በረሃን ወደ አረንጓዴ ገነት መቀየር፣ በአሸዋ ላይ አዝመራ ማፍራት እና ከጠብታ ውኃ ሕይወትን ማለምለም ተረት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ይህ ተረት ሳይሆን መሬቷ ከግማሽ በላይ በረሃ በሆነችው እስራኤል ውስጥ ዕውን የሆነ ድንቅ እውነታ ነው። ከዚህ አስደናቂ የስኬት ታሪክ ጀርባ ያለው ዋነኛ ምስጢር ደግሞ ዓለምን ያስደነቀው የጠብታ መስኖ (Drip Irrigation) ቴክኖሎጂ ነው።
ይህች በውኃ እጥረት የተፈተነች ሀገር እንዴት የዓለም የግብርና ቴክኖሎጂ መሪ ልትሆን ቻለች? “የውኃ ማማ” ተብላ የምትጠራው እና አሁንም ድረስ በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተችው ኢትዮጵያስ ከዚህ ተሞክሮ ምን ልትማር ትችላለች?
እስራኤል አነስተኛ የውኃ ሃብቷ በምንም መልኩ እንዲባክን አትፈቅድም። አንድን የውኃ ሃብት እስከ ሦስት ጊዜ ለተለያዩ ተግባራት ጥቅም ላይ በማዋል እሷን የሚስተካከላት ሀገር የለም። ለመጸዳጃ ቤት ግልጋሎት የዋለ የውኃ ሀብቷን ሳይቀር እያጣራች እና እያከመች ለተለያዩ አገልግሎቶች በመጠቀም የዓለማችን ግንባር ቀደም ሀገር ሆናለች።
ሀገሪቱ የምትጠቀመውን ውኃ ከ70 እስከ 80 በመቶ መልሳ በማጣራት በጠብታ መስኖ ለግብርና ታውለዋለች። በዚህም በአነስተኛ ውኃ ከፍተኛ ምርት በማምረት ለዓለም ተምሳሌት ሆናለች።
እስራኤል አግሪ (www.israelagri.com) የመረጃ ምንጭ እንዳስነበበው እስራኤል የጠብታ መስኖን በዘርፉ በሰለጠኑ ኢንጂነሮቿ አማካይነት የጀመረችው ”ችግር ብልሃትን ይወልዳል” የሚለውን የሀገራችን ብሂል በተግባር ያሳየችበት ነው። እስራኤል በረሃማነት የሚያጠቃት ሀገር ብቻ ሳትሆን በተፈጥሮ የውኃ ሃብትን ካልታደሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት።
ሀገሪቱ ታዲያ ይህንን ችግሯን እጅ እና እግሯን አጣጥፋ አልተቀበለችውም። ዘርፈ ብዙ ልሂቃንን በማፍራት የታደለችው እስራኤል ኢንጂነሮቿ ያላትን አነስተኛ የውኃ ሃብት እያንዳንዷን ጠብታ ለመስኖ ልማት በማዋል እንድትጠቀም እያደረጓት ይገኛሉ። ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሬቷ በረሃማ እና ለግብርና የማይመች የነበረችው እስራኤል በ1960ዎቹ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂን በስፋት በማስተዋወቅ ታሪክ ቀይራለች። እስራኤላዊው መሃንዲስ ሲምቻ ብላስ (Simcha Blass) የቀየሰው ይህ ጥበብ ዛሬ የሀገሪቱን ፍጆታ ከመሸፈን አልፎ የግብርና ምርት ላኪ አድርጓታል።
እስራኤል የጠብታ መስኖን ከዘመናዊ የኮምፒውተር እና መለያ ማሽኖች (የሴንሰር ቴክኖሎጂ) ጋር በማስተሳሰር እያንዳንዱ ተክል የሚፈልገውን ትክክለኛ የውኃ እና ንጥረ- ነገር መጠን በሰከንዶች ውስጥ እንዲያገኝ አድርጋለች። በ1930ዎቹ የነበረው ሲምቻ ብላስ የተባለ እስራኤላዊ መሃንዲስ በአንድ የአትክልት ስፍራ ውስጥ ሌሎች ዛፎች ደርቀው አንዲት ዛፍ ግን ለምልማ ያያል። ምክንያቱን ሲመረምርም ከመሬት ስር ከተቀበረ የውኃ ቱቦ አንዲት ቀዳዳ በጠብታ መልክ የምታፈሰው ውኃ ለዛፏ ሕይወት እንደሰጣት ይገነዘባል።
ይህ ክስተት የዘመናዊው የጠብታ መስኖ ፅንሰ-ሐሳብ መነሻ እንደሆነ የእስራኤል የግብርና እና ገጠር ልማት ሚኒሥቴር (Israel Ministry of Agriculture and Rural Development) መረጃ ያመላክታል።
እስራኤል ይህን ጥበብ በማሳደግ ኔታፊም (Netafim) የተባለውን ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያ አቋቋመች። የቴክኖሎጂው ፍልስፍና እጅግ ቀላል ግን ኃያል ነው፡፡ መሬቱን ሳይሆን ተክሉን ብቻ ማጠጣት የሚያስችል ነበር፡፡
