ማንያራ ሐይቅ ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ ሰሜናዊ ክልል ነው የሚገኘው፡፡በውብ መልከአምድራዊ አቀማመጡ እና ሰፊ ብዝሃ ህይወት ሀብት መገኛነቱ በጎብኝዎች ተመራጭ መዳረሻ ሆኗል፡፡
ለፓርኩ ስመገናናነት ጉልህ ያበረከቱት ድር ዛፍ ላይ የሚንጠላጠሉ አናብስት አስደናቂ መስህቦች ናቸው፡፡የፓርኩ ጠቅላላ ስፋት 648.7 ካሬ ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው በማንያራ ሐይቅ የተሸፈነ ነው፡፡
የፓርኩ መግቢያ ከአሩሻ ከተማ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነባር ጎሣዎች መገበያያ በሆነው ምቶዋምቡ ከተማ አቅራቢያ ነው የሚገኘው፡፡
በሀይቁ ዙሪያ ረግረጋማ እና ደን ለበስ ሜዳማ ቀጣናዎች ይታዩበታል፡፡ በአካል ግዝፈት ካላቸው የዱር እንስሳት ዝሆን፣ ጎሽ፣ አንበሳ፣ የሜዳ አህያ፣ ጉማሬ፣ ዝንጀሮ … መገኘታቸው ተረጋግጧል፡፡
ከዓዕዋፍ ፔሊካን፣ ዓሣ በል ንስር፣ሽመላ፣“ስፖንቢል”፣ “ስቶርክ” የመሣሰሉት ይገኛሉ፡፡
ከእፅዋት ማንያራ ሐይቅን በከበበው ቀጣና ግርጌ የተለያዩ ዝርያዎችን ባካተተ ደን የተሸፈነ ነው፡፡ ደኑ ከሐይቁ ውኃ የሚገኝ በመሆኑ ጥቅጥቅ፣ የሀይቁ ዳርም ረግረጋማ ነው፡፡ጎብኚዎች ወደ ስፍራዉ ሲያቀኑ የፀሀይ መከላከያ ባርኔጣ ማድረግ እና ደማቅ ቀለም ያልበዛባቸው ልብስ መልበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የዱር እንስሳቱን ለመመልከት ደረቁ /ከሀምሌ እስከ ጥቅምት/ በጀልባ ለሽርሽር ተጉዋዦች ከኅዳር እስከ ሰኔ ያሉት ወራት ይመከራሉ፡፡
ለጎብኝዎች ማረፊያም ሎጂዎች እና ሪዞርቶች ይገኛሉ፡፡የፓርኩ የበላይ አስተዳደርም የታንዛኒያ ብሔራዊ ፓርኮች ባለስልጣን ነው፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት አፍሪካን ቪው ድረገጽ፡-ፓራዳይዝ ዋይልደርነስ እና ታንዛኒያ ፓርክስ ዶት ኦርግን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


