ዛሬ ተመዝግበን ነገን እንገንባ

0
574

የአማራ ክልል የ2019 በጀት ዓመት የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ18/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም አዲሱን የትምህርት ዘመን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናን መቆየቱን ለአሚኮ  መረጃ መስጠቱ ይታወቃል።በዚህ መሰረት በክልሉ ባሉ ሁሉም ዞንና  ወረዳዎች  የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በደሴ ከተማ መምህር አካለ ወልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ማህነኝ ግርማ ከ11ኛ ክፍል ወደ 12ኛ ክፍል ተዘዋውራ በትምህርት ቤቷ በወቅቱ መመዝገቧን ተናግራለች። ተማሪዋ እንደገለጸችው፣ ትምህርት ቤቱ ባወጣው የመመዝገቢያ ሰሌዳ መሠረት በተቀመጠው ጊዜ መመዝገቧ የትምህርት ጉዞዋን በእርጋታ እንድትጀምር እንደሚያስችላት ገልጻለች።

ማህነኝ እንደገለጸችው፣ በወቅቱ መመዝገቧ ከፍተኛ የአእምሮ እርካታ እንዲሰማኝ አድርጓልም ነው ያለችው። ተማሪዋ ትምህርቷን በተወሰነው ጊዜ መመዝገቧ የወደፊት ዕቅዷን በመተማመን እንድትከታተል እንደሚረዳት ጠቁማለች።

ይህ ተሞክሮ ለሌሎች ተማሪዎችም ጠቃሚ መልዕክት ይዟል። የትምህርት መምሪያዎችና ትምህርት ቤቶች በሚያወጡት የመመዝገቢያ ጊዜና ሰሌዳ መሠረት በወቅቱ መመዝገብ የትምህርት ጉዞን ከመጀመሪያው ማስተካከል የሚያስችል ቀላል ነገር ቢሆንም፣ ያለው ጥቅም ግን ትልቅ መሆኑን ነው የገለጸችው።

ጦርነትና ግጭት በሰዎች ሕይወት ላይ ከሚያስከትሉት ጉዳቶች መካከል አንዱ የትምህርት መቋረጥ  ነው። ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍላቸው ሲርቁና የተማሪነት ሕይወታቸው ሲቋረጥ የወደፊት ሕልማቸውም እንደተዘጋ የሚሰማቸው ብዙዎች ናቸው።

ነገር ግን ትምህርት ቢቋረጥም ሕልም መቋረጥ የለበትም። የተማሪ በላይ አስናቀውታሪክ የሚያሳየውም  ይህንኑ ነዉ ።

በላይ አስናቀው ከቋሪት ወረዳ የመጣ ተማሪ ነው። በአገራዊ ግጭት ምክንያት 11ኛ ክፍል ትምህርቱን ለአንድ ዓመት ለማቋረጥ ተገዶ እንደነበር ተናግሯል። ትምህርት ቤቱ በተፈጠረው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መማር ለመቀጠል እንዳይችል ተዘግቶ ነበር።

ይህ ሁኔታ ግን የበላይን ሕልም አላቆመውም። ከቤተሰቡ ርቆ በሌላ አካባቢ መኖርና መማር እንደሚከብድ ቢያውቅም፣ የወደፊቱን ሕይወት በማሰብ ውሳኔ ወሰነ። ወደ በባህር ዳር በመሄድ ጣና ሐይቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዝግቦ ትምህርቱን ከ11ኛ ክፍል እንደጀመረ ተናግሯል፡፡

“ከቤተሰብ ወጣ ብሎ ለመማር ትንሽ አዲስ ሆኖብኝ ነበር፤ አካባቢውም አዲስ ነው። ነገን ግን  ሕልሜን ማሳካት ስላለብኝ ትምህርቴን ማስቀጠል አለብኝ ብዬ ወሰንኩ” ሲል በላይ ያሳለፈውን ጊዜ ያስታውሳል።በተለይ እናቱ የሰጠችው ማበረታቻ በወቅቱ ትምህርቱን እንደገና ለመጀመር እንደረዳው ይገልጻል።

