ሁልጊዜ መማር

0
65

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቤተሰብ ሳሎን ውስጥ ከሁሉም በላይ ትልቅ ክብር ተሰጥቶት ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን አንድ ምስል እናስተውል፦

ጥቁር የጋውን ካባ የለበሰ፣ ኮፍያውን ወደ ሰማይ የወረወረ ወይም በደማቅ ቀይ ሪባን የታሰረ ወረቀት ይዞ በኩራት የሚመለከተን የምረቃ ፎቶግራፍ!

በዚያች ዕለት በጎች ይታረዳሉ፣ እናቶች እልልታቸውን ያቀልጣሉ፣ አባቶችም አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት ይመላለሳሉ። ዘመድ አዝማዱም በአንድ ድምፅ “እንኳን ደስ አላችሁ፤ ልጃችሁ ተምሮ ጨረሰ!” ይላል።

ነገር ግን ቆም ብለን እናስተውል፦ “ተምሮ መጨረስ” የሚባል ነገር በሕይወት ምድር ላይ በእርግጥ አለ?

ትልቁ የማኅበረሰባችን አባዜ የሚጀምረው ከዚሁ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ነው። ምረቃን እንደ አዲስ ጉዞ መጀመሪያ ሳይሆን እንደ ዕውቀት ማጠቃለያ አድርገን እንወስደዋለን።

ዛሬ በየከተማው ጎዳና ቢጫ ፖስታ ይዘው የሚንከራተቱ “የተማርኩት ሙያ አልጠቀመኝም” በሚል ምሬት የተሞሉ በርካታ ወጣቶች የሚታዩት ለዚህ ነው።

ያ በመስታወት ፍሬም ውስጥ የታጎረው ወረቀት የቋሚ ዕውቀት ማረጋገጫ ተደርጎ ስለታሰበ አእምሮ አዲስ ነገር መመገቡን ያቆማል።

ትናንት በቆሎ ተማሪነት ጥበብን ፍለጋ በቆሎንና ቆሎውን ቋጥረው ደጋና ቆላ ሲያቋርጡ የነበሩ አባቶቻችን “ሰው እስኪሞት ድረስ ይማራል” የሚለውን ጥልቅ ሚስጥር ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።

የዛሬው ዘመን ሰው ግን አንዲት የዲግሪ ወረቀት ሲቀበል ራሱን የጥበብ ሁሉ ቁንጮ አድርጎ ይቆጥራል።

ዛሬ ዓለም እኛ ባሰብነው ፍጥነት ሳይሆን በማይታሰብ ግስጋሴ እየተለወጠች ነው። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የድሮውን ሙያ እና እውቀት ዋጋ-ቢስ እያደረጉት ባሉበት በዚህ ወቅት በድሮ ማስታወሻዎች እና ባረጁ ማዕረጎች ተማምኖ መቀመጥ ራስን በገዛ ፈቃድ በድንቁርና እስር ቤት ማጎር ነው።

ትልቁ አደጋ ዕውቀት ማጣት ሳይሆን “ተምሬ ጨርሻለሁ” ብሎ መታበይ ነው።

ለዚህም ነው የዘመኑን እውነተኛ የድንቁርና ትርጉም ለመረዳት ከአራት አስርት ዓመታት በፊት የተነገረን አንድ አስደንጋጭ ትንቢት ዛሬ ደጃፋችን ላይ መጥቶ የሚሞግተን፦

ተመራማሪው እና ደራሲው አልቪን ቶፍለር “ፊውቸር ሾክ” በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፉ ላይ ለዘመናችን የሚሆን አንድ አስደንጋጭ ትንቢት አስፍሮ ነበር።

“የ21ኛው ክፍለ ዘመን ያልተማረ ሰው የሚባለው ማንበብና መጻፍ የማይችል ሳይሆን መማር፣ የተማረውን አሮጌ እውቀት መተው እና እንደገና አዲስ ነገር መማር (Learn, Unlearn, and Relearn) ያልቻለው ነው!” ብሏል።

