ከፍርስራሽነት ወደ ልዕልና – የጃፓን ጉዞ

0
73

ከከባድ ውድመት ማግስት እንዴት ማንሰራራት ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ በመሆን  በአብነት ትጠቀሳለች – ጃፓን፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ ወደ ፍርስራሽነት ከተቀየረችበት በመነሳት አሁን ላይ የዓለም የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ እና የስልጣኔ ማዕከል ለመሆን በቅታለች፡፡ ተፈጥሮ ፊቷን ያዞረችባት፣ በተደጋጋሚ በተፈጥሮ አደጋዎች በሚታመስ ምድር ላይ የቆመችው ይህች ሀገር የሰው ኃይልን እና የሥራ ባሕልን ትልቅ ሀብት በመጠቀም የሠራችው ተአምር ለቀሪው ዓለም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡

የጃፓን አመሠራረት እና አቀማመጥ

ጃፓን በምሥራቅ እስያ የምትገኝ የደሴት ስብስብ  ሀገር ናት፤ በምሥራቅ በፓሲፊክ ውቅያኖስ እና በምዕራብ በጃፓን ባሕር የተከበበች ናት፤ ይህ ስትራቴጂካዊ አቀማመጧም በባሕር ንግድ እንድትበለፅግ እና ከውጭ ወረራ እንድትጠበቅ ረድቷታል፡፡

በጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሕበራዊ ድረ ገጽ ላይ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የጃፓን ታሪክ እና አመሠራረት ከቅድመ አፈ – ታሪክ እና በጥንታዊ የሺንቶ (Shinto) እምነት ባሕል ጋር የተሳሰረ ነው፡፡

ጃፓን እንደ ሀገር የተዋቀረችው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ660 ዓ.ዓ ነው፤ የመጀመሪያው ንጉሥም ንጉስ ጂሙ እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል፡፡ ጃፓናዊያን ሀገራቸው የተመሰረተችበትን ቀንን በየዓመቱ የካቲት 11 ያከብራሉ፡፡

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና ጃፓን

በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ሕዝብ እና ቁሳዊ ውድመት ከተከሰቱባቸው ወቅቶች መካከል የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፤ ጃፓን ደግሞ እጅግ የከፋ እልቂትን ያስተናገደች ሀገር ናት፡፡ ለዚህ ዋናው አብነት ደግሞ ጦሱ አሁንም ድረስ ያልጠፋው በሂሮሽማ እና ናጋሳኪ የደረሱት የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታዎች ናቸው፡፡

የሂሮሽማ እና ናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ ድብደባ እና ያስከተለው መዘዝ

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ እ.አ.አ ነሐሴ 1945 አሜሪካ በጃፓን ላይ የኒውክሌር ቦምብ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን የመጀመሪያው አቶሚክ ቦምብም “ሊትል ቦይ” ተብሎ የተሰየመ ነበር፡፡ ይህ ቦምብ ነሐሴ 06 ቀን 1945 እ.አ.አ በሄሮሺማ ላይ ተጣለ፡፡ ነሐሴ 09 ቀን 1945 እ.አ.አ ደግሞ “ፋት ማን” የተሰኘው ሁለተኛው ቦምብ ናጋሳኪን ደበደበ፡፡ በዚህም በሁለቱ ከተሞች ከ140 ሺህ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

አቶሚክ ቦምቡ በተጣለበት ቀጣና የተለቀቀው ጨረርም ለበርካታ ዓሥርት ዓመታት ለካንሰር የሚያጋልጥ እና ሕጻናት ሲወለዱ ሙሉ አካል ይዘው እንዳይወለዱ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ጦርነቱ የጃፓንን ኢኮኖሚ አናግቶት ነበር፡፡ በአማካይ 13 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሰዎችም ሥራ አጥ ነበሩ፡፡

ይህን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ በወቅቱ የሀገሪቱ ገዥ የነበሩት ንጉሥ ሂሮሂቶ እ.አ.አ ነሐሴ 15 ቀን 1945 ጃፓን እጅ እንደሰጠች አውጁ፤ በዚህም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጠናቅቋል፡፡