በባህርዳር ጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአቋረጠበት የክፍል ደረጃ በመመዝገብ በፈተናው የ12ተኛ ክፍል ውጤት 461 ነጥብ አስመዘገበ። አሁንም ወደ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የተሻለ ወደፊት ለመገንባት ተስፋ አለው።

በላይ በራሱ ላይ ያሳለፈውን ተሞክሮ ሲያካፍል፣ “ተማሪዎች ሁሉም ነገር እንደሚያልፍ ማሰብ አለባቸው። ከአሁን በፊት ያመለጡ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን ጥሩ ነገር በማሰብ መጓዝ አለባቸው” ብሏል፡፡

ስለዚህ በግጭት ምክንያት ትምህርታችሁ የተቋረጠ ተማሪዎች፣ የጠፋውን ጊዜ ብቻ አትቁጠሩ፤ የሚቀረውን ጊዜ ተጠቀሙ። እድል ካገኛችሁ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሳችሁ ተመዝገቡ። በሌላ አካባቢ መማር ካስፈለገም አማራጩን ፈልጉ። ዛሬ የምትወስኑት ውሳኔ የነገውን ሕይወታችሁን ሊቀይር ይችላል ሲል ትምህርት ላቋረጡ ተማሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ልባዊ ምክሩን ለግሷል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ2019 ዓ.ም. የተማሪዎች ምዝገባ በተመደበለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን የጣና ሐይቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር ደረጀ ከፋለ ገልጸዋል።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ እንደገለጹት፣ በትምህርት ቤቱ የ2019 ዓ.ም. የተማሪዎች ምዝገባ ለዚህ ተግባር በተመደቡ ቀናትና በተዘጋጀ ፕሮግራም መሠረት እየተከናወነ ይገኛል። በምዝገባውም ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በአላፊ፣ በአቋራጭ እና በመሸኛ የሚመጡ ተማሪዎችን በመለየት ምዝገባው እየተከናወነ ነው።

ትምህርት ቤቱ በ2019 ዓ.ም. 5ሺህ115 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ሲሆን፣ እስካሁን 2ሺህ715 ተማሪዎች መመዝገባቸውን ደረጀ ከፋለ ገልጸዋል። ይህም ከታቀደው የተማሪ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነው በምዝገባ ሂደቱ ውስጥ መካተቱን ያሳያል።

በቀሪዎቹ የምዝገባ ቀናትም የተጀመረውን ሥራ በማጠናከር በዕቅድ የተያዘውን የተማሪ ቁጥር ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ ምክትል ርዕሰ መምህሩ አስታውቀዋል።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ አክለውም ትምህርት ከችግር ወጥቶ ወደ ተስፋ የሚወስድ መንገድ ነው። ስለዚህ የተፈጠረውን የትምህርት ዕድል ማሳለፍ ሳይሆን፣ በወቅቱ በመመዝገብ የትምህርት ጉዞን መቀጠል የተማሪዎች፣ የወላጆችና የመላው ማህበረሰብ የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ ያቋረጡም ሆነ ነባር ተማሪዎች የመመዝገቢያ የጊዜ ሰሌዳው ከመጠናቀቁ በፊት በንቃት እንዲመዘገቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ከ63 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመዝግቧል፡፡

በቀሪ ቀናት የቀሩ ተማሪዎችን  በመመዝገብ የታቀደውን  ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡

ለ2019 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለመመዝገብ ከታቀደው 77 ሺህ 40 ተማሪዎች ውስጥ 63 ሺህ 161 ተማሪዎችን እስካሁን ማስመዝገቡን የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

የደሴ ከተማ የመማር ማስተማር ባለሙያ ኡስማን ጁብሪል እንደገለጹት፣ የተማሪዎች ምዝገባ ከክረምት ሥራዎች ጋር ተያይዞ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኖ ነው የተጀመረው።

በዚህም የመምህራን ዝውውርና የሰው ኃይል ማሟላት፣ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ደረጃ የአመራር ዝግጅት፣ የትምህርት ቤቶች ጥገናና የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት ከተሰሩት ዋና ሥራዎች መካከል ናቸው።

