ሕንድ

0
5

ሕንድ በደቡብ እስያ የምትገኝ ጥንታዊት ሀገር ናት፡፡ ከሰሜን ሂማሊያ ተራሮች እስከ ደቡባዊ የሕንድ ውቅያኖስ የሚሸፍን የቆዳ ስፋት አላት፡፡ ሕንድ በሕዝብ ብዛት ከዓለማችን ቀዳሚ ሀገሮች  አንዷ ናት፤ ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የሚጠጋ ሰው ይኖርባታል፡፡

ሕንድ ከሌሎች የዓለማችን ሀገራት የምትለይባቸው በርካታ መገለጫዎች አሏት፡፡ እንደ ሂንዱይዝም፣ ሲኪዝም፣ ቡድሂዝም እና ጄኒዝም ያሉ ዋና  ዋና ሃይማኖቶች ይመለኩባታል፡፡

ሕንድ በቅመማ ቅመም ምርቷ ትታወቃለች፡፡ በርካታ ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎች የሚገኙባት ሀገርም ናት፡፡ ታጅ ማሃል፣ ቫራናሲ፣ ጃይፑር፣  ኬራላ፣ ሌህ ላዳክ፣ ጎዋ፣ አጃንታ እና ኤሎራ ዋሻዎች፣ አምሪትሳር፣ ሙምባይ እንዲሁም ሀምፒ ዋና ዋናዎቹ የመስህብ ስፍራዎቿ ናቸው፡፡ ቀጥለን እያንዳንዳቸውን ባጫጭር ቆይታ በእግረ ህሊና በጽሑፍ እንጎበኛለን፤

  1. ታጅ ማሃል

በተባበሩት መንግሥታት  የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩ.ኔ.ስ.ኮ.) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ድንቅ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ የሚገኘው በኡታር ፕራዴሽ ግዛት በአግራ ከተማ በያሙና ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡ ያረፈበት ቦታ ወደ 17 ሄክታር ወይም 170  ሺህ ካሬ ሜትር ይጠጋል፡፡ ወደ 73 ሜትር ያህል ከፍታ አለው፡፡ ታጅ ማሃል የተሠራው በነጭ እብነ በረድ ነው፡፡ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሀያ አንድ ዓመታት (1632 – 1653) ወስዷል፡፡ ታጅ ማሃልን ያሠራው ንጉሠ ሻህ ጃሀን ነው፡፡ መስጊዱን ያስገነባውም በወሊድ ሕይወቷ ላለፈው ሚስቱ ሙምታዝ ማሃል ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ በማሰብ እንደኾነ ከ”ሂስትሪ ዶትኮም” ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

  1. ቫራናሲ

ቫራናሲ በሰሜን ሕንድ በኡታር ፕራዴሽ ግዛት ጋንጅስ ወንዝ ዳርቻ ትገኛለች፡፡  ቫራናሲ በሕንድ ዜጎች እንደ ቅዱስ ስፍራ የምትቆጠር ጥንታዊ ከተማ ናት፡፡ የሂንዱዊዝም ሃይማኖት ተከታዮች ወደ ከተማዋ በማምራት ወንዙ ውስጥ ይታጠባሉ፤ ጸሎት ያደርጋሉ፤ ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችንም ይከውናሉ፤ ከ”ብሪታኒያ ዶት ኮም” ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፡፡

በተለይም ምሽት በወንዙ ዳርቻ ጋንጋ አራቲ የተሰኘ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እሳት የያዙ መቅረዞችን በማንቀሳቀስ፣ በመዝሙር እንዲሁም በጸሎት ይከወናል፤ ብዙዎችም በወንዙ ዳርቻ ተሰብስበው ሥነ ሥርዓቱን ይከታተላሉ፡፡

ቫራናሲ ከሃይማኖት በተጨማሪ የትምህርት፣ የፍልስፍና፣ ሙዚቃን ጨምሮ የተለያዩ ሥነ ጥበባት ማዕከል በመኾን ስታገለገል ኖራለች፡፡ ከሕንድ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የኾነው የቫናራስ ሂንዱ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው በዚች ከተማ ነው፡፡