ከጦርነት ፍርስራሽ ወደ ኢኮኖሚ ገናናነት

ጃፓን ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማሕበራዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ተንኮታኩታ ነበር፡፡ ሆኖም በ30 ዓመታት ውስጥ ከአንድ እስከ አምስት ከሚጠሩት ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው የዓለማችን ሀገራት ተርታ ገብታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜም በሀገር ውስጥ ምርት በአራተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በጠቅላላ ብሔራዊ ሀብቷ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የዓለም ገንዘብ ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ይህን ዕድገት እንድታስመዘግብ ያደረጓት ምክንያቶችም በርካታ ናቸው፡፡ ዋናው ምክንያት ከጦርነቱ በኋላ በወጣው ሕገ – መንግሥት (አንቀጽ 9) ጃፓን ጦር ቀስቃሽነት እና የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት መዳፈርን አስወግዳለች፡፡ ይህም ለጦርነት ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ በጀት ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ እና መሠረተ ልማት እንድታዞር አድርጓታል፡፡ በጥቅሉ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጃፓን አጠቃላይ የሰላም ፍልስፍናን ተቀብላለች፡፡ ዜጎቿም ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የወደቀው የአቶሚክ ቦምብ ያስከትለውን እጅግ አስከፊ ውድመት በተግባር ስላዩ ለጦርነትና ለግጭት ያላቸው አመለካከት በፍጹም አይደገምም (Never Again) የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ጦርነትን የችግር መፍትሔ አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ በሕብረተሰቡ ዘንድ እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡

አሜሪካም ጃፓንን መልሳ ለመገንባት ያደረገችው ድጋፍ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Dodge Plan) መረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ ጃፓን ትኩረቷን በጥራት ላይ ያደረጉ የኢንዱስትሪ ምርቶች ማለትም እንደ ቶዮታ፣ ሆንዳ፣ ኒሳን፣ ሶኒ እና ፓናሶኒክ ላይ ማድረጓ እና “ካይዘን ኮንቲኒየስ ኢምፕሩቭመንት” የተሰኘውን የጥራት ፍልስፍና በመከተሏ የዓለምን ገበያ ለመቆጣጠር አስችሏታል፡፡ የመንግሥት ሚኒስቴር እና ግዙፍ ኩባንያዎችም ተቀናጅተው መሥራታቸው የኢኮኖሚውን ዕድገት ፈጣን ማድረጉን ሂስትሪስኪልስ ድረገጽ ላይ ያገኘነው ማስረጃ ያትታል፡፡

ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ሌላኛው የጃፓን ተአምራዊ ዕድገት ምስጢር በዋናነት  የማሕበረሰቡ  ዕሴቶች እና ባሕል ነው፡፡ በጃፓን ያሰቡትን እስኪያሳኩ እጅ አለመስጠት እና እስከመጨረሻው መጣር የሕይወት መመሪያቸው ነው፡፡ ጃፓናዊያን ለሥራቸው ያላቸው ቁርጠኝነት በጣም ከፍተኛ ነው፤ በሥራ እና በምርት ጥራት ላይ ፍጹምነትን የመሻት ፍላጎታቸውም የላቀ ነው፡፡

በጃፓን ተማሪዎች እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ምንም አይነት ፈተና አይፈተኑም፤ ትምህርታቸው የሚያተኩረው ስነ-ምግባር፣ ሰው አክባሪነት እና ንፅህና አጠባበቅ ላይ ነው፡፡ በዚህም ተማሪዎች የትምህርት ቤታቸውን ቅጥር ግቢ እና መማሪያ ክፍሎቻቸውን፣ መጸዳጃ ቤታቸውን እና የመመገቢያ አዳራሻቸውን በራሳቸው ያጸዳሉ፤ ይህም የሥራ ክቡርነትን እና ኃላፊነትን በለጋ ዕድሜያቸው እንዲያውቁ ረድቷቸዋል፡፡

ጃፓኖች ሰዎችን ሰላም ለማለት፣ ለማመስገን ወይም ይቅርታ ለመጠየቅ ዝቅ ብሎ እጅ መንሳት የዕለት ተዕለት ስነ-ምግባራቸው ነው፡፡ በባቡር ውስጥ በስልክ አለመነጋገር፣ ቆሻሻ በየቦታው አለመጣል እና የሌሎችን ሰላም አለመሻማት የጸና ሕጋቸው ነው፡፡

ሌላው ጃፓኖች ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ባሕላቸው ለእንደኛ አይነት ሀገር ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ነው፡፡ በጃፓን ሰዓት ማክበር ማለት ልክ በሰዓቱ መገኘት ሳይሆን ከአምስት እስከ 10 ደቂቃ ቀድሞ መገኘት ማለት ነው፡፡

የጃፓን ፈጣን ባቡሮች ከ20 ሴኮንድ በላይ ከዘገዩ ኩባንያው ይቅርታ ይጠይቃል፤ ለተሳፋሪዎችም በሥራ ቦታቸው የሚያስረዱበት የዘገዩበትን ምክንያት ማረጋገጫ ወረቀት ይሰጣል፡፡ በጃፓን በቀጠሮ ወቅት በጊዜ መገኘት የትህትና እና የሰዎች ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ትልቁ መገለጫ ነው፡፡ ማረፈድ እጅግ ትልቅ ነውር እና ክብር ማጣት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት እና የተፈጥሮ አደጋዎችን የመቋቋም ጥበብ

