በእቅድ መመራት ስንል አንድን ሥራ ከመስራታችን በፊት ምን ማድረግ እንዳለብን፣ መቼ እንደምናደርገው እና እንዴት እንደምናከናውነው አስቀድመን የምንወስንበት ጥበብ ነው። ልጆች ገና በታናሽነታቸው የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በእቅድ እንዲመሩ ማስተማር ወደፊት ለሚጠብቃቸው ትልቅ ሕይወት መሠረት ይጥልላቸዋል። እቅድ ማውጣት ልጆች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከመርዳቱም በላይ ትኩረታቸውን ሳይበታተን የሚፈልጉት ነገር ላይ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል።
አንድ ልጅ በእቅድ መመራት ሲጀምር በሕይወቱ ውስጥ የሚታየው የመጀመሪያው ትልቅ ለውጥ የጊዜ አጠቃቀም ክህሎት ነው። ለጨዋታ፣ ለትምህርት፣ ለንባብ እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ የሚሆን የተመጣጠነ ጊዜ እንዲኖረው ያደርጋል። ይህ ደግሞ ልጆች ድንገተኛ ውጥረት እና ጭንቀት ውስጥ እንዳይገቡ ይጠብቃቸዋል። ለምሳሌ ፈተና ከመድረሱ በፊት በየቀኑ ጥቂት ሰዓት መድበው የሚያጠኑ ልጆች የፈተና ቀን ሲደርስ ያለምንም ፍርሃት በልበ ሙሉነት ይፈተናሉ።
በእቅድ መመራት ልጆች ኃላፊነትን የመውሰድ እና ራሳቸውን የመግዛት አቅማቸውን ያሳድጋል። የራሳቸውን የጊዜ ሰሌዳ አውጥተው በዚያ መሠረት ሲንቀሳቀሱ በሌሎች ሰዎች ግፊት ሳይሆን በራሳቸው ፍላጎት ሥራዎችን ማከናወን ይለምዳሉ። ያቀዱትን ነገር ነጥብ በነጥብ ሰርዘው ሲያጠናቅቁ የሚሰማቸው የውስጥ እርካታና ደስታ በራሳቸው የመተማመን ስሜታቸውን በእጅጉ ይገነባዋል። ይህም ሰነፍና ሰበብ አብዦዎች እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ሲል የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የልጅ ልማት ማዕከል ድረገጽ ያስገነዝባል።
በእቅድ መመራት ለልጆች የሚሰጠው ጥቅም ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂው የሕይወት ጉዟቸው የሚጠቅም ትልቅ ስጦታ ነው። ወላጆች እና መምህራን ልጆች ቀላል እቅዶችን (ለምሳሌ የዕለት ማስታወሻ መጻፍ) እንዲያወጡ ማበረታታትና አርአያ መሆን ይኖርባቸዋል። ዛሬ በትንሹ በእቅድ መመራት የለመደ ልጅ ነገ ሀገሩን እና ዓለምን የሚጠቅም ስልጡን፣ ስኬታማ እና የተረጋጋ ስብዕና ያለው ትልቅ ሰው ሆኖ ያድጋል።
ተረት
አይጥ እና እንቁራሪት
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ለምለም መስክ ላይ የምትኖር አንዲት ምስኪን አይጥ ነበረች። ይህች አይጥ በአቅራቢያው ከሚገኝ ኩሬ ውስጥ ከምትኖር በአንድ እንቁራሪት ጋር የጠበቀ ጓደኝነት መሰረቱ። በየቀኑ አብረው እየተጫወቱና እየተጋገዙ ረጅም ጊዜ አሳለፉ። ሆኖም ግን እንቁራሪቱ በውስጡ ክፉ እና ምቀኛ ነበረ፤ በአይጧ ደስታ እና ቅንነት ይቀና ነበር።
አንድ ቀን እንቁራሪቱ አይጧን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አንድ ተንኮል አሰበ። ወደ አይጧ ቀርቦ “ጓደኛዬ ሆይ ወዳጅነታችን ይበልጥ እንዲጠነክርና የትም ቦታ ስንሄድ እንዳንጠፋፋ እግርሽን በእግሬ ላይ በገመድ አብረን እንሰረው” አላት። አይጧም በቅንነት ተስማማችና እግራቸውን በጠንካራ ገመድ አሰሩ።
መጀመሪያ ላይ በየብሱ ላይ አብረው እያነከሱ ሲጫወቱ ቆዩ። ነገር ግን ወደ ኩሬው አቅራቢያ ሲደርሱ እንቁራሪቱ ያሰበውን ተንኮል ለመተግበር በድንገት ወደ ውኃው ውስጥ ዘለለ። አይጧ ውኃ መዋኘት ስለማትችል “እባክህ አውጣኝ፣ እየሰመጥኩኝ ነው!” እያለች ብትጮኽም ክፉው እንቁራሪት ግን ሳይራራላት ይበልጥ ወደ ውኃው ጥልቀት እየሳባት ገባ። ምስኪኗ አይጥም በውኃው ውስጥ ትንፋሽ አጥታ ህይወቷ አለፈ፤ በገመዱ ምክንያት ግን አስከሬኗ በውኃው ላይ ተንሳፎ ቀረ።
በዚህ ጊዜ አንድ ትልቅ ጭልፊት በሰማይ ላይ እየበረረ ሳለ በውኃው ላይ የተንሳፈፈችውን አይጥ ተመለከተ። ወዲያውኑ ቁልቁል ተወርውሮ አይጧን በረዣዥም ጥፍሮቹ ጨበጣት እና ወደ ሰማይ ይዟት በረረ። ነገር ግን እንቁራሪቱ እግሩ ከአይጧ ጋር በገመድ በጥብቅ ታስሮ ስለነበር እሱም አብሮ ከውኃው ተስቦ ወጣ። ጭልፊቱም ደህንነቱ በተጠበቀ ዛፍ ላይ አርፎ አይጧንም ክፉውን እና ተንኮለኛውን እንቁራሪትም በአንድ ላይ ለምሳው ተመገባቸው።
የተረቱ ምስጢር በሰው ላይ ክፉ የቆፈረ መጀመሪያ እራሱ ይገባበታል። ለሰዎች መልካም ማሰብ እና በታማኝነት መኖር እራሳችንን ከጥፋት ይጠብቀናል።
ሞክሩ
- ሁለት ጎረቤታሞች መተያየት ግን አይችሉም?
- መሬት ላይ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ ትልቁ እንስሳ ማን ይባላል?
- ዓባይ ወንዝ መነሻ ምንጭ ማን ናት?
መልስ
- ዓይኖች
- ዝሆን
- ሰከላ
ነገር በምሳሌ
-“ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ”፡- አንድን ነገር በአግባቡ እና በልኩ መሥራትን ያመላከታል፡፡
-“ካለመናገር ደጅ አዝማችነት ይገራል”፦ በጊዜው እና በአግባቡ አለመናገር ወይም መብትን አለማስከበር ትልቅ ክብርንና የሥልጣን ዕድልን ጭምር ሊያሳጣ ይችላል።
-“የታገሰ ቆቅ ያጠምዳል”፦ ቆቅ ለመያዝ ትዕግሥት እንደሚያስፈልግ ሁሉ በሕይወት ውስጥም ትልልቅ እና ከባድ ስኬቶችን ለማግኘት መታገስ እና ነገሮችን በትዕግስት መከታተል ያስፈልጋል ማለት ነው።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


