የነገ አዙሪቱን ስበሩት

0
82

“አዲሱ ዓመት ሲጠባ ሲጋራ ማጨስ አቆማለሁ፤ በሚቀጥለው ሰኞ ጂም እጀምራለሁ፤ ደመወዝ ሲጨመርልኝ ገንዘብ መቆጠብ እጀምራለሁ፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ መጽሐፍ ማንበብ እጀምራለሁ…” ብላችሁ ታውቃላችሁ?

ይህ አባባል በሀገራችን ማኅበረሰብ ውስጥ እጅግ የተለመደ በየጓዳው እና በየሻይ ቤቱ የሚደመጥ የዘወትር ዜማ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ለመለወጥ ውጫዊ መነሻ ምክንያት ይፈልጋል፤ ለውጡን ከቀን መቁጠሪያ ቅያሪ፣ ከሳምንቱ መጀመሪያ ወይም ከገንዘብ መገኘት ጋር ያቆራኘዋል፡፡

መስከረም ሲጠባ ወይም አዲስ ዓመት ሲመጣ በከፍተኛ ስሜት ይነሳሳል፤ “ዘንድሮ ህይወቴን እቀይራለሁ!” ብሎ ይምላል፡፡

ይሁን እንጂ ጥቂት ሳምንታት እንኳ ሳይዘልቁ የጋለው ስሜት ይቀዘቅዛል፤ ሰውየው ቀስ በቀስ ወደ ቀደመው ጎጂ ልማዱ ይመለሳል፡፡ ከዚያስ? ጥልቅ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት፣ የተስፋ መቁረጥ ቁስል እና ራስን የመውቀስ ሰበብ ይከተላል፡፡

“ዘንድሮ ሁኔታዎች አልተመቻቹልኝም፤ በሚቀጥለው ዓመት ግን በእርግጠኝነት እለወጣለሁ” በሚል ሌላ ሰበብ ራሱን ያጽናናል፡፡ በዚህ ዓይነት አዙሪት ውስጥ እየተሽከረከሩ ህይወታቸውን ሙሉ “ለመለወጥ የሚመኙ” ነገር ግን በተግባር አንድም እርምጃ የማይራመዱ የነገ እስረኞች ሆነው የሚያልፉ ስንቶች ናቸው?

የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች፣ የባህርይ ኢኮኖሚክስ ሊቃውንት እና የስኬት ባለቤቶች ይህን አደገኛ አዙሪት እንዴት ያዩታል? የሰው ልጅ ከዚህ የስነ-ልቦና ወጥመድ ወጥቶ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው? ዓለም አቀፍ ጥናቶች እና ሳይንሳዊ ግኝቶች የሚሰጡንን ወሳኝ ትምህርቶች እንመልከት፡፡

የማዘግየት ስነ-ልቦናዊ ምስጢር፦ ለምንድን ነው ለመለወጥ የምንቸገረው?

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለውጥን ይፈራል፤ የአእምሯችን አሠራር ሁልጊዜም ኃይልን ለመቆጠብ እና ቀላሉን መንገድ ለመከተል የተቃኘ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ሰዎችን በምኞት አዙሪት ውስጥ የሚያስቀሯቸው ሦስት መሠረታዊ የስነ-ልቦና ምክንያቶች አሉ፦

  1. የሐሰተኛ ተስፋ ሲንድሮም

በካናዳ የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች የሆኑት ጃኔት ፖሊቪ እና ፒተር ሄርማን ያካሄዱት ጥናት እንደሚያሳየው ሰዎች በአዲስ ዓመት ወይም በልዩ ቀናት የሚያቅዷቸው ዕቅዶች የሚፈርሱት ግባቸውን ከልክ በላይ አግዝፈው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተአምር ስለሚጠብቁ ነው፡፡ ተመራማሪዎቹ ይህን ሁኔታ “የሐሰተኛ ተስፋ ሲንድሮም” ይሉታል፡፡ ሰዎች ግቡን ሲያቅዱ የሚሰማቸው ደስታ ከፍተኛ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩ የሚጠይቀውን እውነተኛ መስዋዕትነት ሲጋፈጡ ወዲያውኑ እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡

