ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ

0
127

ቀይ ባሕር ደማችን አሁንም ቀይ ናት፣

ጀግኖች በትግላቸው እስካሁን ያቆዩዋት፤

ለጠላት ዘንዶ ነው የቀይ ባሕር አሳ፣

ውጦ ያስቀረዋል አሳይቶ አበሳ፤

(ድምጻዊ መስፍን ኃይሌ)

የኢትዮጵያ ታሪክ ከቀይ ባሕር ጋር ያለው ትስስር ጥልቅ፣ የስልጣኔዋ ምንጭ፣ የሉዓላዊነቷ መገለጫ እና የደህንነቷ ዋስትና ሆኖ የኖረ የሺህ ዓመታት ታሪክ ነው።  ሆኖም ግን ይህ ወሳኝ የህልውና በር በረጅም የታሪክ ሂደት፣ በውጭ ኃይላት ቀጣይነት ያለው ወረራ እና በውስጥ የፖለቲካ ተለዋዋጭነቶች እና ስልታዊ ስህተቶች ምክንያት ቀስ በቀስ እየጠበበ ሄዶ በመጨረሻም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ እጅ ሊወጣ ችሏል።

  1. የታሪካዊ ትስስር ወርቃማ ዘመን እና የቀይ ባሕር ጠቀሜታ፦

-የአክሱም ስልጣኔ እና የአዱሊስ ወደብ ገናናነት

በጥንቱ ዓለም የኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ላይ የነበራት የበላይነት ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ እስከ መጀመሪያዎቹ  ክፍለ-ዘመናት የደረሰ ነበር። የአክሱም ስልጣኔ በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ ኃይላት (ሮም፣ ፋርስ እና ቻይና) ተርታ እንዲሰለፍ ያደረገው ዋነኛው ምክንያት የአዱሊስ ወደብ ባለቤት መሆኑ ነበር።

-የመካከለኛው ዘመን እና የ”ባህረ-ነጋሽ” መዋቅር

የእስልምና ስልጣኔ መነሳትን ተከትሎ አረቦች የቀይ ባሕርን ደሴቶች እና ወደቦች መቆጣጠር ሲጀምሩ የአክሱም ማዕከላዊ መንግሥት ወደ ደቡብ (ወደ ውስጠኛው የየብስ ክፍል) ቢያፈገፍግም የኢትዮጵያ ነገሥታት ግን የባሕር ጠረፉን ለማስከበር ጥረታቸውን አላቋረጡም ነበር። በተለይም በሰለሞናዊው ስርወ-መንግሥት መነሳት (በ13ኛው ክፍለ ዘመን) እና በ15ኛው ክፍለ ዘመን በነገሡት በታላቁ ንጉሥ ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን የባሕር በሩን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል “ባህረ-ነጋሽ” (የባሕር ንጉሥ / የባሕር ገዥ) የተባለ ልዩ የሥልጣን መዋቅር ተዘረጋ።

-የጂኦፖለቲካ እና የደህንነት ጥቅሞች

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ በር ብቻ ሳይሆን የሀገር ደህንነት መከላከያ ጋሻም ነበር። ከሰሜን እና ከምሥራቅ የሚመጡ ወራሪ ኃይላት ወደ ሀገሪቱ መሀል ከመግባታቸው በፊት የሚገቱት በባሕር ጠረፉ ላይ ነበር። ቀይ ባሕርን መቆጣጠር ማለት ከክርስቲያኑ የዓለም ክፍል (በተለይም ከአውሮፓ ነገሥታት) ጋር የዲፕሎማሲ እና የቴክኖሎጂ (የጦር መሣሪያ) ግንኙነት ለማድረግ ዋነኛው መንገድ ነበር። ይህ በር ሲዘጋ ግን ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ተከባ ከዓለም እንድትገለል እና የቴክኖሎጂ እድገቷ እንዲገታ ያደርጋት ነበር።

  1. ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ እጅ የወጣበት ታሪካዊ መንገድ፦

ምዕራፍ 1፦ የኦቶማን ቱርክ መስፋፋት

በ16ኛው ክፍለ ዘመን መካከለኛ ክፍል ላይ የኦቶማን ቱርክ ግዛት የምሥራቅ አፍሪካን የቀይ ባሕር ዳርቻ ለመቆጣጠር ሰፊ ዘመቻ አደረገ። በ1557 እ.አ.አ የቱርክ ጦር አዛዥ የነበረው ኦዝደሚር ፓሻ የወደብ ከተማዋን ምጽዋን እና አርኪቆን ተቆጣጠረ። ቱርኮች ይህንን ይዞታቸውን “የሀበሻ ክፍለ-ሀገር” በሚል አደራጁት።

