በአንድ አገር ታሪክ ውስጥ መሪዎች ይመጣሉ፤ይሄዳሉ፤ የፖለቲካ ማዕበሎች ይነሣሉ፤ ይረግባሉ፤ ርዕዮተ ዓለማትም ያብባሉ፤ ይጠወልጋሉ፡፡ ታዲያ አንዲትን አገር ከትውልድ ወደ ትውልድ በጽናት የሚያሻግራት ምስጢር ምንድን ነው? አገር በግለሰቦች መልካም ፈቃድና ጊዜያዊ ስሜት ላይ ብቻ የምትመሠረት ከሆነ፤ የመሪዎች መለወጥ የህልውናዋ ማክተሚያ፣ የፖለቲካ ንትርክ ደግሞ የመፍረሷ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንጻሩ ጸንተው በቆሙ ተቋማት የምትመራ አገር፤ ማናቸውንም የፖለቲካ ውጣ ውረዶች ተሻግራ ቀጣይነቷን ታረጋግጣለች፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) አገረ መንግሥትን አጽንቶ ስለማቆየት፣ ስለ አዲስ መንግሥት ምሥረታ ምንነት፣ ስለ ተቋማት ሚና እንዲሁም ስለ ብቃት አስተዳደር (ሜሪቶክራሲ) ከበኩር ጋር ቆይታ በማድረግ ጥልቅ ሙያዊ ትንታኔ ሰጥተውናል፡፡
የመንግሥት ምሥረታ፦ የሕዝብ ውል ወይስ የስልጣን ሽኩቻ?
አዲስ መንግሥት መመሥረት ሲባል ብዙዎች በካቢኔ አባላት መለዋወጥ ወይም በቤተ መንግሥት ወንበሮች መያዝ ብቻ ያጥሩታል፡፡ ዶክተር ደሴ ጥላሁን እንዳሉት ግን፣ የመንግሥት ምሥረታ ትርጉም ከዚህ እጅግ የላቀ ፍልስፍናዊና ሕጋዊ መሠረት አለው፡፡
በአንድ በኩል፣ እንደ ጆን ሎክና ዣን ዣክ ሩሶ ያሉ ፈላስፎች የሚያነሡትን የማኅበራዊ ውል ንድፈ ሐሳብ ማስታወስ ይገባል፡፡ ዜጎች ከተፈጥሯዊ ነጻነታቸው ቀንሰው የጋራ ሰላምና ደኅንነታቸውን የሚያስጠብቅ ልዕለ ኃይል የሚፈጥሩበት ሂደት ነው፤ በመሆኑም አዲስ መንግሥት መመሥረት ማለት ይህ ማኅበራዊ ውል የሚታደስበት አሊያም አዲስ መልክ የሚይዝበት ሁነት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጉዳዩ የሕገ መንግሥታዊ ቅቡልነት ጥያቄ ነው፡፡ ዶክተር ደሴ እንዳብራሩት ቡድኖች ሥልጣን ስለያዙ ብቻ መንግሥት አይመሠረትም፤ ይልቁንም በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መዋቅር፣ ቀመርና ሥነ ሥርዓት መሠረት ሲጓዝ ብቻ ነው ተቀባይነት ያለው መንግሥት የሚወለደው፡፡
ዶክተር ደሴ ጥላሁን የመንግሥት ምሥረታ የሚከሰትባቸውን ሦስት ገፊ ምክንያቶች ያነሣሉ፤ ከምርጫ በኋላ የሚከናወን፦ በዴሞክራሲያዊ አሠራር አሸናፊው አካል ሕጋዊ ሥልጣን የሚረከብበት ሂደት ነው፤
ከቀውስ ወይም ከመንግሥት መፍረስ በኋላ፦ የሕዝብ አመኔታ በማጣት፣ በጦርነት ወይም በፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ በማጣት ምክንያት አዲስ አስተዳደር የሚዋቀርበት ሁኔታ ነው፤ የሥርዓት ለውጥ ሲያጋጥም፦ አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ ሥር ነቀል ለውጥ ሲያደርግ የሚፈጠር ነው፡፡
ለምሳሌ በኢትዮጵያ በ1967 ዓ.ም የዘውድ ሥርዓቱ በደርግ ሲተካ እንዲሁም በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የታየው የመንግሥት ምሥረታ ሂደትን ተጠቃሽ ማድረግ ይቻላል፡፡
የጠንካራ ተቋማት አስፈላጊነት፦ የአገረ መንግሥት ዐምዶች
አንዲት አገር ጸንታ እንድትቆም ተቋማት እንደ ጀርባ አጥንት ማገልገል አለባቸው፡፡ ያለ ጠንካራ ተቋማት የሚገነባ አገር ልክ በአሸዋ ላይ እንደተሠራ ቤት ነው፡፡ ዶክተር ደሴ ጥላሁን ጠንካራ ተቋማት ለምን እንደሚያስፈልጉ ሲያስረዱ፣ የመጀመሪያው ፋይዳቸው የአገረ መንግሥት ቀጣይነትን (State Continuity) ማረጋገጥ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ መሪዎች፣ ፓርቲዎችና ርዕዮተ ዓለሞች ቢቀያየሩም፣ የተቋማት መጽናት የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ሳይናጋ አገር እንድትቀጥል ያደርጋል፡፡
