በኢትዮጵያ ምድር የነሐሴ ጭጋግ ተገፎ የመስከረም ፀሐይ ብቅ ስትል ተፈጥሮ ብቻ ሳትሆን የሰው ልጅ ልቡናም አብሮ የመታደስ እስትንፋስ ይዘራበታል፡፡
መስከረም ሲጠባ አየሩ ደስ ይላል፤ የክረምቱ ድፍርስ ወንዞች ይነጻሉ፤ በየሸለቆው እና በየኮረብታው ላይ ቢጫው አደይ አበባ ፈንድቶ ምድሪቱን በወርቃማ ካባ ይሸፍናታል፡፡ በየደጃፉ ለምለሙ ቄጠማ ይጎዘጎዛል፤ የዕጣን እና የተቆላ ቡና መዓዛ ከመኖሪያ ቤቶች አልፎ መንደሩን ያውደዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን የዘመን መለወጫን ድምቀት የሚያጎላው በልጃገረዶች እና በሕፃናት አንደበት የሚሰማው የዕንቁጣጣሽ ዜማ ነው፡፡
ልጆች “ዕንቁጣጣሽ” እያሉ በዜማ ሲዘምሩ እናት አባቶች ደግሞ በምስጋና ሲመርቁ የሚፈጠረው ድባብ ተራ የበዓል ስሜት አይደለም፡፡ ይልቁንም መላው ማኅበረሰብ ያለፈውን የክረምት ድካም፣ ጭጋግ እና የጨለማ ውጥረት አራግፎ አዲሱን ብርሃን በይፋ የሚቀበልበት ታላቅ የደስታ እና የተስፋ ማዕበል ነው፡፡
በባህል ጥናት (በፎክሎር) እና በባህል አንትሮፖሎጂ ጥናት መሠረት ባህላዊ ማኅበረሰቦች ለጊዜ ያላቸው ግንዛቤ ዘመናዊው ዓለም ከሚረዳበት የተለየ ነው፡፡ በዘመናዊው አስተሳሰብ ጊዜ ወደፊት ብቻ የሚነጉድ መስመራዊ (ቀጥ ያለ) መንገድ ነው፤ በሀገራችን ሀገር በቀል ዕውቀት እና ፎክሎር ውስጥ ግን ጊዜ ራሱን በየወቅቱ እያደሰ የሚመላለስ ክበባዊ (ክብ) ሕያው ክስተት ነው፡፡
የዓለም አቀፍ የባህል እና የፎክሎር ተመራማሪው ቪክቶር ተርነር በማኅበራዊ ሥርዓቶች ውስጥ “የሽግግር ወቅት” የሚለውን ፅንሰ-ሐሳብ ያስቀምጣል፡፡ እንደ ተርነር ማብራሪያ ማኅበረሰቦች ከአንድ የሕይወት ምዕራፍ ወደ ሌላው ሲሸጋገሩ አሮጌውን ማንነት ጥለው አዲሱን የሚላበሱበት ድንበር-አልባ የሽግግር ወቅት አለ፡፡ በኢትዮጵያ ፎክሎር ውስጥ የጳጉሜን ወራት እና የመስከረም ዋዜማ ይህ ድንቅ የመሸጋገሪያ ወቅት ናቸው፡፡
በዚህ ወቅት የሚከናወኑ ባህላዊ እና ፎክሎራዊ ክዋኔዎች በሙሉ ጥልቅ ተምሳሌታዊ ትርጉም አላቸው፦
ችቦ ማብራት፦ እሳት በፎክሎር ውስጥ የመንጻት እና የጨለማ ማሸነፊያ ኃይል ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ችቦ ለኩሶ ሲያበራ፣ አካላዊውን ጨለማ ብቻ ሳይሆን በዓመቱ ውስጥ የነበረውን መከራ፣ ቂም፣ በሽታ እና የልብ ድካም አብሮ በማቃጠል ወደ ብርሃን የመሸጋገሩን ውሳኔ ያውጃል፡፡
የቄጠማ እና የአደይ አበባ ምስጢር፦ ለምለሙ ቄጠማ እና አደይ አበባ ተፈጥሮ ከክረምቱ ሞት እና ጭጋግ ተነሥታ ሕያው የመሆኗ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ አረንጓዴው ሳር የምስራች፣ የዕርቅ እና የበረከት ተምሳሌት ተደርጎ በየቤቱ እና በየደጁ ይነሰነሳል።
