“ቶንሲል አለኝ” ማለት ምን ማለት ነው?

0
587

“ቶንሲል አመመኝ” ወይም “ቶንሲል አለኝ” የሚለው አገላለጽ በዕለት ተዕለት ንግግራችን የተለመደ ነው። ጉሮሮ ሲያም፣ ምግብ ለመዋጥ ሲከብድ፣ ትኩሳት ሲኖር ወይም በጉሮሮ ውስጥ ነጭ ነጠብጣብ ሲታይ “ቶንሲል ነው” ማለት የተለመደ ነው።

ነገር ግን ቶንሲል ራሱ በሽታ ሳይሆን፣ በጉሮሮ ጀርባ በሁለቱም ጎኖች የሚገኝና ሰውነታችንን ከበሽታ አምጪ ተሕዋስያን ለመጠበቅ የሚረዳ የመከላከያ አካል ነው።

ቶንሲሉ ሲቆጣ ወይም በበሽታ አምጪ ተሕዋስያን ሲጠቃ ግን የቶንሲል እብጠት ይከሰታል።

የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንገት በላይ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ካሳው ከተማ እንደሚያብራሩት፣ የቶንሲል እብጠት በአብዛኛው በቫይረስ፣ አንዳንዴም በባክቴሪያ ይከሰታል።

የተለመዱ ምልክቶቹም የጉሮሮ ሕመም፣ ምግብና ፈሳሽ ሲዋጥ ሕመም፣ ትኩሳት፣ የቶንሲል መቅላትና ማበጥ እንዲሁም በቶንሲል ላይ ነጭ ወይም ቢጫ ነጠብጣብ መታየት ናቸው።

ሆኖም ምልክቶቹ ብቻቸውን በሽታው በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ መከሰቱን ስለማያረጋግጡ፣ በሐኪም ማስመርመር ያስፈልጋል። ጸረ  ተሕዋሲያን መድኃኒት (አንቲባዮቲክ) በራስ ፈቃድ አይወሰድም።

ዶ/ር ካሳው እንደሚገልጹት፣ በቫይረስ የሚመጣ የቶንሲል እብጠት በአንቲባዮቲክ አይድንም። መድኃኒቱ የሚሰጠው የባክቴሪያ በሽታ መሆኑ ሲረጋገጥና በሐኪም ግምገማ መሠረት ነው። አላስፈላጊ አንቲባዮቲክ መውሰድም መድኃኒትን የማይቀበሉ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን እንዲበዙ ሊያደርግ ይችላል።

ቶንሲል በሽታ ሳይሆን በጉሮሮ ጀርባ በሁለቱም ጎኖች የሚገኝ  ሰውነታችንን ከኢንፌክሽን የሚጠብቅ የመከላከያ ሥርዓት አካል ነው፡፡ ይህ አካል ሲቆጣ ወይም በኢንፌክሽን ሲያዝ  ግን “ቶንሲሊቲስ” የሚባለው የጤና ችግር ይከሰታል፡፡ በተለይ በህጻንነት የዕድሜ ክልል ላይ በተደጋጋሚ በኢንፌክሽን መጠቃት ሲኖር የቶንሲል ሕመም ይፈጠራል፡፡

እንደ ባሙያው ማብራሪያ ህጻናት እያደጉ ሲሄዱ ቶንሲሎች በተፈጥሮ መጠናቸው ሊቀንሱ ይችላል፤ ሆኖም ከሰባት እስከ 10 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ላይ በተደጋጋሚ ኢንፌክሽን ከሌለ ቶንሲል ሥራውን ስለሚጨርስ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስለዚህ አዋቂዎች ላይ የቶንሲል ኢንፌክሽን ሊኖር አይችልም፡፡

ቶንሲሊቲስ ለምን ይከሰታል?