ቫራናሲ የሕይወት እና ሞት ትውፊታዊ ክዋኔ የሚፈጸምባት ከተማ ናት፤ ሕያዋን በጋንጅስ ወንዝ ሲታጠቡ እና ሲጸልዩ የሙታን አስከሬን ደግሞ ይቃጠልባታል፡፡

  1. ጃይፑር

ጃይፑር በሰሜን ምዕራብ ሕንድ በራጃስታን ግዛት ትገኛለች፤ የግዛቲቱ ዋና ከተማም ነች፡፡ ከሕንድ ዋና ከተማ ኒው ዴልሂ በደቡብ ምዕራብ በ270 ኪሎ ሜትር ርቀት በ1727 የተመሠረተችው ጃይፑር ሮዝ ከተማ በሚል ስያሜም ትታወቃለች፡፡ ከተማዋ ሮዝ የተባለችው በ1878 የዌልስ ልዑል (በኋላ ንጉሥ ኤድዋርድ 7ኛ የኾነው) ወደ ከተማዋ ሲመጣ ብዙ ህንጻዎች ሮዝ ቀለም ስለተቀቡ ነው፡፡

ጃይፑር በጌጣ ጌጥ ዕቃዎች እና የከበሩ ድንጋዮች፣ በባህላዊ ጨርቃ ጨርቅ፣ በእጅ ሥራ ውጤቶች፣ በቆዳ ምርቶች፣ በባህላዊ ምግቦች እንዲሁም በባህላዊ ሙዚቃ እና ዳንስ ትታወቃለች፡፡ ከተማዋ የሕንድ የኪነ ህንጻ ጥበብ የሚታይባት ናት፡፡ ለምሳሌም እንደ ሐዋ ማሀል ያሉ አስደናቂ የኪነ ህንጻ ጥበቦችን ማየት ይቻላል። ይህ ህንጻ የቤተ መንግሥቱ ሴቶች የከተማውን ሕዝብ እንቅስቃሴ ሳይታዩ ለመታዘብ ይችሉ ዘንድ 953 ትናንሽ መስኮቶች እንዲኖሩት ተደርጎ ተሠርቷል።

  1. ኬራላ

ኬራላ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቁ ቅመማ ቅመም ምርቶቿ እንዲሁም በውኃ ሀብቷ የምትታወቅ የመስህብ ስፍራ ናት፡፡ እኛም ሀገር በስፋት ከሻይና ከተለያዩ ነገሮች እየጨመርን የምንጠቀምበት ቀረፋ (ሲናሞን) እንዲሁም በተለምዶ ሄል የምንለው (ካራዳሞም)  ከታዋቂ ቅመማ ቅመም ምርቶቿ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአክሱም ዘመነ መንግስትም ከሕንድ የመጡ ነጋዴዎች በአዱሊስ ወደብ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የቅመማ ቅምም ንግድ ያደርጉ ነበር፡፡

ያረብ ባሕር፣ ወንዞች፣ ሐይቆች… ተደማምረው ኬራላን ማራኪ የመስህብ ስፍራ አድርገዋታል፡፡  በምዕራብ ባረብ ባሕር የተከበበች ሲሆን ባሕሩ፣ ዘንባባዎች እንዲሁም ያሸዋ ዳርቻዎቿ ልዩ መስህቦቿ ናቸው፡፡

ከኬራላ  የውኃ አካላት መካከል ቬምባናድ ሐይቅ በጣም ትልቁ ነው፤ ስመ ጥርም ነው፡፡ በቬምባናድ ሐይቅ ዳርቻ የሚገኘው ኩማራኮም የጎብኝን ቀልብ የሚስብ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ ጠዋት በጀልባ ላይ ኾኖ ጸጥ ያለውን ውኃ ማየት፣ የወፎችን ዝማሬ ማዳመጥ፣ በውኃው ዳር እጅብ ብሎ የበቀለውን የኮኮናት ዛፍ መመልከት በእጅጉ ያስደስታል፡፡ ኬራላ ባላት በርካታ የተማረ የሰው ኃይልም ትታወቃለች፡፡

