ሠላም የአምዳችን ተከታታዮች በዚህ እትም የምናስነብባችሁ ስለ ሆሊውድ እውነተኛ ገጽታ ነው፡፡ የዘመን አቆጣጠሩ ሁሉም በአውሮፖውያኑ ነው፡፡ በሆሊውድ ቡልቫርድ ታሪካዊ ጎዳና ላይ እግርዎን ሲያሳርፉ አየሩ ላይ የሚንሳፈፈው የካሊፎርኒያ ሞቃታማ ንፋስ ብቻ ሳይሆን የተስፋ፣ የህልም፣ የጥበብ እና የተረት ሽታ ጭምር ነው። ወደ ታች ሲመለከቱ፣ ከ2ሺህ 700 በላይ በሚሆኑ በሮዝ እብነ በረድ እና በነሐስ በተሰሩ የከዋክብት ስሞች የዝና ጎዳና ላይ ይራመዳሉ፤ የፀሐዩ ብርሃን በነሐሶቹ ላይ ሲያርፍ መንገዱን ያንፀባርቀዋል። እዚህ መሬት ላይ የተፃፈው እያንዳንዱ ስም ዝም ብሎ ፊደል ብቻ ሳይሆን የራሱ የሆነ የትግል፣ የእንባ፣ የውድቀት፣ የፅናት እና የስኬት ታሪክ ያለው ነው።
ዙሪያዎን ሲቃኙ ቦታው በሕይወት የተሞላ ነው። ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የመጡ ጎብኝዎች በሚያወሩት የተለያየ ቋንቋ ግርግር መሀል የካሜራ ብልጭታዎች በየሰከንዱ ይፈነጥቃሉ። በታዋቂው የቻይኒዝ ቲያትር ፊት ለፊት ከቀድሞዋ ማሪሊን ሞንሮ እስከ ዘመናዊው ስፓይደርማን፣ ቻርሊ ቻፕሊንን እና ባትማንን መስለው የለበሱ የጎዳና ላይ ጥበበኞች መንገዱን የፊልም ቀረፃ ስቱዲዮ አስመስለውታል። አልፎ አልፎ ጣሪያቸው ክፍት የሆኑ የጎብኝዎች አውቶቡሶች በዝግታ እያቋረጡ የከዋክብትን መኖሪያ ቤቶች ለማሳየት ሲጣደፉ ይታያሉ። ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ የዘመናችንን ፊልሞች የሚያስተዋውቁ ሰማይ ጠቀስ ዲጂታል ማስታወቂያዎች እንዲሁም ከሩቅ በሊ ተራራ ላይ በኩራት የተገተረው ያ ታሪካዊ ነጭ የ ሆሊውድ ምልክት የቦታውን ግርማ ሞገስ ያውጃሉ።
ይህ አካባቢ ሁለት የተለያዩ ዓለማት የሚገናኙበት አስማታዊ ስፍራ ነው፤ እጅግ አንፀባራቂው የፊልም ዓለም የቅንጦት ገፅታ እና ተራው የጎዳና ላይ እውነተኛ ሕይወት የሚላተሙበት ከተማ። ውጫዊ ገፅታው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀልብ የሚገዛው ይህ የዓለም “የህልም ፋብሪካ” ከካሜራ ብልጭታዎች፣ ከቀይ ምንጣፎቹ እና ከሚያስጎመዥ ድምቀቱ ጀርባ ግን የራሱ ጥልቅ ታሪክ፣ የከዋክብቱ ቅንጡ ኑሮ፣ እጅግ ውስብስብ የንግድ አሰራር እና ብዙዎቻችን የማናውቃቸው አስደናቂ ሚስጥሮች አሉት።
ከእርሻ መንደርነት እስከ ፊልም መዲናነት
ዛሬ ላይ በሆሊውድ ጎዳናዎች ቆሞ የፊልም ስቱዲዮዎችን እና የቅንጦት ኑሮን ሲመለከቱ ይህ ቦታ በአንድ ወቅት ፀጥ ያለ፣ አልኮል መጠጣት የተከለከለበት የግብርና መንደር እንደነበረ ማመን ይከብዳል። ታሪኩ የሚጀምረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ነው። በ1880ዎቹ ሀርቪ ዊልኮክስ የተባለ ሀብታም እና ባለቤቱ ዳይዳ ዊልኮክስ ከካንሳስ ወደ ካሊፎርኒያ በመምጣት 120 ኤከር መሬት ገዙ። ዓላማቸው ክርስቲያናዊ እሴቶች የሞሉበት ፀጥ ያለ መንደር መመስረት ነበር። “ሆሊውድ” የሚለውን ስም ያወጣችው ዳይዳ ዊልኮክስ ስትሆን ስሙን ያገኘችው በባቡር ጉዞ ላይ ካገኘቻት አንዲት ሴት የሰማችውን ቃል በመውደዷ ነበር። በ1903 ዓ.ም ሆሊውድ የከተማ አስተዳደር ቢሆንም የውሀ አቅርቦት ችግር ስለገጠመው በ1910 ዓ.ም ከሎስ አንጀለስ ከተማ ጋር ለመቀላቀል ተገደደ።
ወደ ፊልም ኢንዱስትሪነት የተቀየረበት ታሪክ ግን እጅግ አስገራሚ ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የፊልም ኢንዱስትሪ ማዕከል የነበረችው የኒውዮርክ እና ኒውጀርሲ አካባቢ ነበረች። በወቅቱ ፈጣሪው ቶማስ ኤዲሰን የፊልም ካሜራዎችን እና የፊልም ማምረቻ ቁሶችን የፈጠራ ባለቤትነት በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ስለነበር ነፃ የፊልም ሰሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግ እና ክስ ይመሰርት ነበር።
