ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጅት

0
68

ረጅሙ የክረምት ዕረፍት ተጠናቆ አዲስ የትምህርት ዘመን ሊጀምር ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተዋል። አዲስ ክፍል መግባት፣ አዳዲስ ጓደኞችን ማፍራት እና አዳዲስ እውቀቶችን መቅሰም ሁልጊዜም እጅግ የሚያስደስት የሕይወት ምዕራፍ ነው። በትምህርታችን ጎበዝ እና በባህሪያችን ምስጉን ለመሆን ራሳችንን ከአሁኑ ማዘጋጀት ይኖርብናል። ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ ለመሆን የሚረዱንን አምስት ወርቃማ መንገዶች እነሆ፦

  1. የእንቅልፍ ሰዓትን ማስተካከል

በዕረፍት ጊዜ ረጅም ሰዓት የመተኛት ወይም የማምሸት ልምድ ሊኖረን ይችላል። ነገር ግን ትምህርት ሲጀምር ጠዋት በጊዜ መነሳት ግዴታ ነው። ስለዚህ ትምህርት ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊት በጊዜ የመተኛት እና ጠዋት በጊዜ የመነሳት ልምድን ማዳበር አለብን። ይህ ልምድ ጠዋት በትምህርት ገበታችን ላይ ንቁ እና ብሩህ እንድንሆን ይረዳናል።

  1. የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላት

ደብተሮችን መሸፈን፣ ስማችንን መጻፍ፣ ቦርሳችንን፣ እርሳስ፣ ስክሪፕቶ እና የደንብ ልብሶቻችንን በጥንቃቄ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ቁሳቁሶቻችንን በጊዜ ስናደራጅ ለአዲሱ ክፍል ያለን መነሳሳት እና ጉጉት ይጨምራል። ሁልጊዜም ንጹሕ እና የተስተካከለ የትምህርት መሣሪያ መያዝ ለትምህርት ያለንን አክብሮት ያሳያል።

  1. የንባብ ልምድን ማደስ

አእምሯችን ልክ እንደ ጡንቻ ስፖርት ይፈልጋል። በክረምቱ ካነበብናቸው ታሪኮች በተጨማሪ ያለፈውን ዓመት ማስታወሻዎች በአጭሩ መከለስ እና የመጪውን ክፍል መጻሕፍት ገለጥለጥ አድርጎ ማየት ይመረጣል። ይህ ዝግጅት አዲሱ ትምህርት ሲጀምር እንግዳ እንዳንሆን እና መምህራን የሚያስተምሩትን በቀላሉ እንድንረዳ መንገድ ይጠርጋል።

  1. ግብ ወይም ዓላማ ማስቀመጥ

“በዚህ የትምህርት ዘመን ምን ማሳካት እፈልጋለሁ?” ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል። ለምሳሌ፦ በየቀኑ ማጥናት፣ የሂሳብ ትምህርት ውጤቴን ማሻሻል፣ አዳዲስ መጻሕፍትን ማንበብ ወይም በትምህርት ቤቱ የስፖርት እና የኪነ-ጥበብ ክበባት ውስጥ መሳተፍ ሊሆን ይችላል። ግብ አስቀምጦ መንቀሳቀስ የታላላቅ ተማሪዎች ምስጢር ነው።

  1. አዎንታዊ እና ደስተኛ አእምሮ መያዝ

አዲስ ክፍል ሲገባ አንዳንድ ትምህርቶች ከበድ ሊሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን “እኔ ጎበዝ ነኝ፣ ጠንክሬ ካጠናሁ ማንኛውንም ትምህርት መረዳት እችላለሁ” የሚል በራስ መተማመን ሊኖረን ይገባል። ስህተት መሥራት የመማር አካል መሆኑን አውቀን ካልገባን መምህራንን እና ወላጆችን ለመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብንም ይላል ሳይኮሎጂ ቱዴይ ላይ ያገኘነው መረጃ።

ተረት

ቀበሮዋ እና ቆቅ

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ሰፊ ጫካ ውስጥ አንዲት ብልህ ቆቅ እና አንዲት ተንኮለኛ ቀበሮ ይኖሩ ነበር። ቀበሮዋ ሁልጊዜ ቆቋን እንደ ምንም ብላ በልታ ለማደር ታደባታለች።

አንድ ቀን ቀበሮዋ ቆቋን በአንድ ረጅም ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ተቀምጣ አየቻት። ቀበሮዋ ወደ ዛፉ ሥር ተጠግታ በጣፋጭ ድምፅ “ወዳጄ ቆቅ ሆይ! ዜናውን አልሰማሽም እንዴ? ዛሬ በጫካችን ውስጥ በሁሉም እንስሳት መካከል ሰላም ታውጇል። ከእንግዲህ ወዲህ እንስሳት እርስ በእርስ አይበላሉም፤ ሁሉም ወዳጆች ሆነዋል። ስለዚህ ወደ ታች ወርደሽ በእቅፍ ሰላም እንባባል!” አለቻት።

ብልኋ ቆቅ ግን የቀበሮዋ ተንኮል ወዲያው ገባት። ትንሽ ራሷን ቀና አድርጋ ወደ ሩቅ እየተመለከተች “ኧረ አዎ! እውነትሽን ነው! እነሆ ከሩቅ ብዙ የአደን ውሾች እየሮጡ ወደዚህ ይመጣሉ፤ ምናልባት እነሱም ይህን የሰላም ዜና ሰምተው ሊያከብሩ ይሆናል” አለች።

ተንኮለኛዋ ቀበሮ “የአደን ውሾች” የሚለውን ቃል ስትሰማ በድንጋጤ ልቧ ፈራ። ወዲያው እግሬ አውጪኝ ብላ ልትሮጥ ስትል ቆቋ “ወዳጄ ቀበሮ! ወዴት ነው የምትሮጪው? ሰላም ታውጇል አላልሽም እንዴ? ውሾቹን አትፍሪያቸው!” አለቻት።

ቀበሮዋም እየሮጠች “አዎ አልኩኝ… ግን ውሾቹ የሰላሙን አዋጅ አሁኑኑ የሰሙ አይመስለኝም!” ብላ ወደ ጫካው ውስጥ ገብታ ተሰወረች። ተንኮለኛ ሰዎች በውሸት ሊያታልሉን ሲሞክሩ በብልሃት እና በትዕግሥት ማሰብ አደጋን ለማስወገድ ይረዳል።

ምንጭ፡- የሕዝብ

ሞክሩ

  1. ቢመቱት አያለቅስ፣ ቢጥሉት አይሰበርም።
  2. ለመተንፈስ የምንጠቀምበት ዋና ጋዝ ምን ይባላል?
  3. ያለ እጅ ይደበድባል፣ ያለ አፍ ይጮሃል።

 

መልስ

  1. ውኃ
  2. ኦክስጅን
  3. ነጎድጓድ

ነገር በምሳሌ

-«ካለፈው ህይወት የሚማር ብልህ ነው» — ያለፈ ስህተትን ወይም ልምድን ለአሁኑ ህይወት መማሪያ ማድረግ እንዳለብን ያሳያል።

-«ከመካሰስ መወያየት፣ ከጥላቻ መዋደድ ይበልጣል» — ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት መፍታት እና በፍቅር መኖርን የሚያስተምር ነው።

-«ውኃ ሲፈስ ወደ ታች፣ ሰው ሲያስብ ወደ ላይ» — የሰው ልጅ ሁልጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ማሰብ እና መጣጣር እንዳለበት ያሳያል።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here