  1. ሌህ-ላዳክ

ሌህ-ላዳክ ከተማ በሰሜናዊ ሕንድ በሂማሊያ ተራሮች መካከል ከባሕር ወለል በላይ 3ሺህ 500 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡ ሌህ ላዳክ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ፓንጎግን የመሳሰሉ ሰፋፊ ሐይቆች ይገኙባታል፡፡ በበረዶ የተሸፈኑ የተራራ ሰንሰለቶች፣ ሸለቆዎች እና ጥንታዊ የቡድሂስት ገዳማትም መገኛ ናት፡፡

  1. ጎዋ

ጎዋ በዓረብ ባሕር ዳርቻ የምትገኝ ሲሆን ተፈጥሮ ውበትን አብዝታ የቸረቻት ስፍራ ናት፡፡   ካላንጉቴ፤ ባጋ፣ አንጁና፣ ፓሌሎም… በተሰኙት ወርቃማ አሸዋማ የባሕር ዳርቻዎቿ፣ በየኮኮናት ዛፎቿ፣ በምሽት ውብ ድባቧ፣ በጥንታዊ ህንፃዎቿ ትታወቃለች። ጎዋ የባሕር ምግብ እየተመገቡ ለመዝናናት ተመራጭ ናት።

ጎዋ ለረዥም ጊዜ በፖርቹጋል ቅኝ ተገዝታለች፡፡ በዚህ የተነሳም የአውሮፓ የታሪክ አሻራዎች ገዝፈው የሚታዩባት ከተማ ናት፡፡ ይህ የቅኝ ግዛት አሻራ በህንጻዎቿ፣ በአብያተ ክርስቲያኖቿ፣ በመንገዶቿ… ጎልቶ ይታያል፡፡

ጎዋ በተለይም በምሽት አስደማሚ ገጽታ ትላበሳለች፡፡ የባሕር ዳርቻዎቿ በሰዎች ይሞላሉ፤  የሙዚቃ ድምጾች ይስረቀረቃሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በጎዋ መገኘት ልዩ ሀሴትን ይሰጣል፡፡ ጎዋን መጎብኘት ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ የባሕር ዳርቻ ሕይወትን በማጣጣም የደስታዎችን ሁሉ ደስታ ለማግኘት ያስችላል፡፡

  1. አጃንታ እና ኤሎራ ዋሻዎች

አጃንታ እና ኤሎራ ዋሻዎች በአጃንታ መንደር በማሃራሽትራ ግዛት በምዕራብ ሕንድ  ይገኛሉ፡፡ እነዚህ  ዋሻዎች ሕንድ ለሺህ ዓመታት ያዳበረችውን የጥበብ፣ የሃይማኖት፣ የምሕንድስና፣ የባህል… ትውፊት የሚያሳዩ የታሪክ አሻራዎች ናቸው፡፡

አጃንታ ከአለታማ ተራራ  ተፈልፍለው የተሠሩ ዋሻዎች የሚገኙባት ታሪካዊ ስፍራ ናት፡፡ በዋሻዎቹ ውስጥ የሚገኙት ጥንታዊ ሐውልቶች እንዲሁም ሥዕሎች በጥንት ዘመን የቅርጻ ቅርጽ እንዲሁም የሥዕል ጥበብ በሕንድ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው፡፡  ከአንድ ግዙፍ አለት ተፈልፍለው የተሠሩት እነዚህ ጥንታዊ የቡድሂስት፣ የሂንዱ እና የጄን ገዳማት እና ቤተ መቅደሶች፣ በውስጣቸው የያዟቸው ሥዕሎች እና ቅርጻ ቅርጾች ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ  ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቅርሶች  ናቸው። በዋሻዎቹ ግድግዳዎች ላይ  የቡድሃን ታሪክ፣ የዘመኑን ሒንዱዎች አለባበስ፣ ጌጣ ጌጦች፣ አኗኗር፣ የንጉሣዊያን ቤተሰቦች ሕይወት የሚያሳዩ ሥዕሎች ይገኛሉ፡፡