ሁለተኛው መሠረታዊ ጉዳይ የሥልጣን ክፍፍልና ቁጥጥር ሥርዓት ነው፡፡ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሞንቴስኪዩ እንዳስገነዘበው፣ ያልተገደበ ሥልጣን የተሰጠው አካል ጻድቅ ቢሆን እንኳ ወደ አምባገነንነት ማዘንበሉ አይቀሬ ነው፡፡
ስለሆነም ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እና ሕግ ተርጓሚው ተቋም አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት አሠራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተመሳሳይ የሕግ የበላይነት ሊሰፍን የሚችለው የሰዎች የበላይነት (Rule of Men) ቀርቶ የሕግ የበላይነት (Rule of Law) ሲነግሥ ብቻ እንደሆነ ዶክተር ደሴ ያብራራሉ፡፡ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ሲያስከብሩ በዜጎችና በመንግሥት መካከል አመኔታ ይፈጠራል፤ ይህ አመኔታ ደግሞ ባለሀብቶች ያለምንም ፍርሃት ኢንቨስት እንዲያደርጉና ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ በር ይከፍታል፡፡
የጠንካራ ተቋማት መገለጫዎችና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች
“አንድ ተቋም ጠንካራ ነው የሚያሰኙት መመዘኛዎች ምንድን ናቸው?” ስንል ለዶክተር ደሴ ጥያቄ አንስተንላቸዋል፤ እርሳቸውም የሚከተሉትን ዋና ዋና መለኪያዎች በመዘርዘር ነው ሙያዊ ማብራሪውን የሰጡን፡-
o ተቋማዊ ነጻነት፦ ተቋማት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው ውሳኔዎቻቸውን በሕግ፣ በዕውቀትና በሙያዊ ብቃት ላይ ብቻ መመሥረት አለባቸው፡፡
o ግልጽነትና ተጠያቂነት፦ አሠራሮች ለሕዝብ ይፋ መሆን አለባቸው፤ የተዛቡ ውሳኔዎች በፍርድ ቤት የሚታረሙበት የአስተዳደር ሕግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል፡፡
o ተደራሽነትና ፍትሐዊነት፦ አገልግሎቶች ከከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ ለሁሉም ዜጋ በእኩልነትና ያለምንም አድልዎ መዳረስ አለባቸው፡፡
o አካታችነት፦ ዳሮን አሲሞግሉና ጄምስ ሮቢንሰን “መንግሥታት ለምን ይወድቃሉ? – Why Nations Fail” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳስረዱት፣ ተቋማት የብዙኃኑን መብትና የንብረት ባለቤትነት የሚያከብሩ አካታች መሆን አለባቸው እንጂ የጥቂት ልሂቃን መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም፡፡
“ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ስንቃኝ ተቋማት አገርን ከጥፋት እንዴት እንደሚታደጉ ግልጽ ማሳያዎች እናገኛለን” ይላሉ ዶክተር ደሴ፤ ለአብነትም በዩናይትድ ኪንግደም ያለውን ተሞክሮ ነው ያነሱት፡፡ በሀገሪቱ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ስድስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተፈራርቀዋል፤ ሊዝ ትረስ የተባለው መሪ በሥልጣን ላይ የቆየችው ለ49 ቀናት ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም አገሪቱ አልፈረሰችም፤ ምክንያቱም ጠንካራ የፓርላማ፣ የፍትሕና የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ስላሏት ሥርዓቱ በራሱ ጊዜ ማዕበሉን አልፏል፡፡