ከኤዲሰን ጫና ለማምለጥ የፈለጉ የፊልም ሰሪዎች ወደ ምዕራባዊቷ የአሜሪካ ጠረፍ ሸሹ። ሆሊውድ ለእነርሱ ገነት ሆነላቸው። ምክንያቱም አንደኛ የኤዲሰን ጠበቆች ከኒውዮርክ ተነስተው በቀላሉ ሊደርሱበት የማይችሉበት ርቀት ላይ ነበር። ሁለተኛ ክስ ቢመጣባቸው እንኳ የፊልም መሳሪያዎቻቸውን ይዘው ድንበር አቋርጠው ወደ ሜክሲኮ ለማምለጥ ቅርብ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን ሆሊውድ ዓመት ሙሉ ፀሐያማ መሆኑ እና ከባሕር ዳርቻ እስከ በረሃና በረዷማ ተራሮች በአንድ አካባቢ በመገኘታቸው ለቀረፃ ፍፁም ተስማሚ ስለነበረ ነው። በ1911 ዓ.ም “ኔስተር ስቱዲዮ” የተሰኘው የመጀመሪያው የፊልም ስቱዲዮ ከተከፈተ በኋላ ሆሊውድ ወደ ኋላ ተመልሶ አያውቅም።
የከዋክብቱ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች
ስለ ሆሊውድ ስናወራ የፊልም ኮከቦችን የቅንጦት አኗኗር መዝለል አይቻልም። ከሆሊውድ የንግድ ቀጣና እና የጎብኝዎች ግርግር ወጣ ብሎ ወደ ሆሊውድ ሂልስ፣ ቤቨርሊ ሂልስ እና ቤል ኤር ሰፈሮች ሲያመሩ የሆሊውድ እውነተኛው የሀብት እና የቅንጦት ልክ ይገለፃል። የፊልም ኮከቦች፣ ታዋቂ ዳይሬክተሮች እና የሙዚቃ ከያኒያን የሚኖሩባቸው እነዚህ ሰፈሮች ከተራው ዓለም ሙሉ በሙሉ የተነጠሉ እና የተለየ አየር ያላቸው ይመስላሉ።
በአስር እና በመቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ዶላር የሚገመቱት እነዚህ ግዙፍ መኖሪያ ቤቶች፣ የየራሳቸው የሆነ የግል የፊልም ማሳያ ቲያትር ቤቶች፣ የቴኒስ እና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች፣ ግዙፍ የመዋኛ ገንዳዎች፣ ስፓ፣ እጅግ ዘመናዊ የጂም ማዕከላት፣ የወይን ማከማቻዎች እና እጅግ ማራኪ የአትክልት ስፍራዎች አሏቸው። በአብዛኛው በስፔን ኮሎኒያል፣ ሜዲትራኒያን፣ እና እጅግ ዘመናዊ የህንፃ ዲዛይን የተገነቡት እነዚህ ቤቶች የተለየ የስነ-ህንፃ ጥበብ ማሳያዎች ናቸው።
እነዚህ ቤቶች በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ፣ በረዣዥም አጥሮች፣ የብረት በሮች እና በዘመናዊ ካሜራዎች የተከበቡ በመሆናቸው ማንም ተራ ሰው በቀላሉ ሊጠጋቸው አይችልም። ነገር ግን የጎብኝዎችን ጉጉት ለማርካት ሲባል “Starline Tours” የተሰኙ ጣሪያቸው ክፍት የሆኑ የቱሪስት አውቶቡሶች በየቀኑ ጎብኚዎችን እያጓጓዙ የከዋክብቱን ቤቶች አጥር እና የውጭ ገፅታ ያስጎበኛሉ። በእነዚህ ጉብኝቶች ላይ የብራድ ፒት፣ የሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ፣ የቢዮንሴ ወይም የኪም ካርዳሺያን ቤቶች የት እንደሚገኙ በጉጉት እያዩ ፎቶ የሚያነሱ ጎብኝዎችን ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ ቅንጡ ቤቶች የሆሊውድን ህልም እውንነት የሚያሳዩ ስኬት ምን ያህል የከበረ እንደሆነ የሚሰብኩ የዘመናችን ቤተ መንግሥቶች ናቸው።
ከካሜራ ጀርባ ያለው እውነተኛው ዓለም
የቅንጦት ቤቶቹ እና ደማቅ ፊልሞቹ ውጫዊ ገፅታው ሲሆኑ፣ የሆሊውድ የውስጥ አሰራር ግን እጅግ ፉክክር የበዛበት እና ብዙ የተሰበሩ ህልሞች የሚታዩበት የንግድ ዓለም ነው።
በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ኮከብ የመሆን ህልም ሰንቀው ወደ ሎስ አንጀለስ ይጎርፋሉ። እውነታው ግን አብዛኛዎቹ ተዋንያን የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን በምግብ ቤቶች አስተናጋጅነት፣ በታክሲ ሹፌርነት እና በሌሎችም ስራዎች ላይ ተሰማርተው የዕድላቸውን በር መከፈት ይጠብቃሉ። በሆሊውድ ከችሎታ ባሻገር “ማንን ታውቃለህ?” የሚለው ትልቅ ቦታ አለው። እንደ CAA እና WME የመሳሰሉት ታላላቅ የተዋናይ ተቋማት ከፍተኛ ስልጣን አላቸው። እነዚህ ተቋማት አዳዲስ ተዋንያንን የማውጣትም ሆነ ድምፃቸውን የማጥፋት ሙሉ አቅም አላቸው።
የሆሊውድ ኮከቦች አኗኗር፣ የሚለብሱት ልብስ፣ የሚሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ አልፎ ተርፎም የሚሰሩት የበጎ አድራጎት ስራ በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በጥንቃቄ የተቀነባበረ ነው። የአንድን ኮከብ ዝና መጠበቅ በሚሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ ትልቅ ቢዝነስ ነው። ከዚህም አልፎ የፍቅር ግንኙነቶች ሳይቀር ለፊልም ማስተዋወቂያ ሲባል በኮንትራት የሚፈጠሩበት ጊዜ አለ። ቅሌቶች ሲፈጠሩ ሁኔታውን ለማለዘብ ክራይስስ ማኔጀርስ የተባሉ ልዩ ባለሙያዎች ወዲያውኑ ስራ ይጀምራሉ።
ዘመናዊው ሆሊውድ በጣት በሚቆጠሩ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች (እንደ ዲስኒ፣ ዋርነር ብሮስ፣ ዩኒቨርሳል ያሉ) ቁጥጥር ስር ነው። ኢንዱስትሪው አዲስ የፈጠራ ስራዎችን ከመሞከር ይልቅ ኪሳራ በሌለው አሰራር ላይ ያተኩራል። በየዓመቱ በርካታ ተከታታይ ፊልሞች እና የሱፐር ሂሮ ፊልሞች በብዛት የሚሰሩት ከፍተኛ ትርፍ ስለሚያስገኙ ነው። ዛሬ ላይ ለአንድ አዲስ ወይም ወጥ ሀሳብ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ፈታኝ ሆኗል። ከዚህም በላይ የኔትፍሊክስ እና አማዞን ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀል የሲኒማ ቤቶችን ባህል በመቀየር ጦርነቱን ወደ ትኩስ ፉክክር ወይም እሽቅድምድም ቀይሮታል።
አጫጭር እውነታዎች
ሎስ አንጀለስ – አጫጭር እውነታዎች
- ሎስ አንጀለስ በካሊፎርኒያ ግዛት የምትገኝ ከተማ ናት።
- ሲቲ ኦፍ አንጀለስ – የመላእክት ከተማ ይሏታል።
- በከተማዋ ውስጥ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይኖራል።
- በ1781 እ.አ.አ የስፔን ቅኝ ገዥዎች ከተማዋን መሠረቱ።
- ሎስ አንጀለስ የዓለም የፊልምና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ታላቅ ማዕከል ናት። በተራራ ላይ የተቀመጠው የሆሊውድ ምልክት የከተማዋ ዋነኛ መለያ ነው።
- ሳንታ ሞኒካ፣ ቬኒስ እና ማሊቡ ያሉ ታዋቂ የባህር ዳርቻዎች በአካባቢዋ ይገኛሉ።
- ከተማዋ ከብዙ አገሮች የመጡ ሰዎች የሚኖሩባት በጣም ባህላዊ ብዝሃነት ያላት ከተማ ናት።
- እንግሊዝኛ በዋናነት ቢነገርም ስፓኒሽ እና ብዙ ሌሎች ቋንቋዎችም በስፋት ይነገራሉ።
- ፊልምና ቴሌቪዥን፣ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም፣ ፋሽን፣ የንግድ እና የወደብ እንቅስቃሴ ትልቅ የኢኮኖሚዋ ዘርፎች ናቸው።
- እንደ ሌከርስ፣ ዶጀርስ እና ራምስ ያሉ ታዋቂ የስፖርት ቡድኖች ከከተማዋ ጋር ይያያዛሉ።
- ሎስ አንጀለስ የ2028 የበጋ ኦሎምፒክ አስተናጋጅ ከተማም ናት።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


