አዲሱ የገጠር መሬት አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

0
82

መሬት ለሰው ልጆች ሕልውና፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ መሬት ሰብል ለማምረት፣ እንስሳትን ለማሰማራት እና ለምግብ ዋስትና መሠረት ነው። ለመኖሪያ እና ለመሠረተ ልማት ለሚውሉ  ለቤት፣ ለትምህርት ቤት፣ ለጤና ተቋማት፣  ለመንገድ ግንባታ ምትክ የሌለው ተፈጥሯዊ ስጦታም ነው።

በኢኮኖሚው  ዘርፍም  ጠቀሜታው  የጎላ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ፣ ለማዕድን ፍለጋ እና ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ይውላል። ለውኃ ሀብት መያዣነት እና የተለያዩ እንስሳት መኖሪያም ነው።

ለሰው ልጅ መኖሪያነትን ጨምሮ በርካታ ገፀ – በረከት የተጎናፀፈው መሬት በሕግ እና ሥርአት  መመራት  ይገበዋል፡፡ ይህን ውድ ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደርም መንግሥት ሕግና ሥርዓት አውጥቶ በአግባቡ አያስተዳደረው ይገኛል፤ አሠራሩንም በየወቅቱ እያሻሻለ ነው፡፡

በቅርቡም አማራ ክልል የገጠር መሬት አዋጅን አሻሽሏል፡፡

የክልሉ መሬት ቢሮ አዲሱን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ አስመልክቶ ጥር 04 ቀን 2018 ዓ.ም የሰጠውን መግለጫ በኵር በምጣኔ ሀብት አምዷ መሬት  ለኢኮኖሚው ያለውን ፋይዳ ትኩረት በማድረግ መዘገቧ ይታወሳል፡፡ አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ የመሬትን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እና ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለውም በመግለጫው ተመላክቷል። አዋጁ ለመሬት ባለይዞታዎች ጠቃሚ መብቶችን ይዞ የመጣ መሆኑን የክልሉ መሬት ቢሮ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን ተጠቅሞ የቀደመውን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/1997 በ2016 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 1324/2016 አሻሽሎታል። የክልሉ ሕግ ከፌዴራሉ አዋጅ ጋር መጣጣም ስላለበት የቀደመውን አዋጅ ቁጥር 252/2009 ማሻሻል አስፈላጊ ሆኗል።

በተጨማሪም የክልሉን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የገጠር መሬት ባለይዞታዎችን መብት ለማስፋትና ለአጠቃላይ ዕድገት ሲባል  የአማራ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ በአዲስ ተሻሽሏል።

ይህ የሆነውም በሀገሪቱ በነበረው የገጠር መሬት አሥተዳደር ሥርዓት እና የሕግ ማዕቀፎች ውስንነት ምክንያት  መሠረታዊ ሀብቱ ዘላቂነት ያለው አያያዝ፣ አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓት ተበጅቶለት በጥንቃቄ ባለመመራቱ ለግጭት፣ ለክርክር፣ ለውዝግብ፣ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች መነሻ ሆኖ ቆይቷል።

ጠንካራ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓት መኖር ለሰላም መስፈን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለገጠሩም ሆነ ለከተማው ማኅበረሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል።

ይህን መሠረት በማድረግም የክልሉ ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፤ 5ኛ ዓመት፤ 11ኛ መደበኛ ጉባኤው የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ማሻሻያ አዋጅን አጽድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ተጠቁሟል።

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት መሬት የማን ነው? በማለት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመሬት ቢሮ የሕግ ባለሙያ አቶ አዲሱ ወላን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የመሬት ባለቤትነት በሕገ – መንግሥቱና በገጠር መሬት ሕጉ መሠረት የመሬት ባለቤትነት የሕዝብና የመንግሥት ነው። የመሬት ባለይዞታነት ደግሞ በሦስት ይከፈላል፤  የግል፣ መንግሥት እና የጋራ (የወል) ይዞታ በሚል፡፡