  1. የአሁን ጊዜ ዝንባሌ

የኖቤል ተሸላሚው የስነ-ልቦና ባለሙያ ዳንኤል ካህነማን“ቲንኪንግ ፋስት ኤንድ ስሎው” በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፋቸው እንዳስረዱት የሰው ልጅ አእምሮ ከሩቁ የወደፊት ጥቅም ይልቅ ለቅርቡ ጊዜያዊ እርካታ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ፦ አእምሯችን ከ10 ዓመት በኋላ የሚገኘውን ጤናማ ሰውነት ከማሰብ ይልቅ አሁን በአፉ ውስጥ የሚቀመጠውን ጣፋጭ ኬክ ወይም የሲጋራ ጢስ ፈጣን እርካታ ይመርጣል፡፡ ይህ ዝንባሌ ሰዎችን “ዛሬ ልደሰትበት፤ ነገ እጀምራለሁ” ወደሚል የማያባራ ማዘግየት ይወስዳቸዋል፡፡

  1. የንጹሕ ጅምር ቅዠት

በፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ የዋርተን ቢዝነስ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ካትሪን ሚልክማን እና ባልደረቦቿ ያጠኑት “ዘ ፍሬሽ ስታርት ኢፌክት” የተሰኘው ጥናት እንደሚያስረዳው አዲስ ዓመት ወይም አዲስ ወር ለሰዎች የመነሳሳት ስሜት ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ ጥናቱ አበክሮ እንደሚያስጠነቅቀው ይህ ስሜት የሚቆየው ለጥቂት ቀናት ብቻ ነው፡፡ ስሜቱ ሲበርድ አብሮ የሚቀጥል ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት (ሲስተም) ካልተገነባ ግለሰቡ ወደ ቀድሞ ልማዱ መመለሱ የማይቀር ነው፡፡

ዘላቂ ለውጥ በባዶ ስሜት ወይም በምኞት አይገነባም፤ ይልቁንም በልማድ ሳይንስ ላይ ይመሠረታል፡፡ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀየረው ጄምስ ክሌር  “አቶሚክ ሀቢትስ” በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “አንተ ወደ ግቦችህ ከፍታ አትወጣም፤ ይልቁንም ወደ ዘረጋኸው የአሠራር ሥርዓት ዝቅታ ትወድቃለህ፡፡”

ክሌር እንደሚያስረዳው ሰዎች የሚወድቁት ትልቅ ህልም ስለሌላቸው ሳይሆን ህልማቸውን የሚሸከም ዕለታዊ ሥርዓት ስለሌላቸው ነው፡፡ ለውጥ ማለት በአንድ ጀምበር 180 ዲግሪ መዞር ሳይሆን በየቀኑ የአንድ በመቶ መሻሻል ማምጣት ነው፡፡ በየቀኑ አንድ በመቶ የተሻሻለ ሰው በአንድ ዓመት ውስጥ በ37 እጥፍ የተሻለ ማንነትን ይገነባል፡፡

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቢ.ጄ. ፎግ “ቲኒ ሃቢትስ” በተሰኘው ምርምራቸው ለውጥን ለመጀመር ትልቁ ስህተት ሥራውን አክብዶ መጀመር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ፎግ እንዳረጋገጡት አዲስ ልማድ ለመጀመር ተግባሩን እጅግ አሳንሶ ወደ ሁለት ደቂቃ ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፦ በቀን አንድ ሰዓት መጽሐፍ ለማንበብ ከማቀድ ይልቅ፣ በቀን አንድ ገጽ ብቻ በማንበብ መጀመር አእምሮ በቀላሉ እንዲላመደው ያደርጋል፡፡

ከዘለዓለማዊ ምኞት ወጥተው እውነተኛ የሕይወት ለውጥ ለማምጣት የሚከተሉትን አራት ሳይንሳዊ እርምጃዎች ዛሬውኑ ይተግብሩ፦

  1. የማንነት ለውጥ ላይ አትኩሩ

ግብዎ “መጽሐፍ ማንበብ” ሳይሆን “አንባቢ መሆን” ይሁን፤ ግብዎ “ሲጋራ ማቆም” ሳይሆን “ለጤናው የሚጠነቀቅ ሰው መሆን” ይሁን፡፡ አንድ ሰው ሲጋራ ሲያቀርብልዎ “ለማቆም እየሞከርኩ ነው” ከማለት ይልቅ “እኔ አላጨስም” ብለው ይመልሱ፡፡ ማንነትዎን ከቀየሩ ተግባርዎ ማንነትዎን መከተሉ አይቀርም፡፡

