በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ድብ ዳቦ ማከፋፈያ ውስጥ ገብቶ ሲበላ በመታየቱ በቀጣናው ለጥበቃ አካላት በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በቦታው ሲደርሱ የማከፋፈያው ጥበቃ ሰራተኛ አስፈራርቶት አደጋ ሳያደርስ ከአካባቢው ሊያርቀው መቻሉን ዩፒአይ ድረ ገፅ ለንባብ አብቅቶታል።
የአይን እማኞች የዳቦ ማከፋፈያ ሰራተኞችም ንጋት ላይ ከፍተው ሽያጭ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሳሉ ድቡ ገብቶ የተከመረውን ዳቦ ሲበላ በሞባይል ስልካቸው መቅረፃቸውን እና ሁነቱን ለቀጣናው የፖሊስ ፅ/ቤት ማሳወቃቸውን አስረድተዋል።
የኮሎራዶ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት መምሪያ ቃል አቀባይ ጆይ ሊቪንግስተን እንደተናገሩት በተጠቆመው ቦታ ሲደርሱ የማከፋፈያው ጥበቃ በማስፈራራት ለማባረረ ሲሞክር አስተውለዋል። ጥቂት ቆይቶም ድቡ በራሱ ጊዜ ቀጣናውን ለቆ መራቁን አረጋግጠዋል። የቀጣናው ፓርኮችና የዱር እንስሳት መምሪያም የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤነት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ድቦች በሰዎች መኖሪያ ቀጣና ዘልቀው በተደጋጋሚ መታየታቸውን ነው ያብራራው።
ድቦች ራሳቸውን ለማትረፍ በ(ሰርቫይቫል ኦፍ ዘፊተስት) ንድፈ ሐሳብ መሰረት በክረምት ሐይል የሚሆን የምግብ ክምችት ለማጠራቀም በአደን የሚያገኙት ምግብ በማጠሩ በቀላሉ ወደ ሰዎች መኖሪያ ቀጣና መግባታቸው እና ትኩሱን የዳቦ ሽታ በተፈጥሮ ከርቀት የማሽተት አቅም የተቸረውን ድብ ስቦ ወደ ማከፋፈያው እንዳስገባው ነው በማደማደሚያነት የተብራራው።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