የግል ይዞታ በአርሶ አደሮች ወይም በገጠር ነዋሪዎች እጅ ያለመሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው የመንግሥት ይዞታ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት፣ በወንዞችና ሐይቆች ዳርቻዎች እንዲሁም ጥቅም ላይ ያልዋለ መሬትን ይሸፍናል።

የጋራ (የወል) ይዞታ መሬት የሚባለው ደግሞ  በአርብቶ አደሮች ወይም በአርሶ አደሮች ሳይከፋፈሉ በጋራ የሚጠቀሙበት መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ አዲሱ የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 310/2016 ለባለይዞታዎች ሰፊ መብቶችን ሰጥቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል መሬትን ማከራየት፣ በስጦታ ወይም በውርስ ማስተላለፍ፣ በመሬቱ ላይ ያፈሩትን ንብረት (ቋሚ ተክል ወይም ቤት) የመሸጥ መብት ይገኙበታል፡፡

ነገር ግን ይህ መብት በመሬት አጠቃቀም ዕቅድ (ፕላን) መሠረት ለምተው በተገነቡ ንብረቶች ላይ ብቻ ነው የሚፈቀደው።

መሬትን ከተሸጋሸገ ወይም ከተመጣጠነ ሌላ አርሶ አደር ጋር መለዋወጥ፣ የገጠር መሬት ይዞታን በማስያዝ ወይም በዋስትና በማስቀመጥ ከብድር ተቋማት ገንዘብ መበደር ይችላሉ።

አዋጁ በተለይ የሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችንና ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን መብት በግልጽ ያከበረና የጠበቀ ነው። በተጨማሪም ባለይዞታዎች መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸው፣ መሬቱን ያለአግባብ መጠቀም ወይም ሕግ መጣስ በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመወል፡፡

አዲስ የተሻሻላ የገጠርና የከተማ መሬት አስተዳደር ወሰን ላይ ይፈጠሩ የነበሩ ግራ መጋባቶችን ለመቅረፍ እንዲቻል፣ የገጠር መሬት ይዞታን ምንነትና የሚገኝበትን አስተዳደራዊ ወሰን በማያሻማ ሁኔታ ይገልጻል።

አዋጁ   መሬት የማግኘት መብትና ተጠቃሚነት (አንቀጽ 4-8)በተመለከተ፡-

በግብርና መተዳደር የሚፈልግ የክልሉ ነዋሪ (ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ) መሬት በነፃ የማግኘት መብት አለው። ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካላት ደግሞ ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ወጣቶች ልዩ ትኩረትና የቅድሚያ መብት ይሰጣቸዋል።

የይዞታ ቦታ የመብት ቆይታን በተመለከተም አዋጁ የአርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና የሃይማኖት ተቋማት መብት የጊዜ ገደብ የሌለው (ለዘላለም) ነው። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግን ለሥራቸው አስፈላጊ እስከሆነ ጊዜ ብቻ ይፈቀድላቸዋል።

ኪራይን አስመልክቶ አዋጁ (አንቀጽ 9) ባለይዞታው ከግማሽ የማይበልጥ ይዞታውን ማከራየት ይችላል። (አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ግን ሙሉውን ማከራየት ይችላሉ)። የጊዜ ገደብ ለቋሚ ተክል እስከ 30 ዓመት እንዲሁም  ለሰብል እስከ 10 ዓመት ማከራየት ይቻላል።

ለሥጋ ዘመድ ወይም በ”ይጦረኛል” ውል ለማንኛውም ሰው በጽሑፍ መስጠት እንደሚቻልም (በአንቀጽ 11) ሰፍሯል። (አንቀጽ 12) ማንኛውም ሰው (የመንግሥት ሠራተኛን ጨምሮ) በኑዛዜ ወይም ያለኑዛዜ በፍትሐ ብሔር ሕጉ መሠረት መሬት መውረስ እንደሚችል ተመላክቷል። ይህም ቀደም ሲል የነበረውን ገደብ ያነሳ ትልቅ ለውጥ ነው።