ቶንሲሊቲስ በአብዛኛው በቫይረስ፣ አንዳንዴም በባክቴሪያ ኢንፌክሽን ይከሰታል። ኢንፌክሽኑ ከታመመ ሰው ጋር በቅርብ ንክኪ፣ በሳልና በማስነጠስ የሚወጡ ጠብታዎች ወይም በተበከለ ምራቅ ሊተላለፍ እንደሚችል ሃኪሙ አብራርተዋል፡፡

የቶንሲል ህመም የተለመዱ ምልክቶች፦

የጉሮሮ ሕመም፤ ምግብና ፈሳሽ ሲዋጥ የሕመም ስሜት፤ ትኩሳት፤ የቶንሲል መቅላትና ማበጥ፤ በቶንሲል ላይ ነጭ ወይም ቢጫ ነጠብጣቦች ወይም መግል መያዝ፤ የአንገት አካባቢ ማበጥ፤ የድምፅ ለውጥና የሰውነት ድካም ይከሰታል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች ብቻቸውን ቶንሲሊቲስ በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ መከሰቱን በእርግጠኝነት ሊያሳዩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ምልክቶችን እና የጉሮሮን ሁኔታ በሐኪም ማስመርመር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ካሳው ማብራሪያ፣ በቫይረስ የሚመጣ ቶንሲሊቲስ በጸረ ተሕዋሲያን መድኃኒት (አንቲባዮቲክ) አይድንም፡፡ አንቲባዮቲክ የሚሰጠው የባክቴሪያ ኢንፌክሽን መሆኑ ወይም ሲረጋገጥና በሐኪም ግምገማ መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ አንቲባዮቲክን በራስ ፈቃድ መጀመር አይመከርም፤ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ  መድኃኒቱን መውሰድ የመድኃኒት መላመድን ሊያስከትል ይችላል፡፡

አንድ ሰው በተደጋጋሚ የቶንሲል ኢንፌክሽን ካለበት ለሐኪም የሕመሙን ታሪክ በግልጽ መንገር ወሳኝ ነው፡፡ በዓመት ስንት ጊዜ እንደሚያጋጥም፣ ምን ዓይነት ምልክቶች እንደሚኖሩ፣ ሕክምና እንደተደረገና ችግሩ በሥራ፣ ትምህርት ወይም በእንቅልፍ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው መግለጽ ይጠቅማል፡፡

በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ የጆሮ፣ አፍንጫና ጉሮሮ ስፔሻሊስት በሽታውን ከገመገመ በኋላ ተጨማሪ ሕክምና ወይም ቀዶ ሕክምና ያስፈልግ እንደሆነ ይወስናል፡፡

ቶንሲል ማስወገድ መቼ ይታሰባል? እንደ ዶ/ር ካሳው ገለጻ ቶንሲል ማስወገድ ለሁሉም ቶንሲሊቲስ የሚደረግ ሕክምና አይደለም፡፡ የቀዶ ሕክምና ውሳኔ በተወሰኑ የሕክምና ሁኔታዎች ላይ ብቻ ይመሠረታል፡፡

በተለይ፦

ቶንሲሊቲስ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የኑሮ ሁኔታን ሲረብሽ፤

በቶንሲል አካባቢ ከባድ ኢንፌክሽን ተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ፤

ቶንሲሎች በጣም በማደጋቸው በእንቅልፍ ጊዜ መተንፈስን ካስቸገሩ እና ሌሎች የተለዩ የሕክምና ምክንያቶች ሲኖሩ የቀዶ ሕክምና ውሳኔ ሊወሰን ይችላል፡፡

ቀዶ ሕክምናው ተገቢ በሆነ ሕመምተኛ ላይ ሲደረግ ተደጋጋሚ ኢንፌክሽንን ሊቀንስና ከትልቅ ቶንሲል ጋር የተያያዙ የእንቅልፍና የመተንፈስ ችግሮችን ሊያሻሽል ብሎም ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ይችላል ፡፡

ሆኖም ይህ ቀዶ ሕክምና እንደሌሎች ቀዶ ሕክምናዎች የደም መፍሰስ፣ የሕመም መኖር እና ከማደንዘዣ ጋር የተያያዙ አደጋዎች ሊኖሩት ስለሚችል፣ “ቶንሲል አለኝ” በሚል ብቻ ቀዶ ሕክምና መወሰድ እንደማይገባ ሃኪሙ ይመክራሉ፡፡

መቼ አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልጋል?

