“ጻድቅ በደመና”

0
532

በሰሜን ኢትዮጵያ በታሪካዊው የጣና ሐይቅ ላይ ከሚገኙ በርካታ ጥንታውያን እና ቅዱሳን ደሴቶች መካከል የጣና ቂርቆስ አንድነት ገዳም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ይህ ስፍራ ተራ ደሴት ሳይሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የነበረውን የብሉይ ኪዳን ሥርዓት እና ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጣውን የሐዲስ ኪዳን እምነት በጽኑ ገመድ ያስተሳሰረ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ የጎላ አሻራ ያረፈበት ታሪካዊ መዘክር ነው። ገዳሙ ባለፉት ሺህ ዓመታት ውስጥ በሰው ልጅ ታሪክ የተፈራረቁትን ሦስቱን ታላላቅ የሃይማኖት ሕግጋት ማለትም ሕገ ልቡናን፣ ሕገ ኦሪትን እና ሕገ ሐዲስን በተከታታይ ያስተናገደ ብቸኛ እና ምስጉን ቅዱስ ስፍራ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

የዚህ ቅዱስ ስፍራ የታሪክ መሠረት የሚጀምረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3510 እስከ 982 ዓመተ ዓለም በነበረው እና የሰው ልጅ በህሊናው እግዚአብሔርን ያውቅበት በነበረው በሕገ ልቡና ዘመን ነው። በታሪክ መረጃዎች መሠረት ከኖኅ ልጅ ከካም ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ በዚህ ደሴት ላይ የእግዚአብሔር አምልኮና መሥዋዕት ይፈጸም ነበር። ለዚህም እንደ ማረጋገጫ የሚቆጠሩት ጥንታውያን የድንጋይ መሠዊያዎች እና በተለያዩ የብራና መጻሕፍት ላይ የሰፈሩት የታሪክ ምስክርነቶች ዛሬም ድረስ በገዳሙ ውስጥ በህያውነት ይገኛሉ። ይህ የሕገ ልቡና ሥርዓት ቀጥሎ የመጣውን የሕገ ኦሪት ዘመንን ለመቀበል እንደ ትልቅ መነሻ እና መሠረት ሆኖ አገልግሏል።

ከ982 ዓመተ ዓለም እስከ 34 ዓመተ ምሕረት የነበረው ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የሕገ ኦሪት ዘመን ነው። ቀዳማዊ ምኒልክ የአይሁድን ሥርዓት እና ታቦተ ጽዮንን ከኢየሩሳሌም ይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ታቦቱ በቀጥታ ወደ አክሱም ከመሄዱ በፊት በጸጥታው እና በጥበቃው አስተማማኝ በሆነው በዚህ በጣና ቂርቆስ ደሴት ላይ አርፎ ነበር። ታቦተ ጽዮን በደሴቱ ላይ ለ22 ዓመታት ያህል በታላቅ ክብር እና ጥንቃቄ የተቀመጠ ሲሆን ሌዋውያኑ ካህናትም የኦሪቱን መሥዋዕት በዚሁ ስፍራ ያቀርቡ ነበር። ታቦቱ ወደ አክሱም ከተጓዘ በኋላም ቢሆን ስፍራው የኦሪቱ ሥርዓት መፈጸሚያ ሆኖ ለዘመናት ቀጥሏል። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆኑት እና በወቅቱ መሥዋዕት ለማቅረብ ያገለግሉ የነበሩት የብረት እና የናስ ጸናጽል፣ ጥንታውያን መዛግብት፣ የማንኪያ እና የሌዋውያን ልዩ ልዩ መለያ ምልክቶች ዛሬም ድረስ በገዳሙ ሙዚየም ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቀው ለጎብኝዎች እና ለታሪክ ተመራማሪዎች ታላቅ ምስክር ሆነው ያገለግላሉ።