በመሬት ላይ የለማን ቋሚ ንብረት (ቤት ወይም ቋሚ ተክል) መሸጥ ይቻላል። ቋሚ ተክል ከሆነ ሙሉ በሙሉ ከለማ ግማሹን፣ በከፊል ከለማ ግን የለማውን ማሳ መሸጥ ይፈቀዳል።

አዲሱ አዋጅ ባለይዞታው የመጠቀም መብቱን እንደ ካፒታል በመጠቀም ከባለሀብት ጋር ማልማት፣ የመሬት የመጠቀም መብትን ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስትና የማስያዝ መብትን ሰጥቷል፡፡ የዋስትና ዘመኑ ቢበዛ እስከ 10 ዓመት ይቆያል። ተበዳሪው ካልከፈለ ግን አበዳሪው መሬቱን ለተወሰነ ጊዜ በመጠቀም ዕዳውን ያስመልሳል።

የመሬት መረጃ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ በዲጂታል ሥርዓት መመራት እንዳለበት በአስገዳጅነት በአዋጁ ተደንግጓል። የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመሬት ላይ ያለን መብት የሚያረጋግጥ “የመጨረሻና ፍጹም” ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል።

የይዞታ ክስ ይርጋ መሬት ያለአግባብ የተወሰደበት ሰው በ15 ዓመት ውስጥ ክስ ማቅረብ አለበት (ቀደም ሲል 10 ዓመት የነበረው መሻሻሉን ልብ ይሏል)። የወርሻ ይርጋ ውርሱ ከተከፈተ ደግሞ  በሦስት ዓመት ውስጥ መጠየቅ አለበት።

አዋጁ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችና ሽምግልና እንደ አማራጭ የመፍትሔ መንገድ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ከአንድ ባል ከአንድ በላይ ሚስት በሚኖረው ጊዜ የሴቶችን መብት ለመጠበቅ ሲባል የጋራ መሬቱ ተከፋፍሎ በየስማቸው እንዲመዘገብና ባልየው አዲስ በሚመሠርተው ትዳር ላይ በራሱ ድርሻ ላይ ብቻ እንዲመዘገብም ደንግጓል።

የአጠቃቀም ገደቦችና ግዴታዎች (አንቀጽ 33 – 35) በተመለከተ ባለይዞታው መሬትን የመንከባከብና የአፈር መሸርሸርን የመከላከል ግዴታ ተጥሏል። ተዳፋትነቱ ከ60 በመቶ በላይ የሆነ መሬት ለሰብል እርሻ ሳይሆን ለዛፍ ልማት ብቻ መዋል አለበት። ግዴታን አለመወጣትም ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ የመጠቀም መብትን እስከ ማጣት የሚያደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደ ሚያስከትል አዋጁ አስፍሯል።

 

 

መረጃ

የይርጋ ምንነት እና ዓላማዎቹ

በሕግ ይርጋ ማለት አንድ መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካበት ሰው ጥያቄውን ወይም ክሱን በሕግ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳያቀርብ ሲቀር መብቱ በጊዜ እዳሪነት ቀሪ የሚሆንበት (የሚታገድበት) የጊዜ ገደብ ነው።

የይርጋ  ዋና ዋና ዓላማዎች

  • ንቁነትን ማበረታታት፡- ከሳሽ በተገቢ ትጋት መብቱን በወቅቱ እንዲጠይቅ ለማድረግ።
  • ማስረጃ እንዳይጠፋ መከላከል፡- ተከሳሽ በጣም ዘግይተው በሚቀርቡ ክሶች ምክንያት መከላከያ ማስረጃዎችን እንዳያጣ ለመርዳት።
  • የፍትሕ አሰጣጥን ማስተካከል፡- እጅግ ዘግይተው የሚቀርቡ አቤቱታዎች ፍትሕ ከማስገኘት ይልቅ ማጥቂያ መሳሪያ እንዳይሆኑ ለመከላከል።

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here