም ከፍተኛ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛትና እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር በመሆኗ የባሕር ንግድ መዳረሻዋን ማስፋት ግድ ይላታል። በዚያ ላይ የምፅዋ እና አሰብ ወደቦች በተፈጥሮ በጣም ቅርብ አማራጮች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
በነገራችን ላይ ከኢትዮጵያ ድንበር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአሰብ ወደብ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና መውጫና መግቢያ ነበረች፡፡ ይሁንና አሰብ ኤርትራ በ1983 ዓ.ም ነጻነቷን ስታገኝ ከኢትዮጵያ እጅ ወጥታለች፡፡ ወደቡ ባልተገባ መንገድ ከኢትዮጵያ ባለቤትነት እንዲወጣ መደረጉ ሀገራችንን ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፤ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ከባሕር በር አጠገብ የምትገኝ ብቸኛዋ የባሕር በር አልባ ሀገርም አድርጓታል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