ቀላል የቶንሲሊቲስ ምልክቶች ሲኖሩ በቂ እረፍትና ፈሳሽ መውሰድ ያስፈልጋል ያሉት ሃኪሙ ለጉሮሮ ሕመምና ትኩሳት የሚያገለግሉ ተገቢ መድኃኒቶችንም በሐኪም ወይም በፋርማሲ ባለሙያ ምክር መጠቀም ይቻላል፡፡

ለጉሮሮ የማይከብዱ ለስላሳ ምግቦችን መመገብም ይጠቅማል፡፡

አንዳንድ የቶንሲሊቲስ ጉዳዮች በቀላል እንክብካቤ ሊሻሻሉ ቢችሉም፣ ከባድ ምልክቶች ሲከሰቱ ግን መዘግየት አደገኛ ሊሆን ይችላል ይላሉ ዶ/ር ካሳው።

ከነዚህም ውስጥ፡-

መተንፈስ መቸገር፤

ምራቅን መዋጥ አለመቻል፤

ከፍተኛ የአንገት እብጠት፤

አፍን መክፈት በጣም መቸገር፤

ከፍተኛ ድርቀት፤

የሕመሙ ሁኔታ በፍጥነት እየባሰ መሄድ እና በተለይ ሕፃን ፈሳሽ መውሰድ ካልቻለ፣ ሽንቱ ከቀነሰ ወይም የመተንፈስ ችግር ካሳየ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርበታል።

ቶንሲሊቲስን እንዴት እንከላከል?

ሁሉንም የጉሮሮ ኢንፌክሽን መከላከል ባይቻልም፣ ቀላል የንጽህና ልምዶች የኢንፌክሽን ስርጭትን ሊቀንሱ ይችላሉ።

ዋና ዋና የመከላከያ መንገዶች፦

እጅን በደንብና በተደጋጋሚ መታጠብ፤

የግል ዕቃዎችን ከሌሎች ጋር አለመጋራት፤

ከታመመ ሰው ጋር ያለውን የቅርብ ንክኪ መቀነስ፤

ሲያስሉና ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫን መሸፈን።

ቶንሲል አለኝ ማለት በሽታውን በትክክል ከመግለጽ ይልቅ ቶንሲልን ከቶንሲሊቲስ ጋር የሚያምታታ አገላለጽ ነው። ቶንሲል የሰውነት መከላከያ አካል ሲሆን፣ ችግሩ የሚከሰተው ሲቆጣ ወይም በኢንፌክሽን ሲያዝ ነው።

ስለዚህ በቶንሲል ስም ብቻ አንቲባዮቲክ መጀመርም ሆነ ቀዶ ሕክምና መወሰን አይገባም። የበሽታውን መንስኤ፣ ክብደትና ተደጋጋሚነት በባለሙያ ማስመርመር ዋናው መፍትሔ ነው። በተለይም ተደጋጋሚ የጉሮሮ ሕመም፣ የመዋጥ ወይም የመተንፈስ ችግር ሲኖር የጆሮ፣ አፍንጫና ጉሮሮ ስፔሻሊስትን ማማከር ተገቢ ነው ሲሉ ዶ/ር ካሳው ሙያዊ ምክራቸውን አካፍለወዋል።

መረጃ

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚገልጸው፣ አብዛኛው የጉሮሮ ሕመም በቫይረስ የሚከሰት በመሆኑ አንቲባዮቲክ ሕክምና አያስፈልገውም። ባክቴሪያዊ ኢንፌክሽን፣ በተለይም የGroup A Streptococcus /የጉሮሮ በሽታ ሊያመጣ የሚችል ባክቴሪያ/በሽታ ሲጠረጠር ወይም ሲረጋገጥ ግን አንቲባዮቲክ ሊያስፈልግ ይችላል።

እንደ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (CDC) መረጃ መሠረት፣ የጉሮሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ውስጥ የStrep throat ባክቴሪያ የሚከሰተው በግምት ከአዋቂዎች 10 በመቶ እና ከሕፃናት 30 በመቶ ያህል ብቻ ነው። በተለይ ከ5–15 ዓመት ዕድሜ ባሉ ሕፃናት የStrep throat የመከሰት ዕድሉ ከፍ ያለ ሲሆን፣ የጉሮሮ ምርመራ በቫይረስና በባክቴሪያ መካከል ትክክለኛ ልዩነት ለማድረግ ያግዛል።

WHO በተጨማሪ አንቲባዮቲክን ያለአግባብ መጠቀም የመድኃኒት መቋቋምን (antimicrobial resistance) እንደሚያበረታታ ያስጠነቅቃል። ስለዚህ የቶንሲሊቲስ መንስኤ ሳይታወቅ አንቲባዮቲክ በራስ ፈቃድ መውሰድ አይመከርም።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here