“ግእዝ የአባቶቻችን የጥበብና የታሪክ መዝገብ ነው”

0
75

“የወደብ አልባነት ዳፋ የእያንዳንዱን ዜጋ ቤት ያንኳኳል”

‎መምህር ይበልጣል ዘውዱ ቁምላቸው ከምሥራቅ ጎጃም ባሶ ሊበን ወረዳ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ተወልደው የአንደኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርታቸውን በአካባቢያቸው ካጠናቀቁ በኋላ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ሀብትና መስኖ ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል። ከአጭር የሥራ ፍለጋ ጊዜ በኋላ በመስኖ መሐንዲስነት ሥራቸውን ጀምረው፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኑ።

በትምህርታቸው በመቀጠል በ2013 ዓ.ም. ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ ሃይድሮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በማስተማር፣ በምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት እያገለገሉ ይገኛሉ።

ከሙያቸው በተጨማሪ  በቅርቡ  “ኆኅተ ግእዝ ቁጥር 2” መጽሐፋቸውን አስመርቀዋል፡፡ ከመምህር ይበልጣል ጋር በመጽሐፎቻቸው እና ሌሎችም ጉዳዮች  ቆይታ አድርገናል፡፡

መልካም ንባብ!

 

ከግእዝ ቋንቋ ጋር ያለዎት ጉዞ እንዴት ተጀመረ?

ከግእዝ ቋንቋ ጋር ያለኝ ይፋዊ ጉዞ የጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም ፍላጎቱ ያደረብን የግቢ ጉባኤ ትምህርት እየተማርሁ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰሚ ካጡ ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል አንዱ ግእዝ መሆኑ ውስጤን እንደ እሳት ያቃጥለው ነበር፡፡

በ2011 ዓ.ም ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከባለቤቴ ጋር ከመጣሁ በኋላ፤ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለማስተርስ ትምህርት ከመጣ አንድ ወንድሜ ጋር “ለምን የንግድ ሥራ አንጀምርም?” ብለን መወያየት ጀመርን፡፡ በዚህ ጊዜ ባለቤቴ “ ለምን ለወገን፣ ለሀገር፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ታሪክ ያለው ነገር አንሠራም?” የሚል ድንቅ ሐሳብ አቀረበች፡፡ እኛም በሐሳቧ ተስማምተን የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር ወሰንን፡፡

ከዚያም ታላቁን ሊቅ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክን ጠየቅናቸው፤ እርሳቸውም ፈቃደኛ ሆነው በትንሣኤ ግእዝ የግእዝ ቋንቋ ማሰልጠኛ ተቋም ትምህርቱ ተጀመረ፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ እኔም የግእዝ ትምህርቴን ጀመርሁ፤ ይህም የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ማለት ነው፡፡ በአንድ በኩል የማስተርስ ትምህርቴን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግእዝ ቋንቋ ትምህርቴን እያጠናሁ ፍቅሬን በመጽሐፍ ወደሚዳሰስ ፍሬ ለወጥሁት፡፡

 

ግእዝን ለመማርና ለማስተማር ያነሳሳዎት ዋና ምክንያት ምንድን ነው?

ግእዝ የኢትዮጵያ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሕክምና፣ የሥነ ክዋክብትና የሥነ ጽሑፍ ቤተ መዛግብት ነው፡፡ የጥበብ መክፈቻ ቁልፍ ወይም መርኆ ነው፡፡ አባቶቻችን በግእዝ ቋንቋ ቁልፍነት የዘጉትን ጥበብ ሳይበረዝ ለትውልድ ለማስተላለፍና ከውስጡ ያለውን ፍሬ ለመመገብ ቋንቋውን መማርና ማስተማር የግድ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

ሌላው ምክንያት፤ አብዛኛው ሰው የግእዝ ቋንቋን ሩቅ፣ ውስብስብ፣ ለመማር የማይቻልና የቄስ ትምህርት ብቻ አድርጎ ያስባል፡፡ይህንን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቀየር ግእዝን በቀላሉ መማር እንደሚቻል በተግባር ማሳየት ፈለግሁ፡፡ በተጨማሪም የጥንት ደራሲያን ጦርነት ለግእዝ ቋንቋ መዳከም ምክንያት እንደነበር ከመምህሮቼ በመስማቴ፤ “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ በጽሑፍ ሥራ ለመመከት ተነሣሣሁ፡፡

 

“ኆኅተ ግእዝ” የተሰኘውን ሁለተኛ መጽሐፍ እንዲጽፉ ያነሳሳዎት ምንድን ነው?