በአሜሪካም የፔንታጎን መከላከያ ኃይል ለሕገ መንግሥቱ እንጂ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ፍላጎት ተገዢ ባለመሆኑ ጸጥታው አስተማማኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በሕንድ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት አገር፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን በመኖሩ ግዙፉ ዴሞክራሲ በሰላም ይመራል፡፡ በጀርመን ጠንካራ የማዕከላዊ ባንክ ዲሲፕሊንና ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አገሪቱን ከናዚ ውድቀት በኋላ ወደ ታላቅ ምጣኔ ሀብታዊ ኃይልነት አሸጋግረዋታል፡፡
ወሳኙ ውሕደት፦ ሜሪቶክራሲን ከዴሞክራሲ ጋር ማጣጣም፣
ዶክተር ደሴ ጥላሁን በትንታኔያቸው ማጠቃለያ ላይ ያሰመሩበት ታላቅ ቁም ነገር፣ የብቃት አስተዳደርን (ሜሪቶክራሲን) ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጋር ማጣጣም የሚለውን መርሕ ነው፡፡
በአሜሪካ እስከ 1883 እ.ኤ.አ ድረስ ያሸነፈ ፓርቲ የራሱን ታማኞች ብቻ ወደ ቢሮክራሲው የሚያስገባበት የፖለቲካ ምርኮ ሥርዓት (Spoils System) ይከተሉ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንታቸው ጄምስ ጋርፊልድ ሥልጣን ባልተሰጠው ደጋፊ ከተገደለ በኋላ ግን አሠራሩን በመቀየር ሲቪል ሰርቪሱ በብቃት ላይ እንዲመሠረት የሚያደርገውን የፔንድልተን ሕግ (Pendleton Act) አወጡ፡፡
የሲንጋፖሩ መሪ ሊ ኩዋን ዩም የተፈጥሮ ሀብት ያልነበራትን ደሴት ወደበለጸገች አገር የቀየሯት ምርጥ አዕምሮዎችን በብቃት ብቻ በመመልመልና ተወዳዳሪ ክፍያ በመስጠት ባዋቀሩት ቢሮክራሲ አማካኝነት ነው፡፡ ማክስ ዌበር እንዳስተማረው ቢሮክራሲ ከፖለቲካ ታማኝነት ይልቅ በዕውቀት ላይ መገንባት አለበት፡፡
እንደ ዶክተር ደሴ ማብራያ ለአገራችን ህልውና ሁለት የማይነጣጠሉ ምሰሶዎች ያስፈልጉናል፦
የዴሞክራሲ ምሰሶ፦ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመሥረት ተዓማኒና ነጻ ምርጫ ማካሄድ ይገባል፡፡
የሜሪቶክራሲ ምሰሶ፦ ወደ ሲቪል ሰርቪሱና ወደ ተቋማት አመራርነት የሚገቡ ሰዎችን በዘር፣ በዝምድና ወይም በፖለቲካ አገልጋይነት ሳይሆን በዕውቀትና በብቃት ብቻ መመደብ ግድ ይላል፡፡
ተቋማት በፖለቲካ ታማኞች ብቻ ከተሞሉ ብቃት አልባነት (ሚዲዮክራሲ) ይነግሣል፤ ሚዲዮክራሲ ደግሞ የመንግሥትን አገልግሎት ያዛባል፤ ሙስናን ያበዛል፤ በመጨረሻም አገርን ያፈርሳል፡፡
አገራችንን ከዘመናት የፖለቲካ ቀውስ አውጥተን ዘላቂ አገረ መንግሥት ለመገንባት ጥንካራ ተቋማትን ወደ መገንባት መሸጋገር ግድ እንደሚል ዶክተር ደሴ ጥላሁን ያስገነዝባሉ፡፡
በመጨረሻም “አገር የምትጸናው በጠንካራ ተቋማትና በብቃት አስተዳደር ላይ ብቻ ነውና ዛሬውኑ ተቋሞቻችንን በዕውቀትና በሕግ መሠረት ላይ እንገንባ” ሲሉ ነው ሙያዊ ማብራያቸውን ያጠቃለሉት።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


