በአፍሪካ ቀንድ እና በሰሜን አፍሪካ የጂኦፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደ ዓባይ ወንዝ የብዙ ሕዝቦችን እጣ ፈንታ የወሰነ እና የታሪክ መጋጨትን የፈጠረ ተፈጥሮአዊ ሀብት የለም። ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓባይ (ብሉ ናይል) ውኃ የምታመነጭ ብትሆንም የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የሆነችው ግብፅ ግን ወንዙን ሙሉ በሙሉ በብቸኝነት ለመቆጣጠር ያላሰለሰ ስልታዊ ጫና፣ የፖለቲካ ከበባ እና የታሪክ ሴራዎችን ስትሸርብ ኖራለች። ታዋቂው የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊክ “ኢትዮጵያ እና የመካከለኛው ምስራቅ (Ethiopia and the Middle East) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጹት የካይሮ ስትራቴጂካዊ ግብ ሁልጊዜም አንድ ነው፤ እሱም “ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት የተዳከመች፣ በኢኮኖሚ የደቀቀች እና የተከፋፈለች አድርጎ ማቆየት” ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ መጣጥፍ ግብፅ በታሪክ ሂደት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ለማደናቀፍ የተጠቀመችባቸውን ዋና ዋና ስልቶች፣ የዲፕሎማሲያዊ የክህደት ውሎች እና የቅርብ ጊዜ የከበባ ስራዎችን በማስረጃ አስደግፎ ይተነትናል።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኬዲቭ እስማኤል ፓሻ ትመራ የነበረችው ግብፅ የዓባይን ወንዝ መነሻ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እና የምስራቅ አፍሪካን ግዛት ለመቀላቀል የአውሮፓ እና የአሜሪካ ቅጥረኛ ወታደራዊ መኮንኖችን፣ ዘመናዊ የሬሚንግተን ጠመንጃዎችን (አሜሪካ ሰራሽ) እና መድፎችን በማሰለፍ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘመተች። ይሁን እንጂ ይህ ትዕቢት የተቀላቀለበት ወረራ በታሪክ የማይረሳ ታላቅ ውርደትን እና ሽንፈትን አተረፈባት፤ የመጀመሪያው መቅሰፍት የደረሰባት ኅዳር 16 ቀን 1875 ዓ.ም በታሪካዊው የጉንደት ጦርነት ወቅት ነበር። በኮሎኔል አዶልፍ አረንድሩፕ የሚመራው የግብፅ ወራሪ ጦር የጉንደት ሸለቆ ውስጥ ምሽግ ሰርቶ በነበረበት ወቅት በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ እና በታዋቂው የጦር መሪ ሻለቃ (በኋላ ራስ) አሉላ አባ ነጋ የሚመራው የኢትዮጵያ ጀግና ሰራዊት በጥንቃቄ ተንቀሳቅሶ በጥቂት ሰዓታት ድንገተኛ ጥቃት መሪውን አረንድሩፕን ጨምሮ ከ2,000 በላይ ወታደሮችን በመደምሰስ ዘመናዊ መድፎቻቸውን እና የሮኬት ማስወንጨፊያዎቻቸውን ማረከ።
ይህ የጉንደት ሽንፈት በካይሮ ቤተ መንግሥት ታላቅ ድንጋጤን እና ቁጭትን በመፍጠሩ እስማኤል ፓሻ የሀገሪቱን የተሸረፈ ክብር ለመመለስ እጅግ ግዙፍ እና በላቀ የጦር መሣሪያ የተደራጀ ሁለተኛ ጦር በሙሐመድ ራተብ ፓሻ እና በአሜሪካዊው ጄኔራል ዊሊያም ሎሪንግ እየተመራ በጉራዕ ሜዳ ላይ አሰማራ። ዐፄ ዮሐንስም የሀገርን ጥሪ በማስተላለፍ ከትግራይ፣ ከጎጃም እና ከወሎ የተውጣጣ ከ50,000 በላይ የጀግኖች ሰራዊት በማሰለፍ ከመጋቢት 7 እስከ 10 ቀን 1876 ዓ.ም በተደረገው እጅግ አስፈሪ እና ደማቅ የጉራዕ ጦርነት የግብፅን ምሽጎች ሰብረው በመግባት ወራሪውን ኃይል እንደ ቅጠል አረገፉት። ይህ ታላቅ ድል ካይሮ የምስራቅ አፍሪካን እና የዓባይን ወንዝ በጦር ኃይል የመቆጣጠር ህልሟን ሙሉ በሙሉ የቀበረባት ነበር ሲሉ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፦ “የኢትዮጵያ ታሪክ፦ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” በሚለው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በሀይል ኢትዮጵያን ከመግጠም በስውር የማዳከም ስልትን መጠቀም ጀመረች፡፡
የግብፅ የመጀመሪያው እና ትልቁ ስልት የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካዊ አለማረጋጋት ነው። ካይሮ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ልማት እና ወደ ዓባይ ወንዝ እንዳታዞር ለማድረግ በየዘመናቱ የተነሱ የውስጥ አማፂያንን፣ የነጻነት ግንባሮችን እና የብሔር ድርጅቶችን በገንዘብ፣ በስልጠና እና በጦር መሣሪያ ስትደግፍ ኖራለች። በተለይም በኤርትራ ነጻነት እንቅስቃሴዎች እና በሶማሊያ ወረራ ወቅት ግብፅ ከበስተጀርባ ሆና የነበራት ሚና የጎላ ነበር። ሀገራችን በረሃብና በርስ በርስ ጦርነት እንድትደማ በማድረግ፣ ትልልቅ የግድብ እና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማሰብ እንኳን አቅም እንዳይኖራት የማድረግ ስውር ስራ ለዘመናት ተተግብሯል ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ “Ethiopia and the Nile: Dilemmas of National and Regional Hydropolitics” በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጸዋል።