የመጀመሪያው መጽሐፌ ታትሞ ለሕዝብ ከደረሰ በኋላ ከአንባብያንና ከቋንቋ አፍቃሪያን ያገኘሁት አዎንታዊ ምላሽና ጥልቅ ፍላጎት ትልቅ ብርታት ሆነኝ፡፡

በተጨማሪም በመጀመሪያው መጽሐፍ ያልተሸፈኑ ጥልቅ የሰዋስው ሕጎችን፣ ለአንባብያን በሚገባ ግልጽ በሆነ መንገድ የቀረቡ የቃላት አጠቃቀሞችን፣ በተግባር የተደገፉ የልምምድ ጥያቄዎችን ከነመልሶቻቸው፣ እንቆቅልሾችን፣ ንግግሮችንና የዘጠኙን ፊደላት ምሥጢር በጥልቀት አካትቶ ሁለተኛውን መጽሐፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ይኸውም “ኆኅተ ግእዝ ቁጥር 2”ን እንድወልድ አበቃኝ፡፡

 

“ኆኅተ ግእዝ” የሚለው ርእስ ምን ያመለክታል? ርእሱን ሲመርጡ ምን አስበው ነው?

“ኆኅት” ማለት በር፣ መግቢያ ወይም ደጃፍ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ “ኆኅተ ግእዝ” ማለት የግእዝ ቋንቋ መግቢያ በር ማለት ይሆናል፡፡

የግእዝ ቋንቋ የዜማ፣ የአቋቋም፣ የድጓ፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ፣ የጥበብ፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የመድኃኒት ቅመማና የሥነ ሕንፃ መግቢያ ቁልፍ ነው፡፡ አንባብያን ይህን መጽሐፍ ሲከፍቱ ወደ ጥንታዊው፣ ታሪካዊው፣ ምሥጢራዊው እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ የዕውቀትና የጥበብ መንደር የሚገቡበትን ቁልፍ በእጃቸው እንደያዙ እንዲሰማቸው በማሰብ ርእሱን “ኆኅተ ግእዝ” አልሁት፡፡

 

ይህ ሁለተኛ መጽሐፍ ከመጀመሪያው መጽሐፍዎ በምን ይለያል? ለአንባቢው የሚያመጣው አዲስ ነገር ምንድን ነው?

ዋናው ልዩነት ይዘቱ ከ200 ገጽ ወደ 500 ገጽ ማደጉ ነው፡፡ መጽሐፉ በርካታ አዳዲስ ይዘቶችን አካቷል፤ ከእነዚህም መካከ  የግእዝ ፊደላትና አኃዛት አመጣጥ፤ ለምን ሰባት እንደሆኑ እና የሰው ልጅ ለምን ፊደል እንደተሰጠው የሚያትት ትንታኔ፣የዘጠኙ ፊደላት ምሥጢርና በሥርዓተ ጽሕፈት ላይ ያላቸው ተጽዕኖ በምሳሌ ተደግፎ መተንተኑ፣የግእዝ አኃዛት ደረጃ በደረጃ ተቀምጠው በአራቱ የሒሳብ ስሌቶች (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት፣ ማካፈል) በተግባር መሠራታቸው፣ እንቆቅልሽ፣ ንግግር፣ ደብዳቤ አጻጻፍ፣ የግል ታሪክ አጻጻፍና ሥርዓተ ንባብ በስፋት መካተታቸው፣ የተለያዩ የቤት፣ የበረሃና የዱር እንስሳት ስሞች መጠቀሳቸው፣የተለየ የግስ ርባታ ጠባይ ያላቸው ግሶች ተለይተው መቅረባቸው፣ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የልምምድ ጥያቄዎች ከነመልሶቻቸው መካተታቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

 

መጽሐፉ በተለይ ለማን ተዘጋጅቷል? አንባቢው ካጠናው በኋላ ምን ዓይነት አቀባበል አግኝቷል?

መጽፉ የተዘጋጀው፦ከመጀመሪያው አንሥቶ የግእዝ ቋንቋን ለማወቅ ፍላጎት ላለው ማንኛውም ሰው፣  ከኪንደርጋርተን እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ የአስኳላ ተማሪዎች፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለአብነት ተማሪዎችና ለመምህራን፣ለማንኛውም ኢትዮጵያዊና የግእዝ ቋንቋ አፍቃሪ ለሆኑ የውጭ ዜጎች ሁሉ ነው፡፡

ከአንባብያንና ከተማሪዎች ያገኘሁት ምላሽ እጅግ በጣም የሚያበረታታ ነው፡፡ አቀራረቡ ግልጽ፣ በማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚረዳና ሸክም የማይሆን የቀለለ የቃላት አጠቃቀም ያለው መሆኑን ገልጸውልኛል፡፡

 

መጽሐፉን “የግእዝ መማሪያና ማስተማሪያ” በማለት ገልጸውታል። መማርንና ማስተማርን በመጽሐፉ እንዴት አጣምረዋል?