  1. የሁለት ደቂቃውን ሕግ ተግብሩ

ማንኛውንም አዲስ ልማድ በሁለት ደቂቃ ውስጥ በሚጠናቀቅ መልኩ ጀምሩ፦

  • በቀን 10 ኪሎ ሜትር መሮጥ ሳይሆን የስፖርት ጫማዎን አድርገው ደጃፍ መውጣት፤
  • ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሳይሆን የመጽሐፉን አንድ ገጽ ማንበብ፤
  • ሁሉንም ዕዳ በአንድ ጊዜ መክፈል ሳይሆን በቀን 10 ብር መቆጠብ ይሁን፡፡

መጀመሪያ ልማዱን ማጽናት ያስፈልጋል፤ ማሻሻልና ማሳደግ የሚመጣው ከጸና በኋላ ነው፡፡

  1. አካባቢዎን ለስኬት በሚያመች መልኩ ቅረጹ

የሰው ልጅ የፍላጎቱ ሳይሆን የአካባቢው ውጤት ነው፡፡ ሲጋራ ማቆም ከፈለጉ ሲጋራ የሚያጨሱ ጓደኞችን ይቀንሱ፤ ፓኬቱን ከቤትዎ ያስወግዱ፡፡ ገንዘብ መቆጠብ ከፈለጉ የባንክ መተግበሪያዎን በቀላሉ እንዳይከፈት ያድርጉ፤ ወጪ የሚጠይቁ ቦታዎችን አያዘውትሩ፡፡ መጽሐፍ ማንበብ ከፈለጉ መጽሐፉን ከትራስዎ አጠገብ ያስቀምጡ፡፡ ጥሩውን ልማድ ቀላል እና የሚታይ፣ መጥፎውን ልማድ ደግሞ ከባድ እና የማይታይ ያድርጉት፡፡

  1. “በተከታታይ ሁለት ቀን አታቋርጥ” የሚለውን ሕግ ያክብሩ

ፍጹም ሰው የለም፤ አንድ ቀን ስንፍና ሊያጠቃዎት ወይም ባልታሰበ ምክንያት ያቀዱትን ሳያደርጉ ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ቁምነገር ስህተቱ ሲፈጠር ራስን መውቀስ ሳይሆን ወዲያውኑ ወደ መስመር መመለስ ነው፡፡ አንድ ቀን ልምምድ ቢያመልጥዎት እንኳን በሁለተኛው ቀን በምንም ዓይነት ሁኔታ እንዳያመልጥዎ ያድርጉ፡፡ ሰንሰለቱ አንድ ጊዜ ቢበጠስ አደጋ የለውም፤ ሁለት ጊዜ ከተበጠሰ ግን አዲስ መጥፎ ልማድ መፈጠሩ ነው፡፡

አዲስ ዓመት፣ አዲስ ወር ወይም ሰኞ የሚባሉ ቀናት በራሳቸው ምንም ዓይነት አስማታዊ ኃይል የላቸውም፡፡ የቀን መቁጠሪያው ላይ ያለው ቁጥር ይቀየራል እንጂ፤ እርስዎ አሮጌውን አስተሳሰብ፣ ያረጀውን ሰበብ እና የስንፍና ልማድ እስካልቀየሩ ድረስ ሕይወትዎ በነበረበት ነው የሚቀጥለው፡፡

“ገንዘብ ሳገኝ እለወጣለሁ፤ በሚቀጥለው ዓመት እጀምራለሁ” የሚለው ማታለያ የነገ እስረኛ የሚያደርግ የሰነፎች መጠጊያ ነው፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሚጀምረው ሁኔታዎች ሲመቻቹ ሳይሆን ባልተመቹ ሁኔታዎች ውስጥ አነስተኛ እርምጃዎችን በጽናት መውሰድ ሲቻል ነው፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጳጉሜ 2  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here