ጃፓን የማዕድን፣ የነዳጅ ወይም የእርሻ መሬት ሀብት የላትም፡፡ አብዛኛው የመሬት ክፍሏ (ወደ 70% ገደማ) በተራራዎች የተሸፈነ ነው፡፡ ትልቁ የተፈጥሮ ሀብቷ ደን፣ የዓሳ ሀብት እና የተማረ የሰው ኃይል ነው፡፡

ጃፓን በዓለም ላይ ለተፈጥሮ አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ከተጋለጡ ሀገራት አንዷ ናት፡፡

የሀገሪቱ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ እንዳብራራው ሀገሪቱ የምትገኘው ሪንግ ኦፍ ፋዬር (የእሳተ ገሞራ እና የምድር መንቀጥቀጥ ቀለበት) ተብሎ በሚጠራው የፓስፊክ ውቅያኖስ ቀጣና ውስጥ ነው፡፡ ይህ አቀማመጧም በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት መንቀጥቀጦች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በጃፓን የሱናሚ እና የኃይለኛ ታይፉን አውሎ ንፋስ አደጋዎችም በተደጋጋሚ ይከሰታሉ፡፡

ይሁንና  ጃፓን ተፈጥሮን ለመዋጋት ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖር የሚያስችል ረቂቅ ቴክኖሎጂ እና ሥርዓት ዘርግታለች፡፡ ለአብነትም  ሴስሚክ  ኢንጀነሪንግ    (Seismic Engineering) የሚባለውን የሕንፃዎች ግንባታ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ አድርጋለች፤ ይህ የምህንድስና ቴክኖሎጂ ሕንፃዎች የምድር መንቀጥቀጥ ሲከሰት የሚፈጠረውን የመናጥ ኃይል እንዲቋቋሙ ያደርጋቸዋል፡፡

ሕንፃዎች ሙሉ በሙሉ ተደርምሰው በሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መለጠጥ/መታጠፍ የሚችል ተፈጥሮ እንዲኖራቸው ተደርገው ነው የሚገነቡት፡፡ የሀገሪቱ የሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲም የመሬት መንቀጥቀጡ ከመድረሱ ከሰከንዶች በፊት በስልክ ጥሪ፣ በቴሌቪዥን እና በራዲዮ አውቶማቲክ ማስጠንቀቂያዎችን ለዜጎች ያደርሳል፡፡

ጃፓናዊያን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በትምህርት ቤት አደጋ ሲከሰት እንዴት ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸው ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱ መስከረም አንድ  “ብሔራዊ የአደጋ ዝግጁነት ቀን” ተደርጎም ይከበራል፡፡

ጃፓን እና ሀገር በቀል እድገት

ጃፓን የሀገር በቀል እውቀትን፣ ባህልን እና ጥንታዊ እሴቶችን ከዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ(Hybridization) ረገድ በዓለም ላይ ግንባር ቀደም ምሳሌ የምትሆን ሀገር ናት፡፡ ጃፓናዊያን ምዕራባዊውን ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ሲቀበሉ የራሳቸውን ማንነትና የሀገር በቀል እውቀት አልጣሉም፡፡ ይህ አካሄድ በጃፓንኛ “ዋኮን ዮሳይ” (Wakon Yosai) ይባላል፤ ትርጉሙም “የጃፓን መንፈስ ከምዕራባዊያን እውቀት ጋር” ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከጃፓን ምን ተሞክሮ ትውሰድ?

ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውድመት በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመሆን የቻለችበት ሚስጢር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ ማስተማሪያ ነው፡፡

ጃፓን በየቀኑ አነስተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ የሥራ ጥራትንና ምርታማነትን የማሳደግ ፍልስፍና አላት፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ፍልስፍና በኢንዱስትሪዎች፣ በግብርና እና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሰፊው በመተግበር ብክነትን መቀነስና ቅልጥፍናን ማሳደግ ትችላለች፡፡ ለምርቶች ጥራትና ለፈጠራ ሥራ የሚሰጠውን ትኩረት በማዳበር የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻላል፡፡

ጃፓን ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ትምህርት እንዲሁም ለሙያና ቴክኒክ ስልጠና ከፍተኛ ትኩረት ትሰጣለች፡፡

ኢትዮጵያም የሰው ኃይሏን በቴክኖሎጂና በፈጠራ ለማብቃት የትምህርት ጥራትን ማሻሻል ይኖርባታል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here