ዛሬ በየቤቱ ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉት የዲግሪ ማስረጃዎች፣ የምረቃ ፎቶግራፎች እና የተቆለሉት ማዕረጎች ለብዙዎች የትምህርት ፍጻሜ ይመስላሉ።

እውነታው ግን ተቃራኒ ነው። መደበኛ ትምህርትህ ያበቃው በምረቃ ቀንህ ሊሆን ይችላል፤ እውነተኛው የሕይወት ትምህርትህ ግን የሚጀምረው ከዚያ በኋላ ነው።

ዓለም በየሰከንዱ አዳዲስ እውቀቶችን በምትፈለቅቅበት በዚህ ዘመን “ሁሉንም አውቄያለሁ” ብሎ መቀመጥ በራስ ፈቃድ ወደ ኋላ ለሚደረግ ጉዞ እጅ መስጠት ነው።

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ካሮል ድዌክ በዘርፉ አብዮት በፈጠረውና “ማይንድሴት: ዘ ኒው ሳይኮሎጂ ኦፍ ሰክሰስ” በተሰኘው የምርምር መጽሐፋቸው የሰዎችን የስኬት ሚስጥር በጥልቀት መርምረዋል። ድዌክ ሰዎችን በሁለት የአስተሳሰብ ጎራ ይከፍሏቸዋል፦

የመጀመሪያዎቹ “የተገደበ አስተሳሰብ” (Fixed Mindset) ባለቤቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች እውቀት፣ ተሰጥኦ እና ብልህነት ከተፈጥሮ የተሰጡ ቋሚ ቅርሶች ናቸው ብለው ያምናሉ። ውድቀትን ይፈራሉ፤ አዳዲስ ፈተናዎችን ከመጋፈጥ ይሸሻሉ፤ ምክንያቱም አለመሳካትን እንደ የግል ብቃት ማነስ አድርገው ስለሚቆጥሩት ነው።

በአንፃሩ “የእድገት አስተሳሰብ” (Growth Mindset) ያላቸው ሰዎች ደግሞ አእምሮ ልክ እንደ ጡንቻ በትጋት፣ በልምምድና በትምህርት ያለማቋረጥ ሊያድግ እንደሚችል ያምናሉ።

ለእነዚህ ሰዎች ስህተት የውድቀት ማረጋገጫ ሳይሆን የማደጊያ መማሪያ መድረክ ነው።  ድዌክ የብዙ ዓመታት ጥናት እንዳረጋገጠው በሕይወት ውስጥ የላቀ ስኬት እና ውስጣዊ እርካታ የሚያገኙት የተለየ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ያላቸው ሳይሆኑ ያልተቋረጠ የመማር እና የማደግ ጥማት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው።

ለብዙ አሥርት ዓመታት የሕክምናው ዓለም “የሰው ልጅ አእምሮ በልጅነት ብቻ አድጎ ከዚያ በኋላ የነርቭ ሴሎቹ መታደስ ያቆማሉ” የሚል የተሳሳተ እምነት ነበረው። ይሁን እንጂ ዘመናዊው የነርቭ ሳይንስ ይህንን የተሳሳተ ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ ሰባብሮታል።

ተመራማሪዎች “ኒውሮፕላስቲሲቲ” ብለው በሚጠሩት ግኝት እንዳረጋገጡት የሰው ልጅ አእምሮ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ አዳዲስ የነርቭ ትስስሮችን የመፍጠር፣ አዳዲስ ነገሮችን የመቀበልና ቅርፁን የመቀየር ተፈጥሯዊ አቅም አለው።

አንድ ሰው በ70 ዓመቱ አዲስ ቋንቋ መማር፣ አዲስ የሙዚቃ መሳሪያ መለማመድ ወይም አዲስ ቴክኖሎጂ መቅሰም ይችላል። አእምሮ የሚያረጀው በዕድሜ መግፋት ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችን መመገብና መፈተን ሲያቆም ብቻ ነው።

የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የወደፊቱን የሥራ ገበያ አስመልክቶ ባወጣቸው ተከታታይ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና አውቶሜሽን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባህላዊ ስራዎችን እየቀየሩት እንደሆነ ያሳያል።

ሪፖርቱ እንደሚያስጠነቅቀው ዛሬ በሥራ ዓለም ተፈላጊ ሆኖ ለመቀጠል ቁልፉ ነገር “የተማርከው ሙያ” ሳይሆን “በፍጥነት የመላመድ እና አዳዲስ ክህሎቶችን ያለማቋረጥ የመቅሰም ብቃት” ነው።

የአመራር ጥበብ መምህሩ ጆን ሲ. ማክስዌል “15 አይተኬ የእድገት ሕጎች” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው እድገት እንዲሁ በራሱ ጊዜ የሚመጣ የተፈጥሮ ሂደት አይደለም፤ ሆን ተብሎ ካልታቀደበት በስተቀር ዕድሜ ብቻውን ብስለት አያመጣም።

የአሜሪካው የኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ ሄንሪ ፎርድ በአንድ ወቅት የተናገረው ድንቅ አባባል አለ፦ “መማር ያቆመ ማንኛውም ሰው ዕድሜው ሃያም ሆነ ሰማንያ አርጅቷል፤ መማሩን የቀጠለ ሰው ግን ምንጊዜም ወጣት ነው።”

የዕድሜ ልክ ተማሪነት ማለት ሁልጊዜ የዩኒቨርሲቲ በር ማንኳኳት ማለት አይደለም። ይልቁንም፦

  1. የትህትና ልብ መያዝ፦ ሁሉንም አላውቅም፣ ከማንኛውም ሰው እና ሁኔታ አዲስ ነገር መማር እችላለሁ ብሎ ማመን ነው።
  2. ንባብን የዕለት ተዕለት ምግብ ማድረግ፦ በየቀኑ ጥቂት ገጾችን ማንበብ አእምሮን ከአስተሳሰብ ድርቀት ይታደጋል።
  3. ከስህተት ጋር መታረቅ፦ ውድቀትን እንደ ውርደት ሳይሆን እንደ ውድ የትምህርት ክፍያ መቀበል።

የሕይወት ትልቁ አደጋ ድንቁርና ሳይሆን “አውቃለሁ” የሚለው የውሸት እርካታ ነው። ያ በክብር ግድግዳህ ላይ የተሰቀለው ወረቀት የትናንት ጥረትህ መታሰቢያ እንጂ የነገ ብቃትህ ዋስትና ሊሆን አይችልም።

ዓለም በየቅጽበቱ አሮጌውን እውቀት እየቀበረች አዲሱን በምታነግስበት በዚህ አውድ ውስጥ ባለህበት ቆሞ መቅረት ወደ ኋላ እንደመራመድ ይቆጠራል።

ስለዚህ ያንን “ተምሬ ጨርሻለሁ” የሚል የአስተሳሰብ ድንበርህን ዛሬውኑ ሰባብረህ ጣለው። በየቀኑ አዲስ ገጽ የምትገልጥ፣ ስህተትህን እንደ ምርጥ አስተማሪ የምትቀበል፣ እና ሕይወትን ራሷን እንደ ታላቅ ዩኒቨርሲቲ የምታይ የዕድሜ ልክ ተማሪ ሁን።

አስታውስ፦ ትናንት የደረስክበት የዕውቀት ጣሪያ ለነገው መሠረትህ ብቻ ነው። ማደግን አታቋርጥ፤ አእምሮህን በየዕለቱ አድሰው፤ ምክንያቱም በፈጣን ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ በሕይወት የመኖሪያው ብቸኛው ቀመር “ሁልጊዜ መማር” ብቻ ነው!

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here