ሁለተኛው ስልት ኢትዮጵያን ያገለሉ እና በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጠሩ ኢ-ፍትሃዊ የውኃ ክፍፍል ውሎችን እንደ ዓለም አቀፍ ህግ አድርጎ የመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነው። እ.አ.አ በ1929 ዓ.ም በብሪታንያ እና በግብፅ መካከል እንዲሁም በ1959 ዓ.ም በግብፅ እና በሱዳን መካከል የተፈረሙት ስምምነቶች የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ ለሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ብቻ ያደላደሉ ነበሩ። ኢትዮጵያ የእነዚህ ውሎች ተጠቃሚም ሆነ ፈራሚ ባልነበረችበት ሁኔታ ግብፅ ዛሬም ድረስ እነዚህን ውሎች እንደ “ታሪካዊ መብት” በመቁጠር ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታደርገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለማፈን ትሞክራለች።
በሦስተኛ ደረጃ ግብፅ የኢትዮጵያን የልማት ፕሮጀክቶች ለማደናቀፍ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን እንደ መሣሪያ ስትጠቀም ቆይታለች። ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ግድብ ለመገንባት በምታቅድበት ጊዜ ሁሉ ካይሮ በዓለም ባንክ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ ላይ ያላትን ተጽዕኖ በመጠቀም ብድር እና እርዳታ እንዳይሰጥ ስታደርግ ኖራለች። ለዚህም ትልቁ ማረጋገጫ በ1950ዎቹ መገባደጃ ላይ ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያን ያገለለውን የ1959ኙን የውኃ ክፍፍል ስምምነት ሲያደርጉ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድርጊቱን በጽኑ በመቃወም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በሳይንሳዊ መንገድ ለመጠቀም የአሜሪካን የጥናት ቢሮ (USBR) ጋበዙ። ከ1956 እስከ 1964 ዓ.ም የተካሄደው እና ዛሬ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለተገነባበት የጉባ ስፍራ መሠረት የጣለው ይህ ጥናት በዓባይ ተፋሰስ ላይ አራት ግዙፍ ግድቦችን ለመገንባት ፍኖተ ካርታ አስቀምጧል፤ ነገር ግን በወቅቱ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የነበረው እና በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) ዋና ጸሐፊ የሆነው ስትራቴጂስቱ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ስውር የፋይናንስ ከበባ በማዘጋጀት ሴራውን አጋባው። ጋሊ የግብፅን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ በመጠቀም ማናቸውም የውጭ ብድር እና እርዳታ ለኢትዮጵያ እንዳይሰጥ በማገዱ እና የኢትዮጵያን የባህር በር የማሳጣት ፖለቲካዊ ስራዎችን ከበስተጀርባ ሆኖ በመደገፉ ሀገሪቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ያቀደችውን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት በወቅቱ እንዳትጀምር ትልቅ ዕንቅፋት ሆኗል።
ይሁን እንጂ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እነዚህን የካይሮ ተፅዕኖዎች ለመመከት እና የኢትዮጵያን ጽኑ አቋም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ እ.አ.አ በ1957 ዓ.ም የዛሬው የሕዳሴ ግድብ መመርያ የሆነውን ታሪካዊ ንግግራቸውን አደረጉ። ጃንሆይ በንግግራቸው፦ “ኢትዮጵያ ይህንን በተፈጥሮ የተቸረችውን ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ለወዳጅ የጎረቤት ሀገሮቿ በደግነት እና በለጋስነት ለማካፈል ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ብትሆንም በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የገዛ ሕዝቧ ፍላጎት እና ለኢኮኖሚዋ ዕድገት ሲባል ግን ይህንን የውኃ ሀብቷን ማልማት የኢትዮጵያ ቀዳሚና የተቀደሰ ብሔራዊ ግዴታዋ ነው፤ዛሬ እኛ በተለያዩ ምክንያቶች ግድም መገንባት አልቻልንም፤ ቀጣዩ ትውልድ ግን ይገነባዋል” በማለት የሀገሪቱን ሉዓላዊ መብት በታሪክ መዝገብ ላይ አትመዋል። ይህ ንግግር ኢትዮጵያ የሌሎችን ፍላጎት ሳትጎዳ የገዛ ሕዝቧን ለመመገብ ያላትን የማያወለውል አቋም ያሳየበት እና የግብፅን የዘመናት የብቸኝነት የበላይነት ሴራ የተጋፈጠበት ታላቅ የታሪክ ማኅተም ሆኖ ይኖራል።