የጠብታ መስኖ ግን ውኃን እና ማዳበሪያን በቀጥታ ከተክሉ ስሩ ድረስ በጥንቃቄ እና በልክ ያደርሳል። በዚህም ምክንያት የውኃ ብክነትን ከ70 እስከ 80 በመቶ ይቀንሳል፤ የአረም እድገትን ይገድባል (ውኃው ባዶ መሬት ላይ ስለማይፈስ)፤ የምርት መጠንንም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል።
ዛሬ እስራኤል አብዛኛውን የግብርና ምርቷን በዚህ መንገድ የምታመርት ከመሆኑም በላይ ቆሻሻ ውኃን በማጣራት ለግብርና በመጠቀም የዓለማችን ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን ዓለም አቀፉ የውኃ አስተዳደር ተቋም (IWMI – International Water Management Institute) ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ከእስራኤል ምን ትማር?
ኢትዮጵያ ዋና ዋና የወንዝ ተፋሰሶች ያሏት፣ ዓባይ እና አዋሽን የመሳሰሉ ሰፊ ጸጋዎች የታደለች ሀገር ናት። ሆኖም አሁንም ድረስ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ዘርፍ በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው። ድርቅ በመጣ ቁጥር ዜጎቿ ለችግር ይጋለጣሉ። ኢትዮጵያ ከእስራኤል ልትወስዳቸው የሚገቡ አራት ወሳኝ ትምህርቶችም አሉ፡-
‘‘ችግር የፈጠራ እናት ናት’’ – የአስተሳሰብ ለውጥ
እስራኤላውያን የውኃ እጥረት ሲገጥማቸው ተስፋ አልቆረጡም፤ ይልቁንም ውኃን እንደ ወርቅ ቆጥረው እያንዳንዷን ጠብታ በአግባቡ መጠቀም ጀመሩ። የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የውኃ እጥረት ሳይሆን የውኃ አያያዝ እና አስተዳደር ጉድለት ነው። የመጀመሪያው ትምህርት የተትረፈረፈ ውኃ ቢኖርም እንኳ ውኃን እንደ ብርቅዬ ሃብት የመቁጠር እና የማስላት የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው።
ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሮች ማላመድ
የጠብታ መስኖ ለትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ብቻ የሚሆን ውድ ቴክኖሎጂ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። እስራኤል በስበት ኀይል ብቻ የሚሠሩ የኤሌክትሪክ ፓምፕ የማይፈልጉ አነስተኛ የጠብታ መስኖ ፓኬጆችን ለአነስተኛ አርሶ አደሮች አዘጋጅታለች። ኢትዮጵያ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ከውጭ ከማስገባት ባለፈ በሀገር ውስጥ በስፋት በማምረት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ማዳረስ ትችላለች።
የቆላማ እና ከፊል-በረሃማ አካባቢዎችን ማልማት
በእነዚህ አካባቢዎች የመሬት ውስጥ ውኃን በፀሐይ ኀይል በማውጣት እና በጠብታ መስኖ በመጠቀም ሀገሪቱን መመገብ የሚችሉ የፍራፍሬ፣ የስንዴ እና የአትክልት ጎተራዎች ማድረግ እንደሚቻል መረጃዎች አመላክተዋል።
የምርምር፣ የፖሊሲ እና የተግባር ትስስር
የእስራኤል ስኬት የሳይንቲስቱ፣ ፖሊሲ አውጪው እና የአርሶ አደሩ ጥብቅ ትስስር ውጤት ነው። ስለሆነም መንግሥት መስኖን ለሚጠቀሙ አርሶ አደሮች የግብርና እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸት እና የስልጠና ድጋፍን ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡
ኢትዮጵያ የገጸ-ምድር እና የከርሰ – ምድር ውኃ ሃብት የታደለች ናት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የውኃ እና ለም መሬት እያላቸው በዝናብ እጥረት ሳቢያ ለድርቅ እና ለምግብ እጥረት የሚጋለጡ ሀገራት ከእስራኤል ልምድ በርካታ ቁም ነገሮችን መቅሰም ይችላሉ። የተፈጥሮ ሃብት ውስንነት ለእድገት እንቅፋት ሳይሆን ለፈጠራ መነሻ ሊሆን እንደሚችል የእስራኤል ተሞክሮ ህያው ምስክር ነው። አነስተኛ ውኃን በመጠቀም ከፍተኛ ምርት ማምረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተግባር ማስገባት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ዋነኛው መፍትሔ ነው።