ይህ ስፍራ የብሉይ ኪዳን መዝጊያ ብቻ ሳይሆን የሐዲስ ኪዳን ታሪክ መጀመሪያም ለመሆን በቅቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሕፃንነቱ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅድስት ሰሎሜ እና ከአረጋዊው ዮሴፍ ጋር ከሄሮድስ ሰይፍ ለመሸሽ ወደ ግብፅ እና ወደ ኢትዮጵያ በተሰደደበት ወቅት በጣና ቂርቆስ ደሴት ለረጅም ቀናት አርፏል። እመቤታችን ድንግል ማርያም በዚህ ሰላማዊ ደሴት ላይ ለ3 ወራት ከ10 ቀናት የቆየች ሲሆን በወቅቱም የደሴቱ መኮንን የነበረው ረዶኤት በታመመ ልጁ ምክንያት ቅዱስ ቤተሰቡን በታላቅ አክብሮት እና ፍቅር ተቀብሎ አስተናግዷቸዋል። በዚሁ የቆይታ ወቅትም የጌታችን መለኮታዊ ኃይል የተገለጠባቸው በርካታ ተአምራት ተፈጽመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመኮንኑ ልጅ መፈወስ፣ አጋንንት ከሐይቁ እና ከደሴቱ ተባረው ወደ ማዶ መኮብለላቸው እንዲሁም “ጻድቅ በደመና” ከሚለው ቃል በመነሳት ደሴቱ “ጣና” የሚለውን ስም ማግኘቷን የርእሰ ገዳማት ጣና ቂርቆስ የአባቶች እና እናቶች አንድነት ገዳም አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ምህረት ተናግረዋል።።

በመቀጠልም በ34 ዓመተ ምሕረት የሕንድ እና የኢትዮጵያ ንግሥት የነበረችው ህንደኬ ጃንደረባ (ባኮስ) በኢየሩሳሌም ክርስትናን ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፤ ከዚያ በኋላ የጣና ቂርቆስ ነዋሪዎች የክርስትናን ቃል ቀድመው ከተቀበሉ እና ከተጠመቁ የመጀመሪያዎቹ የሀገሪቱ ማኅበረሰቦች መካከል አንዱ ለመሆን በቅተዋል። ከዘመናት በኋላም በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከታዋቂዎቹ መንታ ነገሥታት ከአብርሃ ወአጽብሃ ጋር በመሆን ወደ ጣና ቂርቆስ መጓዛቸውን ቅዱስ ዮሐንስ አፈዎርቅ “የሐዋርያት ሥራ ትርጓሜ” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። በደሴቱ ላይ የነበረውን የኦሪት መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ በመሻር ወደ ሐዲስ ኪዳን የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ለወጡት፤ በዚህም ስፍራው የክርስትና እምነት ማዕከልነቱ ይበልጥ ጸንቷል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታዋቂ መምህር እና ሰባኪ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ተናግረዋል። ለአማኞቹ ትልቅ መንፈሳዊ እሴት የሆነው የአቡነ ሰላማ መስቀል እና የመጀመሪያው የድንጋይ መንበር አሁንም በገዳሙ ይገኛሉ።

ይህ ገዳም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት የተነሱ ነገሥታት እና መኳንንት ልዩ ትኩረት እና ጥበቃ የሚያደርጉለት ስፍራ ነበር። በተለይም በሀገሪቱ ላይ የተለያዩ የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነቶች በተነሱበት ወቅት መኳንንቱ እና ካህናቱ በአክሱም በጎንደር እና በሌሎች ታላላቅ ከተሞች የሚገኙ ውድ የሆኑ የወርቅ እና የብር ንዋያተ ቅድሳትን፣ የብራና መጻሕፍትን እና የነገሥታትን የዘውድ ቅርሶች ወደዚህ ደሴት በማምጣት ከጥፋት እና ከዘረፋ ይታደጓቸው ነበር። የጣና ሐይቅ ውኃ ለደሴቱ ተፈጥሯዊ ምሽግ በመሆኑ ጠላቶች በቀላሉ ሊደርሱበት እና ሊያጠፉት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ገዳሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የታሪክ ማኅደር እና የሥልጣኔ አሻራ ተደርጎ ይቆጠራል። በውስጡ የሚገኙት ጥንታዊ ሥዕሎች እና የሕንፃ ጥበቦች የኢትዮጵያውያንን የሥነ-ሕንፃና የሥነ-ጥበብ ዕድገት ደረጃ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።