የልጃገረዶች እና የወጣቶች ክዋኔ፦ ልጃገረዶች አደይ አበባ ይዘው ከቤት ወደ ቤት ሲዘዋወሩ የሰላም እና የተስፋ መልእክተኞች ሆነው ነው፡፡ ይህ ክዋኔ ማኅበረሰቡን ከአሮጌው የስነ-ልቦና ድባብ አውጥቶ ወደ አዲስ የስሜት ከፍታ ያሸጋግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የባህል ፍልስፍና ውስጥ አዲስ ዓመት ተራ የቁጥር ለውጥ አይደለም፤ ይልቁንም የፍጥረት መታደስ ነው፡፡ በሀገራችን የተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ የሚከበሩ የዘመን መለወጫ እና የወቅቶች ሽግግር በዓላት (እንደ እንቁጣጣሽ፣ እሬቻ፣ ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል፣ ጊፋታ፣ ዮ ማስቃላ እና ሌሎችም) የጋራ አንድ መሠረታዊ ፍልስፍና አላቸው፤ ይኸውም “ከአሮጌው አዙሪት መውጣት እና በንጹሕ ኅሊና ዳግም መወለድ” የሚለው ነው፡፡
በፎክሎር ዕይታ አዲስ ዓመት እውነተኛ የለውጥ መሠረት የሚሆነው በሚከተሉት ሦስት ምሰሶዎች ላይ ስለሚገነባ ነው፦
ሥነ-ምሕዳራዊ ለውጥ፦ ክረምት ተፈጥሮ የምታበቅልበት፣ የምትታገልበት እና ዝናብ የሚዘንብበት ወቅት ነው፡፡ መስከረም ደግሞ ፍሬ የሚታይበት፣ እሸት የሚቀመስበት እና ምድር የምታጌጥበት ወቅት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ውጭ ሕልውና ስለሌለው የተፈጥሮ ለውጥ በቀጥታ የሰውን ውስጣዊ ስነ-ልቦና ይቀይረዋል፡፡
ማኅበራዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ዕርቅ፦ በሀገራችን ፎክሎር ውስጥ ያለ ዕርቅ እና ያለ ይቅርታ አዲስ ዓመትን መቀበል እንደ ኃጢአት እና እንደ ነውር ይቆጠራል፡፡ የተቀያየሙ ወገኖች በአሮጌው ዓመት መጨረሻ ላይ ይቅር እንዲባባሉ፣ አበዳሪ እና ተበዳሪ እንዲግባቡ፣ ጎረቤት ከጎረቤት ሰላም እንዲያወርድ ይደረጋል፡፡ ይህ ማኅበራዊ የመንጻት ሂደት እውነተኛ ለውጥን ይፈጥራል፡፡
ኢኮኖሚያዊ እና የሥራ ተስፋ፦ መስከረም የድካም ፍሬ የሚታይበት፣ የእሸት እና የአዝመራ መሰብሰቢያ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ማኅበረሰቡ ከችግር ወደ ብልጽግና፣ ከእጦት ወደ ሙላት እንዲሸጋገር አዲስ ተነሳሽነት ይፈጥርለታል፡፡
ፕሮፌሰር ፈቃደ አዘዘ “የስነ-ቃል መምሪያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ እና የበዓላት የቃል ግጥሞች ተራ የድምፅ ዜማዎች ሳይሆኑ የማኅበረሰቡ “ተግባራዊ የንግግር ክዋኔዎች” መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
የዘመን መለወጫ ግጥሞች እና ምርቃቶች ማኅበረሰቡ በነገው ሕይወቱ ላይ ሰላምን፣ ጤናን እና ልማትን በቃሉ አማካይነት የሚተነብይባቸው እና በአእምሮው ውስጥ ተጨባጭ የለውጥ ውሳኔ የሚያሳድርባቸው ስነ-ልቦናዊ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ፈቃደ እንደሚያስረዱት የኢትዮጵያ የቃል ስነ-ጽሑፍ ማኅበረሰቡ በዘመን ሽግግር ወቅት ያለፈውን መከራ አራግፎ በአዲስ ስነ-ልቦና እንዲዋቀር የሚያስችል የጋራ ሕክምና (Collective Therapy) ሆኖ ያገለግላል፡፡