በ1978 እ.አ.አ የፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ መጠነኛ የመስኖ እና የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ሲያቅድ ግብፅ በፈጠረችው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ከበባና የጦርነት ዛቻ ዕቅዱ እንዲሰናከል ተደርጓል።
ይህ የታሪክ ርዝራዥ ሴራ በቅርብ ጊዜ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅትም በግልጽ ታይቷል። ግብፅ ግንባታው ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱን ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ከበባ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጫናዎች እና አልፎ ተርፎም ወታደራዊ የኃይል አማራጮችን ስትዝት ቆይታለች። በአረብ ሊግ በኩል ኢትዮጵያን የማግለል ጥረቶች የከሸፉት ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማስፈረም የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በተመሳሳይ አቋም ማሰለፍ በመቻሏ ነው። ይሁን እንጂ ግብፅ ይህንን የዲፕሎማሲያዊ የበላይነት ስታጣ በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት በመፈረም እና ወታደሮቿን ወደ ሞቃዲሾ በማስገባት ኢትዮጵያን በጎረቤት ሀገር በኩል የመክበብ እና የሀይል ሚዛን የማዛባት አዲስ ስልት ተያይዛዋለች።
የግብፅ የታሪክ ሴራዎች የኢትዮጵያን ህልውና እና ልማት በቀጥታ የሚፈታተኑ ቢሆኑም ኢትዮጵያ እነዚህን ጫናዎች በዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ፣ በሕዝባዊ አንድነት እና በውስጥ አቅም በመመከት የሉዓላዊነት እና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን በጽናት እያስከበረች ትገኛለች። የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ እና የውኃ ሙሌቶቹ መሳካት የካይሮን የዘመናት የብቸኝነት የበላይነት ሴራ ሙሉ በሙሉ ያከሸፈ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። የዓባይ ወንዝ የወደፊት እጣ ፈንታ በግብፅ ፍፁም የበላይነት ሳይሆን በፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና በጋራ ልማት ላይ ብቻ ሊመሰረት እንደሚገባ ታሪክ እና ወቅታዊው እውነታ ይመሰክራሉ።
ሳምንቱ በታሪክ
በዓሉ ተወለደ
የኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ታላቅ ሰው እና በደርግ ዘመን የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት በድፍረት በመጋፈጡ ምክንያት ህይወቱን ያጣው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የተወለደው መስከረም 26 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር። በቀድሞው ኢሉባቡር ክፍለ ሀገር ሱጴ በተባለች ስፍራ ከህንዳዊ አባት እና ከኢትዮጵያዊት እናት የተወለደው በዓሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በአሜሪካ በመማር ከፍተኛ እውቀት ያካበተ ነበር፤ በሙያው የ”የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” እና “የኢትዮጵያ ሄራልድ” ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ (ምክትል ሚኒስትር) በመሆን ሀገሩን በጋዜጠኝነት ስራው በታማኝነት አገልግሏል። ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር “ከአድማስ ባሻገር”፣ “ሀዲስ” እና “ቅናት” በተሰኙት ድንቅ የልብ-ወለድ ስራዎቹ የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እውነታዎች በጥልቀትና በማራኪ የቋንቋ ስልት በመተንተን በኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ትልቅ አሻራ ጥሎ አልፏል።
ይሁን እንጂ በዓሉ ግርማ በ1976 ዓ.ም የጻፈውና በደርግ ታሪክ የመጨረሻዋ የሆነችው “ኦሮማይ” የተሰኘችው መጽሐፉ በኤርትራ የነበረውን “የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ” ስውር ፖለቲካ እና የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሙስና በድፍረት ያጋለጠች በመሆኗ የደርግን መንግሥት ክፉኛ አስቆጣች። ይህችው መጽሐፍ ከኃላፊነቱ እንዲባረር ምክንያት ከመሆኗም በላይ መጽሐፉ በታተመ በጥቂት ወራት ውስጥ የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም ከቤት እንደወጣ በደርግ የደህንነት አካላት ተጠልፎ እንዲሰወር እና ለህልፈተ ሕይወት እንዲዳረግ ዋነኛ መንስኤ ሆናለች። በዓሉ ግርማ እውነትን በመናገሩ ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል ሲል እንዳለ ጌታ ከበደ (ዶ.ር)”በዓሉ ግርማ፡ ሕይወቱና ሥራዎቹ” በተሰኘው መጽሐፉ ይገልጻል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