ምዕራፍ 2፦ የጣሊያን ቅኝ ግዛት መስፋፋት እና የ”ኤርትራ” መፈጠር

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የአውሮፓ ኃይላት አፍሪካን ለመቀራመት ያደረጉት ፉክክር የቀይ ባሕርን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ቀየረው። የኢጣሊያ መንግሥት በሩባቲኖ የንግድ ኩባንያ አማካኝነት በ1869 እ.አ.አ የአሰብን ወደብ ከአካባቢው የአፋር ሱልጣኖች በገንዘብ ገዛች። ይህ ለጣሊያን በአፍሪካ ቀንድ እግሯን ለመትከል የመጀመሪያው በር ሆነ።

ዐፄ ዮሐንስ ግብጾችን ሁለት ጊዜ ለወረራ መጥተው አሳፍረው መልሰዋቸዋል፡፡ የዐፄ ዮሐንስን መሞት ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት ዐፄ ምኒልክ ከጣሊያን ጋር ግንኙነታቸውን ለማስተካከል እና የሥልጣን እውቅና ለማግኘት ሲሉ በሚያዚያ ወር 1889 እ.አ.አ የውጫሌ ውልን ተፈራረሙ። የዚህ ውል አንቀጽ 3 ጣሊያን በሰሜን የያዘቻቸውን ይዞታዎች (አስመራንና አካባቢውን) ሕጋዊ እውቅና ሰጠ። ይህንን ይዞታ መሠረት በማድረግ ጣሊያን በጥር 1 ቀን 1890 እ.አ.አ “ኤርትራ” የምትባለውን አዲስ የቅኝ ግዛት በይፋ አወጀች። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል ብታደርግም በወቅቱ ከነበሩት ውስብስብ የፖለቲካ እና የወታደራዊ አቅርቦት ሁኔታዎች የተነሳ ዐፄ ምኒልክ ጣሊያንን ከኤርትራ ሳያባርሩ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ብቻ አስከብረው ተመለሱ። ይህም ኤርትራ በጣሊያን እጅ ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት እንድትቆይ አደረገ፤ በዚህም ኢትዮጵያ የባሕር በሯን በሕግ ደረጃ አጣች።

ምዕራፍ 3፦ የፌዴሬሽን ዘመን

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጣሊያን በጦርነቱ በመሸነፏ የኤርትራ እጣ ፈንታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ሆነ። አራት ታላላቅ ኃይላት (አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ሶቪየት ህብረት) በኤርትራ ጉዳይ ላይ መስማማት ስላልቻሉ ጉዳዩ ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመራ። በዐፄ ኃይለ ሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ “ኤርትራ የታሪካዊቷ ኢትዮጵያ አካል ናት ያለ ባሕር በር መቅረት የለብንም” የሚል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ክርክር አደረገ። በመጨረሻም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 390(A) መሠረት በ1945 ዓ.ም ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ተወሰነ።

በ1955 ዓ.ም የኤርትራ ምክር ቤት ፌዴሬሽኑን ማፍረሱን እና ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ መዋሃዱን አወጀ። ይህ ውሳኔ በኤርትራውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን አስነሳ፤ አስቀድሞ ተጀምሮ የነበረውን የታጠቀ የነፃነት ትግል (በጄብሃ እና ሻዕቢያ መሪነት) ይበልጥ አቀጣጠለው። ይህ ክስተት ለ30 ዓመታት የዘለቀውን እና የሀገሪቱን መዋቅር ያደቀቀውን የእርስ በርስ ጦርነት ወለደ።

ምዕራፍ 4፦ የደርግ መውደቅ

የ30 ዓመቱ ከባድ ጦርነት ማክተሚያው የደረሰው በ1983 ዓ.ም ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራው የደርግ ወታደራዊ መንግሥት በገጠመው የኢኮኖሚ መዳከም እና የወታደራዊ ሽንፈት ምክንያት ወደቀ። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አዲስ አበባን ሲቆጣጠር፣ የኤርትራ ሕዝባዊ ነፃነት ግንባር (ሻዕቢያ) ደግሞ አስመራንና የወደብ ከተማዎችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ።