ኤሎራ የቡድሂስት፣ የሒንዱ እና የጄይን ባህል የሚያሳዩ አያሌ ዋሻዎች የሚገኙባት ማራኪ ስፍራ ናት፡፡ በኤሎራ ካንድ አለት ተፈልፍሎ የተሠራዉ የካይላላ ቤተ መቅደስ ይገኛል፡፡

  1. አምሪትሳር

አምሪትሳር ባለማችን ላይ ከሚገኙ ቅዱሳን ስፍራዎች አንዷ ናት፡፡ ወርቃማው ቤተ መቅደስ በከተማዋ ከሚገኙ ድንቅ የመስህብ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ ሳሮቫር በተባለው ቅዱስ ኩሬ መሀል ይገኛል፡፡ ቦታው የአንድነት፣ የእኩልነት… ቦታም ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በየቀኑ ዘር፣ ሃይማኖት እና ማህበራዊ ደረጃ ሳይለይ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነፃ ምግብ የሚያቀርብ ግዙፍ ምግብ ቤትም  አለው።

ከወርቃማው ቤተ መቅደስ ብዙም ሳንርቅ ጃሊያን ዋላ ባህ የተባለውን ቦታ እናገኛለን፡፡ ይህ ቦታ በቅኝ ግዛት ዘመን በስብሰባ ላይ በነበሩ ሕንዳዊያን ላይ  የጅምላ ግድያ የተፈጸመበት ነው፡፡ እናም ሕንዳዊያን ለነጻነት መረጋገጥ ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያስታውሱበት ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡

  1. ሙምባይ

ሙምባይ በሕንድ ምዕራባዊ ጠረፍ በአረብ ባሕር ዳርቻ የምትገኝ  የንግድ እና የቦሊዉድ ሲኒማ ማዕከል ናት፡፡ በአረብ ባሕር ዳርቻ ላይ ታሪካዊው “የሕንድ በር” ይገኛል፡፡ ይህ በር የከተማዋ ዋነኛ የመስህብ ስፍራ  ነው። ከበሩ አቅራቢያ ታሪካዊው የታጅ ማሃል ህንጻ ይታያል፡፡ በከተማዋ ባላቸው የገቢ መጠንና በሀብት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሀብታሞች እንዲሁም የዕለት ከዕለት ሕይወታቸውን ለመምራት የሚቸገሩ ድሆች ይኖሩባታል፡፡

ሙምባይ ስትወሳ ቦሊውድም ይጠቀሳል- ከተማዋ የሕንድ የፊልም ኢንዱስትሪ ዋነኛ ማዕከል ናትና፡፡ ከሕንድ አልፈው ሀገራችንን ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም በብዙ ተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ በዳንስ የታጀቡ የሒንዱ ፊልሞች እና ዘፈኖች  የሚቀረጹት እንዲሁም የሚከወኑት በዚህ ስፍራ ነው፡፡

  1. ሃምፒ

የጥንታዊው ቪጃያናጋራ ግዛት ዋና ከተማ የነበረችው ሃምፒ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት፣ የባህል ድርጅት (ዩ.ኔ.ስ.ኮ.) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበች ፍርስራሽ ከተማ ናት። ከተማዋ በ1565 በተካሄደ ጦርነት ብትፈራርስም በሺዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቤተ መቅደሶች፣ የገበያ ቦታዎች እና የቤተ መንግሥት ፍርስራሾች በትላልቅ ድንጋዮች መካከል ተበታትነው የሚገኙባት በመሆኑ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች እንዴት እንደተነሱ እና እንደወደቁ የምትመሰክር የታሪክ መማሪያ ናት፡፡

የዛሬዋ ፍርስራሽ ከተማ ሃምፒ ባንድ ወቅት ነጋዴዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ጎብኝዎች፣ ነዋሪዎች… ይርመሰመሱባት የነበረች ደማቅ ከተማ እንደነበረች ከ”ሂስትሪ ዶት ኮም” እንዲሁም “ብሪታኒያ ዶት ኮም” ድረ ገጾች ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

(ቦረቦር ዘዳር አገር)

በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬ ሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here