ውድ ልጆች! «ሀገሬ ኢትዮጵያ ናት» ስትሉ ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አስባችሁና አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? ብዙዎቻችን ሀገር ሲባል በዓይነ ሕሊናችን የሚታየን በትምህርት ቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ባለብዙ ቀለም ካርታ፣ በነፋስ የሚውለበለበው ውቡ ሰንደቅ ዓላማ ወይም ማለዳ ላይ ቆመን በኩራት የምንዘምረው ብሔራዊ መዝሙር ሊሆን ይችላል። ይህ እውነት ቢሆንም ሀገር ግን ከዚያ በላይ በጣም ሰፊ፣ ጥልቅ እና በአጭር ቃል የማይገለጽ ትልቅ ትርጉም ያላት ውድ ስጦታ ናት። እያንዳንዳችን በየቀኑ የምንበላበት፣ የምንተኛበት እና ከቤተሰቦቻችን ጋር የምንጫወትበት የራሳችን ትንሽ ቤት እንዳለን ሁሉ ሀገር ማለት ደግሞ የሁላችንም ትናንሽ ቤቶች፣ መንደሮች እና ከተሞች በአንድ ላይ የሚገኙባት፣ ሁላችንንም እንደ እናት አቅፋ የያዘች ትልቅ የጋራ ቤታችን ናት። በዚህች ሰፊ እና ታላቅ ቤት ውስጥ ውድ ወላጆቻችሁ፣ ተወዳጅ ጓደኞቻችሁ፣ ትጋት ያላቸው መምህሮቻችሁ እና በየመንገዱ የምታዩአቸው ሰዎች ሁሉ በአንድነት ይኖራሉ። በደስታ የምናከብራቸው ደማቅ በዓላት፣ በማዕድ ዙሪያ የምንመገበው ጣፋጭ ምግብ፣ በበዓል ቀን የምንለብሰው ያማረ ነጭ የባሕል ልብስ፣ በደስታ የምንጨፍረው ጨዋታ እና የምንነጋገራቸው የተለያዩ ውብ ቋንቋዎች በሙሉ የዚህች ትልቅ ቤት ድምቀቶች እና ቀለማት ናቸው። ከዚህም በላይ ሀገር ስንል የምንረግጠውን መሬት ብቻ ሳይሆን ዓይናችንን ገልጠን የምናያቸውን ሰማይ ጠቀስ ረዣዥም ተራሮች፣ ትላልቅ ወንዞች፣ በወፍ ዝማሬ የተሞሉትን አረንጓዴ ደኖች፣ በሜዳ ላይ የሚፈነጩትን ውብ እንስሳት እና አየሩን ጭምር ያጠቃልላል።
ከእኛ በፊት በዚህች ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩት አያቶቻችን እና ቅድመ-አያቶቻችን ይህችን ውብ ሀገር በነፃነት፣ በክብር እና በጀግንነት ጠብቀው ስላቆዩልን እኛ ዛሬ በደስታ እና በነፃነት ለመኖር፣ ለመማር እና ሕልማችንን ለማሰብ በቅተናል።
ስለዚህ ውድ ልጆች ሀገር ማለት ዝም ብሎ መሬት ወይም ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ነን። እርስ በርሳችን ስንዋደድ፣ በትምህርታችን ስንተጋ፣ አዋቂዎችን ስናከብር እና ለአካባቢያችን ጥንቃቄ ስናደርግ ሀገራችንን በትክክል እየወደድን ነው ማለት በመሆኑ እናንተም ዛሬ ጥሩ እና ታዛዥ ልጆች ስትሆኑ ነገ የምትረከቧትን ታላቅ ሀገራችሁን ይበልጥ ታስውቧታላችሁ ይላል፤ ብሪታኒካ ኪድስ ላይ ያገኘነው መረጃ።
ተረት
ውሸታሙ ልጅ
በአንድ ተራራማ መንደር ውስጥ «ናሆም» የሚባል ፍየሎችን የሚጠብቅ እረኛ ልጅ ነበር። ናሆም በየቀኑ ፍየሎቹን እየነዳ ወደ ሜዳ ሲወጣ በጣም ስለሚሰለቸው በመንደሩን ሰዎች ለማሾፍ አንድ ተንኮል አሰበ፤ በአንድ ኮረብታ ላይ ቆሞ «ተኩላ መጣ! እባካችሁ እርዱኝ!» እያለ ጮኸ። የመንደሩ ሰዎችም የናሆምን ጩኸት ሰምተው ፍየሎቹን ለማዳን እየተጣደፉ መጡ፤ ነገር ግን እዚያ ሲደርሱ ምንም ተኩላ አልነበረም፣ ናሆምም ሰዎች ሲደናገጡ እያየ በሳቅ ይንከባለል ጀመር። ሰዎችም በጣም አዝነው «ልጄ ሆይ በውሸት አትቀልድ!» ብለውት ወደ ቤታቸው ተመለሱ፤ ናሆም ግን በሚቀጥለውም ቀን ይሄንኑ ውሸት ደግሞ ሰዎቹን አታለላቸው።
በሦስተኛው ቀን ግን አንድ ትልቅ እና አስፈሪ ተኩላ ከጫካ ወጥቶ በፍየሎቹ ላይ ዘለለ። ናሆም በጣም ደንግጦ እና ፈርቶ «እባካችሁ ተኩላ መጥቷል! እርዱኝ!» እያለ በኃይል ጮኸ፤ ነገር ግን የመንደሩ ሰዎች የለመደውን ውሸት እየዋሸ መስሏቸው ማንም ሊረዳው አልመጣም። ተኩላውም ፍየሎቹን በላበት፤ ናሆምም ምንም ማድረግ ሳይችል ቀርቶ እያለቀሰ ወደ መንደሩ ተመለሰ። ከዚያ ቀን ጀምሮ ናሆም ውሸት ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ራስንም እንደሚጎዳ ተረዳ፤ መቼም ቢሆን እውነትን ብቻ ለመናገር ቃል ገባ።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች
ሞክሩ
- በዓለማችን ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ ትልቁ የትኛው ነው?
- ሲመቱት ይጮሃል፣ ሲተውት ዝም ይላል -ምንድን ነው?
- እግር የለኝም ሮጣለሁ፤ አፍ የለኝም እናገራለሁ፤ እኔ ማነኝ?
መልስ
- አሳ ነባሪ
- ከበሮ
- ሬድዮ
ነገር በምሳሌ
“እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ”
አንዳንድ የማይጠቅሙ ወይም የማይመለከቱን ነገሮች ላይ ጣልቃ አለመግባትና ማለፍን መልመድ ያስፈልጋል።
“የቀደመ በላ፣ የዘገየ አበላ”
ነገሮችን በጊዜውና ቀድሞ መሥራት ሁልጊዜም ስኬታማ ያደርጋል።
ትዕግስት መራራ ናት፣ ፍረዋ ግን ጣፋጭ ነው
አንድን ነገር በትዕግሥት መጠበቅ መጀመሪያ ላይ ቢከብድም በመጨረሻ ግን በጣም ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