አብርሃም ገነት እና የጥናት ባልደረቦቹ እ.ኤ.አ በ2019 በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ_ሰብ ፋኩልቲ አማካይነት ባካሄዱት እና በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሳይንስ ጆርናል በታተመው ጥናት በአባይ ተፋሰስ እና በጣና ሐይቅ ዙሪያ የሚከናወኑ የዘመን መሸጋገሪያ ሥርዓቶችን መርምረዋል፡፡
ይህ ጥናት እንዲህ ይላል፦ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ማኅበረሰቡ በወንዞች ዳርቻ የሚያከናውናቸው የመታጠብ እና የመንጻት ሥርዓቶች ተራ የሰውነት መታጠብ ሳይሆኑ የስነ-ልቦና እና የኅሊና ቁስልን አጥቦ የማስወገድ፣ ያለፈውን ኀጢአት እና በደል የመቅበር እና በአዲስ ሰብዕና የመወለድ ጥልቅ ተምሳሌት አላቸው፡፡ ይህ ክዋኔ ማኅበረሰቡ ለአዲስ የሕይወት ጅምር ራሱን በሙሉ ልብ እንዲያዘጋጅ ያደርገዋል፡፡ የዘመን መንፈስ ሲለወጥ ሰውም አብሮ ይለወጣል።
የዘመን መንፈስ ማለት በአንድ ወቅት ውስጥ የሚኖር ማኅበረሰብ ዓለምን የሚረዳበት፣ የሚያስብበት፣ ስሜቱን የሚገልጽበት እና የጋራ እሴቶቹን የሚመራበት አጠቃላይ የስነ-ልቦና እና የአስተሳሰብ ድባብ ነው፡፡
የዘመን መንፈስ ሳይለወጥ የሚመጣ ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ለውጥ ዘላቂ ሊሆን አይችልም፡፡ አዲስ ዓመት የዘመን መንፈስን ለመቀየር የሚከተሉትን መሠረታዊ ዕድሎች ይዞ ይመጣል፦
የስነ-ልቦና ዳግም ልደት፦ የሰው ልጅ በአሮጌው ዓመት በገጠሙት ውድቀቶች፣ ስህተቶች እና ኀዘኖች ምክንያት ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል፡፡ አዲስ ዓመት ግን “ያለፈው አልፏል፤ ዛሬ አዲስ ቀን ነው፤ እንደገና መጀመር ትችላለህ!” የሚል ተፈጥሯዊ እና ማኅበራዊ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ ይህ ስነ-ልቦናዊ እረፍት ለአዲስ የፈጠራ እና የሥራ ኃይል መነሻ ይሆናል፡፡
አሮጌ አስተሳሰብን መጣል፦ ዘመኑ ሲለወጥ ሰዎች ያረጁ አመለካከቶችን፣ የቂም በቀል አስተሳሰቦችን እና የልማድ እስረኝነትን ጥለው አዳዲስ ዕውቀቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ለመቀበል ዝግጁ ይሆናሉ፡፡
የጋራ ራዕይ መፍጠር፦ የዘመን መንፈስ ሲታደስ፣ የተበታተነው የግለሰቦች ፍላጎት ወደ አንድ ጠንካራ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ አቅጣጫ ይሰበሰባል፡፡
የሀገራችን ሰዎች ይህን አዲስ ዓመት ለእውነተኛ ለውጥ እና ለመሻሻል እንዴት ሊጠቀሙበት ይችላሉ? እባክዎ መውጫ መንገድ አምድን ይመልከቱ?
ማረፊያ
እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሃል እንምነሽነሽ
ዳመናው ይግፈፍ ይውረድ ዥረቱ
ፀሐይዋ ትውጣ ትሙቅ ምድሪቱ
በፀሐይ ሙቀት ትድመቅ አበባ
ጸደይ አማረች መስከረም ጠባ፡፡
ድምጻዊት ዘሪቱ ጌታሁን
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