እስካሁን የተመዘገቡት 63 ሺህ 161 ተማሪዎች ከዕቅዱ ከ82 በመቶ በላይ መሆናቸውን አቶ ኡስማን ገልጸዋል። ቀሪዎቹን ተማሪዎች በቀሪ ቀናቶች የምዝገባ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካትም የተቀናጀ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።በተለይም ባለፈው ዓመት ደጋሚ የነበሩ፣ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ የተሸጋገሩ እና ከትምህርት ቤት በመሸኘት የለቀቁ ተማሪዎችን ለይቶ ወደ ትምህርት እንዲመለሱ የማንቀሳቀስ ሥራ እየተሰራ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የተለዩ አቋራጭ ተማሪዎችን በማስተባበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ወደ ትምህርት እንዲመለሱ የማድረግ ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡

በተለይም ከትምህርት የቀሩ ወይም ምዝገባቸውን ያላጠናቀቁ ተማሪዎችን መለየት፣ ማፈላለግና ወደ ትምህርት ቤት መመለስ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት  ገልጸዋል።

ስለዚህ አቋራጭና ደጋሚ ተማሪዎችን ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል አፈላልጎ እንዲማሩና እንዲቀጥሉ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል።እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ፣ የአመራሩና የማኅበረሰቡ ድጋፍ በተጠናከረ መጠን በቀሪዎቹ ቀናት የምዝገባውን ሽፋን 100 በመቶ ማድረስ  ይቻላል ነው ያሉ።

የአማራ ክልል የ2019 በጀት ዓመት የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ18/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአሚኮ የሰጠው መረጃ ያሳይል፡፡ በዚህም አዲሱን የትምህርት ዘመን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየቱም ተነግሯል።

ነሐሴ 14 እና 15 /2018 ዓ.ም በተካሄደ የሙከራ ምዝገባ በ158 ወረዳዎች በሚገኙ 541 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎችን መመዝገብ የተቻለበት ሁኔታ እንደነበርም ተነስቷል።

በዚህ የትምህርት ዘመን በክልሉ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ የታቀደ መኾኑንም ገልጸዋል። በምዝገባው ሂደት ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በቀጣይም የምዝገባ ሂደቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ መስከረም 05/2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ እንደሚጀመር ቢሮው አረጋግጧል።

መረጃ

በግጭት ምክንያት ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ የተስተጓጎለባቸው  አገራት

 

  1. ሱዳን

ከ8 ሚሊዮን በላይ ለትምህርት የደረሱ ልጆች ከትምህርት ውጭ ናቸው። በ2026 መረጃ መሠረት 63% ትምህርት ቤቶች ብቻ እየሰሩ ሲሆን፣ በዳርፉር 81% ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

ምንጭ፡-UNICEF – Sudan Mid-Year Situation Report 2026

  1. ማይያንማር

በቀጣይ ያለው ግጭትና የጸጥታ ችግር ትምህርትን ክፉኛ አስተጓጉሏል። ወደ 3ነጥብ 5 ሚሊዮን ልጆች ከትምህርት ሂደት ውጭ ናቸው።

ምንጭ፡-UNICEF Myanmar – Learning

  1. ጋዛ/የፍልስጤም ግዛት

በ2025 መጨረሻ ሁሉም 637 ሺህ ለትምህርት የደረሱ ልጆች መደበኛ ትምህርት አልነበራቸውም፤ 95ነጥብ 5% የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተጎድተው ወይም ወድመዋል።

ምንጭ፡-UNICEF – State of Palestine, 2025 Year-End Report

ማስታወሻ: እዚህ “ትምህርት ተቋርጧል” ማለት በመላው አገር ሁሉ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል ማለት አይደለም፤ ግጭቱ በተጎዳባቸው አካባቢዎች ትምህርት በከፍተኛ ሁኔታ ተቋርጧል ወይም ተስተጓጉሏል ማለት ነው።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here