በግንቦት 24 ቀን 1993 እ.አ.አ ኤርትራ በይፋ ሉዓላዊት ሀገር ሆና ስትታወጅ ኢትዮጵያም ያላትን የባሕር በር ሙሉ በሙሉ አጣች። ምንም እንኳን ከ1991 እስከ 1998 እ.አ.አ ድረስ ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ በነፃ የመጠቀም መብት ቢኖራትም በ1990 ዓ.ም የተነሳው የኢትዮ-ኤርትራ (የባድሜ) ጦርነት ግንኙነቱን ሙሉ በሙሉ አቋረጠው። በዚህም ምክንያት የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘጉ።

  1. የባሕር-አልባነት

ኤርትራ መገንጠሏን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ (በአሁኑ ወቅት ከ120 ሚሊዮን በላይ) ሕዝብ ያላት በዓለም ላይ ትልቁ የባሕር በር የሌላት (Landlocked) ሀገር ለመሆን በቃች። ይህ የታሪክ ተለዋዋጭነት በሀገሪቱ ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ እና ዘርፈ-ብዙ ነው፦

የኢኮኖሚ ጫና እና የወደብ ኪራይ ወጪ፦ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ካጣች በኋላ ከ95% በላይ የወጪ እና ገቢ ንግዷን የምታካሂደው በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው። ለሀገሪቱ የዕለት ተዕለት ፍጆታ፣ ለነዳጅ እና ለልማት ዕቃዎች የምታወጣው የወደብ ኪራይ እና የታሪፍ ወጪ በዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፤ ይህም በኢኮኖሚዋ ላይ እጅግ ከባድ ሸክም ሆኖባታል።

ስልታዊ ጥገኝነት፦ ለአንድ ታላቅ ሀገር የንግድ ህልውና በአንድ አነስተኛ ሀገር (በጅቡቲ) ወደብ ላይ ብቻ ጥገኝነት ማሳደር በጂኦፖለቲካ ረገድ ከፍተኛ አደጋ አለው። በጅቡቲ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም የታሪፍ ጭማሪ የኢትዮጵያን ህልውና በቀጥታ ይነካል።

የደህንነት እና የባሕር ኃይል መፍረስ፦ የባሕር በር ማጣትን ተከትሎ በአንድ ወቅት በቀይ ባሕር ላይ ገናና የነበረው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ተደርጎ ነበር (ምንም እንኳን በቅርብ ዓመታት ዳግም የማቋቋም ጥረት ቢደረግም)። ይህን የባሕር ኃይል እንዲሁም አጠቃላይ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ሂደት ግብጽ ትቃወማለች፤ ይህም ኢትዮጵያ በቀጠናው ብሎም በአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ጠንካራ ሀገር ከሆነች አሁን እንደልብ ያለ ከልካይ የምትጠቀመውን የዓባይ ወንዝ ትከለክለኛለች በሚል ትፈራለች፤ ግብጽ በስዊዝ ካናል ላይ እንደምታስከፍለው ሁሉ ኢትዮጵያም ለዓባይ ወንዝ ከፍያ ትጠይቀኛለች የሚል ስጋት አላት፡፡

 

ሳምንቱ በታሪክ

ጥቅምት እና ኢትዮጵያ

ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ለመመከት ከመሀል ሀገር ወደ ሰሜን ታላቁን የጀግንነት የክተት ጉዞ ጀመሩ፤ ይህም ለታላቁ የዓድዋ ድል ዋነኛ ወታደራዊ መሠረት ሆነ።

ጥቅምት 5 ቀን 1900 ዓ.ም ዐፄ ምኒልክ ሀገሪቱን በዘመናዊ የካቢኔ መዋቅር ለመምራት የጦር ሚኒስቴርን (የአሁኑን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር) በይፋ አቋቋሙ፤ የመጀመሪያው ሚኒስትር አድርገውም ስልታዊውን መሪ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲናግዴን (አባ መላ) በመሾም መደበኛውን ሠራዊት በተማከለ የአዛዥነት ሰንሰለት ስር አደራጁ ሲሉ ሀጋይ ኤርሊክ “ራስ አሉላ እና የአፍሪካ ቅርምት” በተሰኘው መጽሐፋቸው አስቅምጠዋል።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here