መጽሐፉ በሁለት መንገድ እንዲያገለግል ሆኖ ነው የተቀረጸው፤  ለመማሪያነት እንዲሁም ለማስተማሪያነት፡፡

ማንኛውም ሰው ያለመምህር አጋዥነት በራሱ አቅም ደረጃ በደረጃ እያነበበ፣ መልመጃዎችን እየሠራ ስሕተቱንም ወዲያውኑ እያረመ እንዲማርበት አስቤ ነው ያዘጋጀሁት፡፡

ከስተማሪያነት አንጻርም መምህራን በክፍል ውስጥ ትምህርቱን በቅደም ተከተል ለማቅረብ፣ የቤት ሥራዎችንና ፈተናዎችን ለማዘጋጀት የሚያስችላቸውን ስልታዊና ሥነ ዘዴያዊ አካሄድ ይዟል፡፡

 

ግእዝ አስቸጋሪ ቋንቋ ነው የሚል አመለካከት አለ። መጽሐፍዎ ይህን አመለካከት ለመቀየር ምን መፍትሔ ያቀርባል?

የግእዝ ቋንቋ አስቸጋሪ እንዲመስል ያደረገው የሴኩላሪዝም ስብከት (“ግእዝ ከባድ ነው፣ ውስብስብ ነው፣ የቄስ ብቻ ነው”የሚለው የተሳሳተ አመለካከት)፣ የእኛ ስንፍና እንዲሁም የገበያ መጻሕፍት ጥልቀት በሌለው መንገድ ተቀነጫጭበው መቅረባቸው ነው፡፡

“ኆኅተ ግእዝ” ይህንን ለመቀየር የሚከተሉትን መፍትሔዎች ይዟል፦ሕጎችን በአጫጭር፣ በቀላልና በግልጽ ምሳሌያዊ ዓረፍተ ነገሮች ያስረዳል፤በአማርኛ ቋንቋ በሚገባ አብራርቶ ምሳሌዎችን በግእዝና በአማርኛ ያቀርባል፤ ደረጃ በደረጃ የሚያድግ አቀራረብ በመከተል የተማሪውን የፍርሃት ስሜት ያስወግዳል፤ መጽሐፉ የሚጀምረው አንባቢው አስቀድሞ ከሚያውቃቸው ፊደላት (ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ…) በመሆኑ፣ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ውስብስብ ምሥጢራት ያለስጋት እንዲገባ ያደርገዋል፡፡

 

በዘመናችን ግእዝን መማር ለወጣቶችና ለአዲሱ ትውልድ ምን ጠቀሜታ አለው?

ወጣቶች ግእዝን ሲማሩ የሚያገኟቸው ዋና ዋና ጠቀሜታዎች፦ ማንነትን ማወቅ፦ የራስን ታሪክ፣ ባሕል፣ የቀደምት አባቶችን የፍልስፍና፣ የሥልጣኔና የጥበብ ደረጃ ለመረዳት ያስችላል፡፡

ቋንቋው በተጨማሪም ረቂቅ የሰዋስው ትንታኔ ያለውና የሚያመራምር በመሆኑ የአእምሮ የማሰብ አቅምን ያሳድጋል፤ የቋንቋ ችሎታም ያሳድጋ፤ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን በቀላሉ ለመማር በር ስለሚከፍት፡፡

በተጨማሪም ግእዝ የጥበብ ምንጭ በመሆኑ በምርምርና በተለያዩ የፈጠራ የሥራ መስኮች ዕድል ይፈጥራል፡፡

 

ግእዝ ከሃይማኖታዊ ትምህርት ባሻገር በኢትዮጵያ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ሥነ ጽሑፍና ባሕል ላይ ያለው አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

ግእዝ ጥንታዊ፣ ዓለም አቀፋዊና ቀዳሚ ልሳን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷን የምትፈጽምበት ልሳን ቢሆንም፤ ሃይማኖታዊ ብቻ ግን አይደለም፡፡

ይልቁንም፦ የነገሥታት ታሪክ፣ የዲፕሎማሲ ደብዳቤዎችና እንደ “ፍትሐ ነገሥት” ያሉ የሕግ መጻሕፍት የተመዘገቡበት ነው፡፡ የሥነ ጽሑፍ፣ የፍልስፍና፣ የሕክምና፣ የቅጠላ ቅጠል መድኃኒቶችና የሥነ ክዋክብት ዕውቀቶች የተከተቡበት ሀብት ነው፡፡ ለበርካታ የኢትዮጵያ ልሳናት መሠረትና መጋቢ የሆነ የታሪክ ማኅደር ነው፡፡

 

ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ…

ግእዝ የሞተ ቋንቋ ሳይሆን ሕያው ልሳን ነው፡፡ የአባቶቻችን ጥበብና ታሪክ መዝገብ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ማንነቱን እንዲያውቅ የግእዝን ቋንቋ በጽናት መማር ይኖርበታል፡፡

 

የሕይወት ልምድወን ስላጋሩን በበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ስም እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!።

 

 

(ሰናይት በየነ )

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here