የጣና ቂርቆስ ገዳም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዜማ እና የትርጓሜ ጥናት ማዕከልም ጭምር ነው። በ505 ዓመተ ምሕረት ታላቁ እና መለኮታዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ገዳም መጥቶ ለከምስት ዓመታት ያህል ተቀምጧል። በቆይታውም ለደሴቱ መነኮሳት እና ተማሪዎች ሰፊ የዜማ ትምህርት ሰጥቷል፤ በርካታ ድንቅ የብራና መጻሕፍትንም በዚሁ ስፍራ አዘጋጅቷል። ዛሬም ድረስ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙት የቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ የግል መስቀሉ፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት እና የዜማ ምልክቶች የሀገሪቱን የሥነ-ጽሑፍ እና የሙዚቃ ዕድገት የሚያሳዩ ታላላቅ ቅርሶች ናቸው።

በአሁኑ ዘመን የጣና ቂርቆስ አንድነት ገዳም ከ50 ሄክታር በላይ የቆዳ ስፋት አለው፤ ከ350 በላይ የሚሆኑ መነኮሳት እና የቅዱሳን እናቶች በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት እና ገዳማዊ ሕግ ይኖሩበታል። ገዳሙ የራሱ የሆነ ጠንካራ የትምህርት ማዕከል አለው፤ ይህ ማዕከል በአሁኑ ወቅት የብራና አጻጻፍን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሃይማኖት ትምህርቶችን ለ120 የቤተክርስቲያን ተማሪዎች በነፃ ይሰጣል። በተጨማሪም ገዳሙ በየዓመቱ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ከ500 በላይ እንግዶችን፣ ተሳላሚዎችን እና የታሪክ ተመራማሪዎችን ያስተናግዳል።

ይሁን እንጂ ይህ በታሪክ እና በቅርስ የበለጸገው ጥንታዊ ስፍራ በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ በርካታ ተግዳሮቶች ከፊቱ ተደቅነዋል። ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ የምግብ ዋስትና እጥረት፣ የጣና ሐይቅን እያጠፋ ያለው የእንቦጭ አረም ወረራ፣ የቅዱሳን እናቶች ቤተክርስቲያን ሕንጻ መጎዳት እና ማርጀት፣ ደረጃውን የጠበቀ የቅርስ ማስቀመጫ ሙዚየም አለመኖር፣ አስተማማኝ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ችግር እንዲሁም የባህላዊ ዕደ-ጥበብ ስራዎች መዳከም ናቸው። ጣና ቂርቆስ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የእግዚአብሔር ስም ሳይቋረጥ የተጠራበት፣ የታቦተ ጽዮን የመጀመሪያው ማረፊያ፣ የቅዱስ ቤተሰብ ስደት መጠጊያ እና የቅዱስ ያሬድ የዜማ መፍለቂያ ነው። ይህንን ታሪካዊና መንፈሳዊ የሀገር ሀብት ጠብቆ ለትውልድ ማቆየት የቤተክርስቲያኗ፣ የመንግሥት እና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ርብርብና ትኩረት እንደሚጠይቅ ከገዳሙ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ሳምንቱ በታሪክ

የደርግ አዋጅ

የደርግ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ንጉሠ ነገሥቱን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ያወረደበት እና ሥልጣን መረከቡን ያወጀበት ታሪካዊ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 1/1967) የወጣው መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር። ሆኖም ከዚህ ዋና አዋጅ አስቀድሞ በወሩ መጨረሻ በጳጉሜ 6 ቀን 1966 ዓ.ም  ደርግ ለሕዝብ ባስተላለፈው ይፋዊ የመልካም ምኞት መግለጫ እና የፖለቲካ መልእክት ላይ፦

  • ንጉሡ በበዓሉ ምክንያት ለሕዝብ የሚያደርጉትን ባህላዊ የዘመን መለወጫ ንግግር እንዳያደርጉ አግዶ ነበር።
  • የደርግ አባላት በ1967 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ ለሕዝብ ባስተላለፉት የሬዲዮ መልእክት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በሥልጣን ላይ የሚቆዩበት የመጨረሻው ቀን ዕለቱ ጳጉሜ 6 መሆኑን እና በሚቀጥለው ቀን መስከረም 2 አዲስ የመንግሥት ለውጥ እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል በማለት ፕሮፌስር ባሕሩ ዘውዴ ̋የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here