የእስራኤል የመስኖ ልማት ታሪክ የሚያስተምረው ትልቁ እውነት የግብርና ምርታማነት ምስጢር ያለው በውኃው ብዛት ላይ ሳይሆን እያንዳንዱን የውኃ ጠብታ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም አግባብ ባለው መንገድ አገልግሎት ላይ በማዋል መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በበጋ ስንዴ ልማት የታየው መነቃቃት መስኖ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እጣ ፈንታ የመቀየር አቅም እንዳለው በተግባር አሳይቷል። በዚህ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ ያሏት የተፈጥሮ ጸጋዎች እና በተለይም የአማራ ክልል ያለው የመስኖ ሀብት የጎላ ድርሻ አላቸው። የተጀማመሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች የሚበረታቱ ናቸው፡፡
የወንዝ ላይ ዳርቻ ልማት እና የበጋ መስኖ ስንዴ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው። ይሁን እንጂ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ባህላዊውን የጎርፍ መስኖ ወደ ዘመናዊው የጠብታ መስኖ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። እስራኤል ከአሸዋ ላይ ፍሬ ካፈራች ኢትዮጵያ የታደለችውን ለም አፈር እና በጋውን በሙሉ የሚፈስ ወንዝ በጠብታ መስኖ ጥበብ ከተጠቀመችው የራሷን ሕዝብ መመገብ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ማቅረብ ትችላለች።
መረጃ
ዋና ዋና የመስኖ ዓይነቶች
የገጽታ መስኖ
በመሬት ስበት ኀይል ብቻ በመጠቀም ውኃን በማሳው ላይ፣ በቦዮች ወይም በተፋሰሶች ውስጥ በማፍሰስ የሚከናወን ጥንታዊ የመስኖ ዓይነት ነው።
የሚረጭ መስኖ
ግፊት ያላቸውን ቧንቧዎች እና መርጫዎችን በመጠቀም የተፈጥሮ ዝናብን በሚመስል መልኩ ውኃ በሰብሎች ላይ የሚረጭበት ዘመናዊ ዘዴ ነው። ይህ አሠራር ወጣገባ ለሆነ መሬት እና ለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች እጅግ ተስማሚ ነው።
የጠብታ መስኖ
ውኃን በትንንሽ ቱቦዎች አማካኝነት በቀጥታ ወደ ተክሎች ሥር በጠብታ የሚያደርስ እጅግ ውኃ ቆጣቢ ነው።
የማዕከላዊ ሽክርክሪት መስኖ
በአንድ ማዕከላዊ ምሰሶ ዙሪያ በክብ (በ360 ዲግሪ) እየተሽከረከረ ውኃ የሚያጠጣ ባለጎማ ሜካናይዝድ አሠራር ነው።
የጎን /መስመራዊ/ መስኖ
ከማዕከላዊ ሽክርክሪት መስኖ ጋር ተመሳሳይነት ቢኖረውም አሠራሩ ግን አራት ማዕዘን ቅርጽ ባላቸው ሰፋፊ ማሳዎች ላይ በቀጥታ መስመር (ወደ ፊትና ወደ ኋላ) እየተጓዘ ውኃን በእኩል መጠን የሚያዳርስ ነው።
የከርሰ ምድር መስኖ
ከመሬት ወለል በታች (በተክሉ ሥር አካባቢ) በተቀበሩ ቱቦዎች አማካኝነት ውኃን በቀጥታ ለተክሉ የሚያቀርብ ዘዴ ነው። ይህም በፀሐይ ሙቀት ምክንያት የሚፈጠረውን የውኃ ትነት ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።
በእጅ የሚደረግ መስኖ
በውኃ ማጠጫ ጣሳዎች፣ በቱቦዎች ወይም በባልዲዎች አማካኝነት የሰው ጉልበትን በመጠቀም የሚከናወን ቀለል ያለ ዘዴ ነው።
ምንጭ፦ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO)
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


